ገላትያ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየእግዚአብሔር ልጆች ስለ መሆናችን 1 አሁንም የምለው ይህን ነው፤ ወራሹ ሕፃን ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ምንም እንኳ የንብረቱ ሁሉ ጌታ ቢሆን ከባሪያ በምንም አይለይም። 2 ነገር ግን አባቱ የወሰነለት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በሞግዚቶችና በመጋቢዎች ሥር ነው። 3 እንዲሁም እኛ በመንፈሳዊ ነገር እንደ ሕፃናት በነበርንበት ጊዜ ለዚህ ዓለም ሥርዓት ተገዢዎች ሆነን ባሪያዎች ነበርን። 4 ነገር ግን የተወሰነው ዘመን በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከልን፤ እርሱ ከሴት ተወለደ፤ ለሕግም ታዛዥ ሆነ። 5 ይህንንም ያደረገው ከሕግ ሥር ያሉትን ለመዋጀትና እኛም የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን ለማድረግ ነው። 6 የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችንም እግዚአብሔርን “አባባ” እያለ የሚጠራውን የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን ላከ። 7 ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅ ከሆንክም የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ። ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች የነበረው ጭንቀት 8 ከዚህ በፊት እግዚአብሔርን ባለማወቃችሁ ምክንያት በባሕርያቸው አማልክት ላልሆኑት ባሪያዎች ሆናችሁ ትገዙ ነበር። 9 አሁን ግን እግዚአብሔርን ዐውቃችኋል፤ ይልቁንም እግዚአብሔር እናንተን ዐውቋችኋል፤ ታዲያ፥ ወደ እነዚያ ወደ ደካሞችና ወደማይረቡት የዓለም ሥርዓቶች እንዴት ተመለሳችሁ? እንዴትስ እንደገና የእነርሱ ባሪያዎች ለመሆን ትፈልጋላችሁ? 10 ለተለዩ ቀኖችና ወሮች ለተወሰኑ የዓመት ክፍሎችና ዓመቶች ጥንቃቄ በማድረግ ልዩ ክብር ትሰጣላችሁ። 11 በእናንተ መካከል በሥራ የደከምኩበት ድካም ሁሉ ከንቱ ሆኖ ይቀራል ብዬ እፈራለሁ። 12 ወንድሞች ሆይ! እኔ እንደ እናንተ ስለ ሆንኩ እናንተም እንደ እኔ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ፤ እናንተ ምንም አልበደላችሁኝም። 13 በመጀመሪያ ጊዜ የምሥራቹን ቃል ለእናንተ ለመስበክ ዕድል ያገኘሁት በሕመም ላይ በነበርኩበት ጊዜ መሆኑን ታውቃላችሁ። 14 ምንም እንኳ ሕመሜ ፈተና ቢሆንባችሁ አልናቃችሁኝም ወይም አልተጸየፋችሁኝም፤ እንዲያውም የእግዚአብሔርን መልአክ እንደምትቀበሉ አድርጋችሁ ተቀበላችሁኝ፤ እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስን እንደምትቀበሉ አድርጋችሁ ተቀበላችሁኝ። 15 ከዚህ በፊት የነበራችሁ ደስታ ሁሉ የት ሄደ? ቢቻልስ ዐይኖቻችሁን እንኳ አውጥታችሁ ትሰጡኝ እንደ ነበረ እኔ ራሴ እመሰክርላችኋለሁ። 16 ታዲያ፥ አሁን እውነትን ስለ ነገርኳችሁ ጠላታችሁ ሆኜ ተገኘሁን? 17 ሌሎች ሰዎች ስለ እናንተ በመጨነቅ ያስባሉ፤ ይሁን እንጂ ይህን የሚያደርጉት ለመልካም አይደለም፤ የእነርሱ ፍላጎት እናንተ ከእኛ እንድትለዩና ለእነርሱ በትጋት እንድታስቡ ነው። 18 ዓላማው ጥሩ ከሆነ መትጋት ምንጊዜም መልካም ነው፤ ነገር ግን ይህ መትጋታችሁ እኔ ከእናንተ ጋር በምኖርበት ጊዜ ብቻ አይሁን። 19 ልጆቼ ሆይ! ክርስቶስ በእናንተ ላይ ተቀርጾ እስኪታይ ድረስ እንደገና ስለ እናንተ በምጥ ጭንቅ ላይ እገኛለሁ። 20 ከበፊቱ የተለየ ሁኔታ እንዳሳያችሁ አሁን ከእናንተ ጋር መሆን በፈለግሁ ነበር፤ ነገር ግን ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ባለማወቄ ግራ ገብቶኝ ተጨንቄአለሁ። የአጋርና የሣራ ምሳሌነት 21 እናንተ ለሕግ ተገዢዎች ሆናችሁ መኖር የምትፈልጉ እስቲ ንገሩኝ፤ ሕግ የሚለውን አትሰሙምን? 22 በቅዱሳት መጻሕፍት “አብርሃም ሁለት ልጆች ነበሩት፤ አንደኛው የተወለደው ከአገልጋይቱ ሴት ሲሆን ሌላው የተወለደው ከነጻይቱ ሴት ነበር” ተብሎ ተጽፎአል። 23 የአገልጋይቱ ልጅ የተወለደው በሥጋዊ ልማድ ሲሆን የነፃይቱ ልጅ የተወለደው ግን በተሰጠው ተስፋው ቃል መሠረት ነበር። 24 ይህም ምሳሌ ነበር፤ እነዚህ ሁለት ሴቶች የሁለት ኪዳኖች ምሳሌ ነበሩ፤ ከሲና ተራራ የሆነችው የአንደኛዋ ምሳሌ አጋር ናት፤ እርስዋ ልጆችን የምትወልደው ለባርነት ነበር። 25 አጋር በዐረብ አገር ለሚገኘው ለሲና ተራራ ምሳሌ ነበረች፤ ስለዚህ ከአሁኒቱ ኢየሩሳሌም ጋር ትመሳሰላለች፤ እርስዋ ከነልጆችዋ በባርነት የምትገኝ ናት። 26 ከላይ ከሰማይ የሆነችው ኢየሩሳሌም ግን ነጻ ናት፤ እርስዋ የሁላችን እናት ናት። 27 “አንቺ ልጆች የማትወልጂ መኻን ደስ ይበልሽ! አንቺ ለመውለድ አምጠሽ የማታውቂ ‘እልል!’ በዪ፤ ባል ካላት ሴት ይልቅ ባል የሌላት ሴት ብዙ ልጆች አሉአት” ተብሎ ተጽፎአል። 28 ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንተም እንደ ይስሐቅ የተስፋው ቃል ልጆች ናችሁ። 29 ነገር ግን በዚያን ጊዜ በሥጋ የተወለደው በመንፈስ የተወለደውን እንዳሳደደው ዛሬም እንዲሁ ነው። 30 ነገር ግን ቅዱስ መጽሐፍ የሚለው ምንድን ነው? ቅዱስ መጽሐፍ “አገልጋይቱ ሴት የወለደችው ልጅ ነጻይቱ ሴት ከወለደችው ልጅ ጋር አብሮ ስለማይወርስ አገልጋይቱን ከነልጅዋ ወዲያ አስወጣት” ይላል። 31 ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ፥ እኛ የነፃይቱ ልጆች ነን እንጂ የአገልጋይቱ ልጆች አይደለንም። |