ገላትያ 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየጳውሎስ ሐዋርያነት በሌሎች ሐዋርያት ዘንድ መታወቁ 1 ከዐሥራ አራት ዓመት በኋላ ከበርናባስ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሼ ሄድኩ፤ ቲቶንም ከእኔ ጋር ይዤው ሄጄ ነበር። 2 የሄድኩትም እግዚአብሔር በገለጠልኝ መሠረት ነው። ከዚህ በፊት የሠራሁትም ሆነ አሁን የምሠራው ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር በማለት ለአሕዛብ የምሰብከውን ወንጌል ታላላቅ ለሆኑት መሪዎች በግል አስታወቅኋቸው። 3 ከእኔ ጋር የነበረው ቲቶ ምንም እንኳ ግሪካዊ ቢሆን እንዲገረዝ አልተገደደም። 4 ነገር ግን በመካከላችን ሾልከው በስውር የገቡ አንዳንድ ሐሰተኞች ወንድሞች እንዲገረዝ ፈልገው ነበር፤ እነዚህ ሰዎች ለስለላ በመካከላችን ሠርገው የገቡት በኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን ነጻነት ነጥቀው ወደ ባሪያነት ሊመልሱን አስበው ነው። 5 እኛ ግን የወንጌል እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር በማለት ለጥቂት ጊዜ እንኳ አልተበገርንላቸውም። 6 እነዚህ መሪዎች መስለው የሚታዩት ግን እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ ስለማያዳላ ስለ እነርሱ የቀድሞ ማንነት ግድ የለኝም፤ እነዚህ መሪዎች የተባሉት እኔ በማበሥረው የምሥራች ቃል ላይ ምንም አዲስ ነገር አልጨመሩም። 7 እንዲያውም እግዚአብሔር ጴጥሮስን ለአይሁድ የምሥራቹን ቃል እንዲያበሥር በተላከው ዐይነት እኔንም የምሥራቹን ቃል ለአሕዛብ እንዳበሥር እንዳደረገኝ ተገነዘቡ፤ 8 ስለዚህ ጴጥሮስን የአይሁድ ሐዋርያ ሆኖ እንዲያገለግል ያደረገው አምላክ እኔንም የአሕዛብ ሐዋርያ ሆኜ እንዳገለግል አድርጎኛል። 9 እንደ ምሰሶ መስለው የሚታዩት መሪዎች ያዕቆብና ጴጥሮስ ዮሐንስም እግዚአብሔር በጸጋ ይህን ልዩ የአገልግሎት ዕድል እንደ ሰጠኝ በተረዱ ጊዜ ለእኔና ለበርናባስ የመተባበራቸው ምልክት የሆነውን ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ እኛ ወደ አሕዛብ እንድንሄድ እነርሱም ወደ አይሁድ እንዲሄዱ ተስማሙ። 10 ብቻ በመካከላቸው ያሉትን ድኾች እንድናስታውስ ዐደራ አሉን፤ ይህም እኔ በትጋት ያደረግኹት ነገር ነው። ጳውሎስ በአንጾኪያ ጴጥሮስን እንደ ተቃወመው 11 ጴጥሮስ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ በግልጥ ተሳስቶ ስለ ነበር ፊት ለፊት ተቃወምኩት፤ 12 ያዕቆብ የላካቸው አንዳንድ ሰዎች ወደ አንጾኪያ ከመምጣታቸው በፊት ከአሕዛብ መካከል ከአመኑት ጋር አብሮ ይበላ ነበር፤ እነርሱ ከመጡ በኋላ ግን “ከአሕዛብ ወገን ያመኑት መገረዝ አለባቸው” የሚሉትን ቡድኖች በመፍራት ወደ ኋላ አፈግፍጎ ከአሕዛብ ተለየ። 13 አንዳንድ ከአይሁድ ወገን የሆኑ ክርስቲያኖችም የጴጥሮስን ግብዝነት ተከተሉ፤ በርናባስ እንኳ ሳይቀር በግብዝነታቸው ተስቦ ነበር። 14 የእነርሱ አድራጎት ከወንጌል እውነት ጋር አለመስማማቱን ባየሁ ጊዜ ጴጥሮስን “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ ሳለ በአይሁድ ሥርዓት ሳይሆን በአሕዛብ ሥርዓት ትኖር ነበር። ታዲያ፥ አሕዛብ በአይሁድ ሥርዓት እንዲኖሩ ለምን ታስገድዳቸዋለህ?” ስል በሁሉም ፊት ተቃወምኩት። አይሁድም ሆኑ አሕዛብ የሚድኑት በእምነት መሆኑ 15 በእርግጥ እኛ በትውልዳችን አይሁድ ነን፤ እንደ ኃጢአተኞች አሕዛብም አይደለንም። 16 ነገር ግን ሰው የሚጸድቀው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ ሕግን በመፈጸም እንዳልሆነ እናውቃለን፤ እኛም ሕግን በመፈጸም ሳይሆን በክርስቶስ በማመን እንድንጸድቅ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነናል፤ ማንም ሰው የኦሪትን ሕግ በመፈጸም አይጸድቅም። 17 በክርስቶስ በማመን ለመጽደቅ ስንፈልግ እኛ ራሳችን ኃጢአተኞች ሆነን ብንገኝ ታዲያ፥ ኃጢአት እንድንሠራ የሚያደርገን ክርስቶስ ነው ማለት ነውን? ከቶ አይደለም! 18 እኔ ራሴ ያፈረስኩትን የሕግ ሥርዓት መልሼ የምሠራው ከሆንኩ እኔው ራሴ ሕግ አፍራሽ መሆኔን አረጋግጣለሁ ማለት ነው። 19 ለእግዚአብሔር እኖር ዘንድ በሕግ አማካይነት በሞት የመለየትን ያኽል ከሕግ ተለይቼአለሁ። 20 እኔ ከክርስቶስ ጋር እንደ ተሰቀልኩ ያኽል ስለምቈጥር ከእንግዲህ ወዲህ ክርስቶስ በእኔ ውስጥ ይኖራል እንጂ እኔ ለራሴ ሕይወት የምኖር አይደለሁም፤ አሁንም በሥጋዊ አካሌ የምኖረው በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ በማመን በተገኘው ሕይወት ነው። 21 የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ አላስቀርም፤ ሰው የሚጸድቀው ሕግን በመፈጸም ከሆነ ክርስቶስ የሞተው በከንቱ ነው ማለት ነው። |