Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዕዝራ 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የዕዝራ ወደ ኢየሩሳሌም መምጣት

1 ከብዙ ጊዜ በኋላ አርጤክስስ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት በሆነበት ዘመን፥ ዕዝራ ተብሎ የሚጠራ አንድ ሰው በዚያ ይኖር ነበር፤ የእርሱም የቀድሞ አባቶች የትውልድ ሐረግ እስከ ታላቁ ሊቀ ካህናት አሮን ድረስ ሲቈጠር እንደሚከተለው ነው፦ ዕዝራ የሠራያ ልጅ ሲሆን፥ ሠራያ የዐዛርያ ልጅ፥ ዐዛርያ የሒልቂያ ልጅ፥ ሒልቂያ የሻሉም ልጅ፥

2 ሻሉም የሳዶቅ ልጅ፥ ሳዶቅ የአሒጡብ ልጅ፥ አሒጦብ የአማርያ ልጅ፥

3 አማርያ የዓዛርያ ልጅ፥ ዓዛርያ የመራዮት ልጅ፥ መራዮት የዘራሕያ ልጅ፥

4 ዘራሕያ የዑዚ ልጅ፥ ዑዚ የቡቂ ልጅ፥

5 ቡቂ የአቢሹዓ ልጅ፥ አቢሹዓ የፊንሐስ ልጅ፥ ፊንሐስ የአልዓዛር ልጅ፥ አልዓዛር የሊቀ ካህናቱ የአሮን ልጅ ነው።

6 ይህ ዕዝራ ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ እርሱም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሙሴ በሰጠው ሕግ ሊቅ ነበር፤ የእግዚአብሔር ኀይል ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ ንጉሡ የጠየቀውን ነገር ሁሉ ሰጠው።

7 እንዲሁም ንጉሥ አርጤክስስ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ከእስራኤል ልጆች መካከል ካህናት፥ ሌዋውያን፥ መዘምራን፥ በር ጠባቂዎችና የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ከዕዝራ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።

8 ዕዝራ ንጉሡ አርጤክስስ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ወደ ኢየሩሳሌም ደረሰ።

9 የእግዚአብሔር ታላቅ ኀይል በእርሱ ላይ ስለ ነበረ ከባቢሎን በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን ተነሥቶ ኢየሩሳሌም በአምስተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ደረሰ።

10 ዕዝራ መላ ሕይወቱን የእግዚአብሔርን ሕግ በማጥናትና በተግባር በመተርጐም፥ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ትእዛዞች፥ ሕጎችና ሥርዓቶች ለመላው የእስራኤል ሕዝብ በማስተማር ያውለው ነበር።


ንጉሠ ነገሥቱ አርጤክስስ ለዕዝራ የሰጠው የጽሑፍ ፈቃድ

11 እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጣቸውን ሕግና ትእዛዞች ሁሉ የሚያውቅ ሊቅ ለነበረው ለካህኑ ዕዝራ፥ ንጉሠ ነገሥት አርጤክስስ የሰጠው ደብዳቤ ከዚህ የሚከተለው ነው፦

12 “ከንጉሠ ነገሥት አርጤክስስ፥ የሰማይ አምላክ የእግዚአብሔርን ሕግ በማጥናት ረገድ ታላቅ ምሁር ለሆነው ለካህኑ ዕዝራ፦ ሰላም ላንተ ይሁን፤

13 “እኔ በማስተዳድረው የንጉሠ ነገሥት መንግሥት ግዛት ውስጥ የሚገኙና ከአንተ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ የሚፈልጉ እስራኤላውያን፥ ካህናትና ሌዋውያን ሁሉ እንዲመለሱ ፈቅጃለሁ፤

14 ከዚህም ጋር እኔ ራሴ ከሰባቱ አማካሪዎቼ ጋር በአንድነት ያስተላለፍነውን ውሳኔ ለአንተ የተሰጠው የአምላክህ ሕግ በተግባር መፈጸሙን እየተመለከትህ፥ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያለውን ሁኔታ እንድትመረምር ልኬሃለሁ።

15 በተጨማሪም በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ለተሠራለት ለእስራኤል አምላክ እኔና አማካሪዎቼ በበጎ ፈቃድ የሰጠነውን ብርና ወርቅ ይዘህ ሂድ።

16 ከዚህም ሁሉ ጋር አንተ ራስህ ከባቢሎን ምድር የሰበሰብከውን ወርቅና ብር፥ የእስራኤል ሕዝብና ካህናታቸውም ጭምር በኢየሩሳሌም በተሠራው የአምላካቸው ቤተ መቅደስ እንዲቀርብላቸው የሚፈልጉትን መባ ሁሉ ይዘህ ሂድ።

17 ይህም ገንዘብ በጥንቃቄ ሥራ ላይ እንዲውል አድርግ፤ ወይፈኖችን፥ የበግ አውራዎችንና ጠቦቶችን፥ ለመባ የሚሆነውን እህልና የወይን ጠጅ ጭምር በኢየሩሳሌም በተሠራው በአምላክህ ቤተ መቅደስ ውስጥ በሚገኘው መሠዊያ ላይ የሚቀርበውን መባ ሁሉ ግዛበት።

18 ከዚያ የሚተርፈውንም ብርና ወርቅ እንደ አምላካችሁ ፈቃድ አንተና ወገኖችህ ለምትፈልጉት ነገር እንዲውል አድርግ።

19 በአምላክህ ቤተ መቅደስ ውስጥ አገልግሎት እንዲከናወንባቸው የተሰጡህን ንዋያተ ቅድሳት በኢየሩሳሌም ለሚመለከው አምላክ አቅርብ።

20 ለቤተ መቅደሱ መገልገያ የሚያስፈልግህንም ሌላውን ነገር ሁሉ ከቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ልትወስድ ትችላለህ።

21 “እኔ ንጉሥ አርጤክስስ ከኤፍራጥስ ምዕራብ የምትገኙ በጅሮንዶች ሁሉ በሰማይ አምላክ ሕግ ምሁር የሆነው ካህኑ ዕዝራ የሚጠይቃችሁን ሁሉ ትሰጡት ዘንድ አዝዣለሁ።

22 እስከ ሦስት ሺህ አራት መቶ ኪሎ ያኽል የሚመዝን ብር፥ እስከ ዐሥር ሺህ ኪሎ ስንዴ፥ እስከ ሁለት ሺህ ሊትር የወይን ጠጅ፥ እስከ ሁለት ሺህ ሊትር የወይራ ዘይትና የሚያስፈልገውንም ያኽል ጨው ስጡት።

23 በንጉሡና በልጆቹ ላይ ቊጣ እንዳይመጣ የሰማይ አምላክ ለቤተ መቅደሱ የሚያዘው ሁሉ በጥንቃቄ መፈጸም አለበት።

24 እንዲሁም ከካህናት፥ ከሌዋውያን፥ ከመዘምራን፥ ከዘብ ጠባቂዎች፥ በአጠቃላይም ቤተ መቅደሱን የሚመለከት ማናቸውንም ሥራ ከሚያከናውኑት ወገኖች ሁሉ ላይ ቀረጥ፥ ግብርና ግዴታ የመጣል ሥልጣን የሌላችሁ መሆኑን እንድታውቁ።

25 “አንተም ዕዝራ፥ አምላክህ እግዚአብሔር በሰጠህ ጥበብና ዕውቀት እየተመራህ፥ በአምላክህ በእግዚአብሔር ሕግ የሚመሩትን፥ በኤፍራጥስ ማዶ የሚገኙትን ሰዎች የሚመሩ አስተዳዳሪዎችንና ዳኞችን ሹምላቸው፤ ለማያውቁትም ሁሉ የአምላክህን ሕግ አስተምራቸው፤

26 ለእግዚአብሔር ሕግ ወይም ለመንግሥት ሕግ ሁሉ የማይታዘዝ ማንም ሰው ቢኖር በጥንቃቄ እየተመረመረ በሞት ወይም ከሀገር በመባረር ወይም ሀብት ንብረቱን በመወረስ ወይም በእስራት ይቀጣ።”


ዕዝራ እግዚአብሔርን ማመስገኑ

27 ዕዝራ እንዲህ ሲል እግዚአብሔርን አመሰገነ፦ “የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን! በኢየሩሳሌም ለሚሠራው ለእግዚአብሔር ቤት ንጉሠ ነገሥቱ ክብር ለመስጠት እንዲፈቅድ ያደረገው እርሱ ነው፤

28 በእግዚአብሔርም ፈቃድ በንጉሠ ነገሥቱና በአማካሪዎቹ፥ በባለሥልጣኖቹም ሁሉ ዘንድ መወደድን አግኝቻለሁ፤ የአምላኬ የእግዚአብሔር ኀይል ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ከእስራኤል የጐሣ መሪዎች ብዙዎቹ ከእኔ ጋር ተባብረው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ በማግባባት ለማስተማር አብቅቶኛል።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios