ዕዝራ 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምከዕዝራ ጋር ከስደት የተመለሰው ሕዝብ 1 በንጉሡ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት ከእኔ ጋር ከባቢሎን የተመለሱት የቤተሰብ አለቆች በየትውልዳቸው እንደሚከተለው ነው፦ 2-14 ከፊንሐስ ጐሣ ጌርሾም፥ ከኢታማር ጐሣ ዳንኤል፥ ከዳዊት ጐሣ የሸካንያ ልጅ ሐጡሽ፥ ከፓርዖሽ ጐሣ ዘካርያስ ሲሆን፥ ከእርሱ ቤተሰብ ወገን የሆኑ አንድ መቶ ኀምሳ ወንዶች ተመዝግበዋል፤ ከፓሐትሞአብ ጐሣ የዘራሕያ ልጅ ኤልየሆዔናይ ከሁለት መቶ ወንዶች ጋር፥ ከዛቱ ጐሣ የያሐዚኤል ልጅ ሸካንያ ከሦስት መቶ ወንዶች ጋር፥ ከዓዲን ጐሣ የዮናታን ልጅ ዔቤድ ከኀምሳ ወንዶች ጋር፥ ከዔላም ጐሣ የዐታልያ ልጅ የሻዕያ ከሰባ ወንዶች ጋር፥ ከሸፋጥያ ጐሣ የሚካኤል ልጅ ዘባድያ ከሰማንያ ወንዶች ጋር፥ ከኢዮአብ ጐሣ የየሒኤል ልጅ አብድዩ ከሁለት መቶ ዐሥራ ስምንት ወንዶች ጋር፥ ከባኒ ጐሣ የዮሲፍያ ልጅ ሸሎሚት ከአንድ መቶ ሥልሳ ወንዶች ጋር፥ ከቤባይ ጐሣ የቤባይ ልጅ ዘካርያስ ከኻያ ስምንት ወንዶች ጋር፥ ከዓዝጋድ ጐሣ የሃቃጣን ልጅ ዮሐናን ከአንድ መቶ ዐሥር ወንዶች ጋር፥ ከአዶኒቃም ጐሣ ኤሊፌሌጥ፥ ይዒኤልና ሸማዕያ ከስድሳ ወንዶች ጋር፥ እነርሱም ዘግየት ብለው ተመልሰዋል፤ ከቢግዋይ ጐሣ ዑታይና ዛኩር ከሰባ ወንዶች ጋር። ዕዝራ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች የሚሆኑ ሌዋውያንን ማግኘቱ 15 እኔ ዕዝራ ወደ አሀዋ በሚፈሰው ወንዝ አጠገብ መላውን ጉባኤ ሰበሰብኩ፤ በዚያም ሰፍረን ለሦስት ቀኖች ቈየን፤ በዚያም ጉባኤ ውስጥ ከካህናት በቀር ሌዋውያን አለመኖራቸውን ተገነዘብኩ፤ 16 ስለዚህም ኤሊዔዘር፥ አሪኤል፥ ሸማዕያ፥ ኤልናታን፥ ያሪብ፥ ኤልናታን፥ ናታን፥ ዘካርያስና መሹላም ተብለው ወደሚጠሩ ዘጠኝ መሪዎች፥ እንዲሁም ዮያሪብና ኤልናታን ተብለው ወደሚጠሩ ሁለት መምህራን ላክሁባቸው፤ 17 እነርሱንም በካሲፍያ ለሚኖር ሕዝብ መሪ ወደ ሆነው ወደ ኢዶ በመላክ ኢዶና የቤተ መቅደስ ሠራተኞች የሆኑት ረዳቶቹ በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ሰዎችን ይልኩልን ዘንድ እንዲነግሩአቸው አደረግሁ። 18 የእግዚአብሔር ታላቅ ኀይል ከእኛ ጋር ስለ ነበረ እነርሱ በቂ ችሎታ ያለውን፥ የማሕሊ ጐሣ የሆነውን ሼሬብያ ተብሎ የሚጠራውን ሌዋዊ ላኩልን፤ እርሱም ዐሥራ ስምንቱን ወንዶች ልጆቹንና ወንድሞቹን አስከትሎ ወደ እኛ መጣ። 19 እንዲሁም ከመራሪ ጐሣ የሆኑትን ሐሻብያና የሻዕያ ተብለው የሚጠሩትን ሰዎች ቊጥራቸው ኻያ ከሆነ ዘመዶቻቸው ጋር ላኩልን። 20 በተጨማሪም የቀድሞ አባቶቻቸው ሌዋውያንን ይረዱ ዘንድ በንጉሥ ዳዊትና በባለሟሎቹ ተሹመው የነበሩ ብዛታቸው ሁለት መቶ ኻያ የሆነ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ነበሩ፤ እነርሱም በየስማቸው ተመዝግበዋል። ሕዝቡ ጾምና ጸሎት እንዲያደርግ ዕዝራ ማዘዙ 21 እግዚአብሔር ጒዞአችንን እንዲያቃናልን፥ እኛንና ልጆቻችንን፥ እንዲሁም ንብረታችንን ሁሉ እንዲጠብቅልን በእርሱ ፊት ራሳችንን ዝቅ አድርገን እንለምነው ዘንድ በዚያው በአሀዋ ወንዝ አጠገብ ጾም ዐወጅኩ። 22 ከዚህ በፊት ለንጉሠ ነገሥት አርጤክስስ ባስረዳሁት ጊዜ “አምላካችን እግዚአብሔር በእርሱ የሚታመኑትን ሁሉ ይባርካል፤ እርሱን የሚተዉትን ግን በብርቱ ይቀጣቸዋል” በማለት ገልጬለት ስለ ነበረ በመንገድ ከሚገጥሙን ጠላቶቻችን እንዲጠብቁን ወታደሮችንና ፈረሰኞችን ይሰጠን ዘንድ ንጉሡን ጠይቄው ቢሆን ኖሮ ባፈርኩ ነበር። 23 ስለዚህም እግዚአብሔር ራሱ እንዲጠብቀን በጾምና በጸሎት ተማጠንነው፤ እርሱም ጸሎታችንን ሰማ። ለቤተ መቅደስ የቀረበ ስጦታ 24 መሪዎች ከሆኑት ካህናት መካከል ሼሬብያን፥ ሐሻብያንና ሌሎችንም ዐሥር ሰዎች መረጥሁ፤ 25 ከዚህ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ፥ አማካሪዎቹ፥ ባለሟሎቹና በዚያ የተገኙት እስራኤላውያን ለቤተ መቅደስ መገልገያ ይሆን ዘንድ የሰጡትን ብር፥ ወርቅና ሌሎቹንም ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ በሚዛን መዝኜ ለእነዚህ ካህናት አስረከብኳቸው። 26-27 ያስረከብኳቸውም የቤተ መቅደስ ንብረት ከዚህ የሚከተለው ነው፦ 22000 ኪሎ የሚመዝን ብር፥ 70 ኪሎ የሚመዝኑ አንድ መቶ ከብር የተሠሩ ዕቃዎች፥ 3400 ኪሎ የሚመዝን ወርቅ፥ 8 ኪሎ ከ 400 ግራም የሚመዝኑ ኻያ ከወርቅ የተሠሩ ወጭቶች፥ ከወርቅ ከተሠሩት ወጭቶች ጋር እኩል ዋጋ ያላቸው ከንጹሕ ነሐስ የተሠሩ ሁለት ወጭቶች። 28 እኔም እንዲህ አልኳቸው፦ “እነሆ እናንተ ለቀድሞ አባቶቻችን አምላክ ለእግዚአብሔር የተለያችሁ ናችሁ፤ እንዲሁም የበጎ ፈቃድ ስጦታ ሆነው የቀረቡት ከብርና ከወርቅ የተሠሩት ዕቃዎች ሁሉ ለቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ ለእግዚአብሔር የበጎ ፈቃድ መባ ናቸው። 29 ወደ ቤተ መቅደስ መግባት እስኪችሉ ድረስ በጥንቃቄ ጠብቁአቸው፤ እዚያም ለካህናቱ በተመደበው ክፍል ውስጥ እነዚህን ሁሉ ንዋያተ ቅድሳት መዝናችሁ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ መሪዎች እንዲሁም በኢየሩሳሌም ለሚገኙት የሕዝቡ መሪዎች አስረክቡአቸው።” 30 ስለዚህም ካህናቱና ሌዋውያኑ ብሩንና ወርቁን፥ ጠቅላላውንም ንዋያተ ቅድሳት ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ለመውሰድ ኀላፊነትን ተረከቡ። የሕዝቡ ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ 31 ከአሀዋ ወንዝ ተነሥተን ወደ ኢየሩሳሌም ጒዞ የጀመርነውም የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ነበር፤ በምንጓዝበትም ጊዜ አምላካችን ከእኛ ጋር ስለ ነበር ከጠላት አደጋና ከደፈጣ ተዋጊዎች ሽመቃ ጠበቀን። 32 ኢየሩሳሌም በደረስንም ጊዜ በዚያ የሦስት ቀኖች ዕረፍት አደረግን፤ 33 ከዚህም በኋላ በአራተኛው ቀን ወደ ቤተ መቅደስ ሄድን፤ ብሩን፥ ወርቁንና ንዋያተ ቅድሳቱንም ሁሉ መዝነን ለኡሪያ ልጅ ለካህኑ ለመሬሞት አስረከብነው፤ የፊንሐስ ልጅ አልዓዛርና እንዲሁም ሌዋውያኑ ዮዛባድ ተብሎ የሚጠራው የኢያሱ ልጅና ኖዓዲያ ተብሎ የሚጠራው የቢኑይ ልጅ ከእርሱ ጋር አብረው ነበሩ። 34 ሁሉም ነገር በዚያኑ ሰዓት ተቈጥሮና ተመዝኖ በትክክል ተመዘገበ። 35 ከዚያም ቀጥሎ እነዚያ ከምርኮ የተመለሱት ሰዎች ሁሉ ለእስራኤል አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርበውን መባ ሁሉ አመጡ፤ በዚህ ዐይነት በመላው እስራኤል ሕዝብ ስም ዐሥራ ሁለት ኰርማዎችን፥ ዘጠና ስድስት የበግ አውራዎችንና ሰባ ሰባት የበግ ጠቦቶችን አቀረቡ፤ እንዲሁም ስለ ኃጢአታቸው ስርየት ዐሥራ ሁለት አውራ ፍየሎችን አቀረቡ፤ እነዚህ ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነበሩ። 36 ንጉሠ ነገሥቱ የሰጣቸውንም ሰነድ በኤፍራጥስ ምዕራባዊ ክፍል ላሉት ገዢዎችና ባለሥልጣኖች ሰጡ፤ እነርሱም ሕዝቡንና የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ በማገዝ ድጋፋቸውን ሰጡ። |