ዕዝራ 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምዕዝራ ከአይሁድ ዘር ውጪ የተደረገ ጋብቻ መኖሩን መገንዘቡ 1 ይህም ሁሉ ከተፈጸመ በኋላ ከእስራኤል ሕዝብ መሪዎች አንዳንዶቹ ወደ እኔ ቀርበው ከዚህ የሚከተለውን ቃል ነገሩኝ፦ “ሕዝቡና ካህናቱ ሌዋውያኑም ጭምር በጐረቤት ባሉት በዐሞን፥ በሞአብና በግብጽ ከሚኖሩትና እንዲሁም ከከነዓናውያን፥ ከሒታውያን፥ ከፈሪዛውያን፥ ከኢያቡሳውያንና ከአሞራውያን ርኲሰት ራሳቸውን አልጠበቁም፤ እነዚያ አሕዛብ ሲፈጽሙት የነበረውን አጸያፊ ነገር ሁሉ አድርገዋል። 2 ለራሳቸውና ለልጆቻቸው ሚስቶች የሚሆኑ ከእነዚያ ወገኖች አግብተዋል፤ አጋብተዋልም፤ ቅዱሱን ዘር ከሌሎች ከአካባቢው አሕዛብ ጋር ቀላቅለዋል፤ በዚህ እምነተ ቢስ በሆነ ተግባር መሪዎቹና ባለ ሥልጣኖቹ ግንባር ቀደም ሆነዋል።” 3 እኔም ይህን በሰማሁ ጊዜ በሐዘን መጐናጸፊያዬንና ካባዬን ቀደድሁ፤ የራስ ጠጒሬንና ጢሜን በመንጨት በብርቱ ሐዘን ላይ ሆኜ ተቀመጥሁ፤ 4 የሠርክ መሥዋዕት እስከሚቀርብበትም ጊዜ ድረስ በድንጋጤና በሐዘን ቈየሁ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ከምርኮ የተመለሱት ሰዎች ስለ ሠሩት ኃጢአት በተናገረው ቃል ከመፍራት የተነሣ ድንጋጤ አድሮባቸው የነበሩትም ሁሉ በዙሪያዬ ተሰበሰቡ። 5 የምሽትም መሥዋዕት የሚቀርብበት ሰዓት በደረሰ ጊዜ በሐዘን ከተቀመጥኩበት ስፍራ ተነሣሁ፤ የቀደድኩትን ልብስ እንደ ለበስኩ፥ በጒልበቴም በመንበርከክ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እጆቼን ዘርግቼ እንዲህ ስል ጸለይኩ፦ 6 “አምላኬ ሆይ፥ ኃጢአታችን ከራሳችን በላይ ስለ ሆነና በደላችንም ወደ ሰማይ ስለ ደረሰ ፊቴን ወደ አምላኬ ወደ አንተ ለማቅናት ዐፍራለሁ እፈራለሁም። 7 ከቀድሞ አባቶቻችን ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ እኛ ታላቅ በደል ሠርተናል፤ ከኃጢአታችንም ብዛት የተነሣ እኛ፥ ነገሥታቶችንና ካህናታችን በባዕዳን ነገሥታት እጅ ወድቀናል፤ ስለዚህም ለሰይፍ ተዳረግን፤ ሀብታችንንም ተዘረፍን፤ በመታሰር ተማርከን ተወሰድን፤ እነሆ፥ አሁንም እንዳለንበት ሁኔታ እስከ መጨረሻ ተዋርደናል። 8 አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፥ ዐይናችንን አበራህ፤ እነሆ፥ አሁን ደግሞ ለጥቂት ጊዜ በፊትህ ሞገስን አግኝተን ከእኛ ጥቂቶቹ ከባርነት ቀንበር ነጻ ወጥተው በዚህች ቅድስት ምድር በሰላም ይኖሩ ዘንድ ፈቅደሃል፤ ምንም እንኳ በባርነት አገዛዝ ሥር ብንወድቅም እነሆ አዲስ ሕይወት ሰጥተኸናል። 9 እኛ ባርያዎች ነበርን፤ አንተ ግን ባርያዎች ሆነን እንድንቀር አልተውከንም፤ አንተ የፋርስ ነገሥታት እንዲራሩልንና በሕይወት ነጻ ወጥተን ቀደም ሲል ፈርሶ የነበረውን ቤተ መቅደስህን እንደገና መልሰን እንድንሠራ፥ እዚህም በይሁዳና በኢየሩሳሌም በሰላም እንድንኖር ፈቀድክልን። 10 “ነገር ግን አምላካችን ሆይ! እስከ አሁን ስለ ሆነው ነገር ሁሉ ምን ማለት እንችላለን? እነሆ፥ አሁንም እንደገና ትእዛዞችህ አላከበርንም፤ 11 እነዚህም ትእዛዞች በአገልጋዮችህ በነቢያት አማካይነት የተሰጡ ነበሩ፤ ነቢያት አስቀድመው ‘የምትወርሱአት ምድር ከርኲሰት ሁሉ የነጻች አይደለችም፤ የሚኖሩባት ሕዝቦች ዳር እስከ ዳር በአጸያፊ ተግባር ሁሉ እንድትሞላ አድርገዋታል። 12 ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁን በጋብቻ ለእነርሱ ወንዶች ልጆች አትስጡ፤ እናንተም ለወንዶች ልጆቻችሁ የእነርሱን ሴቶች ልጆች በጋብቻ አትውሰዱ፤ በማንኛውም ጊዜ ከምድሩ መልካም ነገር በልታችሁ ለልጆቻችሁ ዘላቂ ርስት አድርጋችሁ ለማስተላለፍ እንድትችሉ በማንኛውም ጊዜ ከእነርሱ ጋር የወዳጅነት ስምምነት አታድርጉ’ ሲሉ ነግረውን ነበር። 13 የደረሰብን ችግር የክፉ ሥራችንና የበደላችን ውጤት ነው፤ ሆኖም አምላካችን የቀጣኸን ልንቀጣ ከሚገባን ያነሰ ነው፤ ከዚህም በላይ ከሞት አምልጠን በሕይወት አትርፈኸናል። 14 ታዲያ እንዴት እንደገና የአንተን ትእዛዞች ጥሰን ከእነዚህ ዐመፀኞች ሕዝቦች ጋር ጋብቻ እንፈጽማለን? በዚህስ ምክንያት ምንም ቅሬታ ሳታስቀርልን እኛን በቊጣህ አታጠፋንምን? 15 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ እውነተኛ ፈራጅ ነህ፤ ነገር ግን ከጥፋት አምልጠን በሕይወት እንድንኖር ፈቀድክልን፤ እነሆ እኛ፥ በደላችንን ተሸክመን በፊትህ ለመቅረብ የተገባን አይደለንም።” |