Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዕዝራ 6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ቂሮስ የሰጠው ትእዛዝ ተፈልጎ መገኘቱ

1 በባቢሎን ቤተ መንግሥት የሚገኙ መዛግብት ሁሉ ይመረመሩ ዘንድ ንጉሠ ነገሥት ዳርዮስ ትእዛዝ አስተላለፈ፤

2 ነገር ግን በባቢሎን ከተማ ሳይሆን በሜዶን ክፍለ ሀገር በተለይ “አሕምታ” ተብላ በምትጠራው ከተማ ውስጥ አንድ የብራና ጥቅል ተገኘ፤ በውስጡም የተጻፈበት ቃል እንዲህ የሚል ነበር፦

3 “ቂሮስ ንጉሠ ነገሥት በሆነ በመጀመሪያው ዓመት በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ የሚቃጠለውና ሌላውም ልዩ ልዩ መሥዋዕት ይቀርብበት ዘንድ እንደገና እንዲሠራ በመፍቀድ ትእዛዝ ሰጥቶአል፤ የቤተ መቅደሱም ርዝመት ኻያ ሰባት ሜትር፥ ስፋቱም ኻያ ሰባት ሜትር መሆን አለበት።

4 ቅጽሮቹም ከድንጋይ በተሠሩት በሦስቱም ዙር ግንቦች አናት ላይ አንዳንድ ዙር ከእንጨት የተሠራ ድምድማት ይኑራቸው፤ ለዚህም ሁሉ ሥራ የሚያስፈልገው ገንዘብ ከቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ወጪ ሆኖ ይሰጥ።

5 እንዲሁም ከዚህ በፊት ንጉሥ ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ ማርኮ ያወጣቸው ከወርቅና ከብር የተሠሩትም ንዋያተ ቅድሳት ወደዚያው ተመልሰው በኢየሩሳሌም በሚሠራው ቤተ መቅደስ በተገቢ ቦታቸው ይቀመጡ።”


የቤተ መቅደሱ ሥራ እንዲቀጥል ዳርዮስ ትእዛዝ መስጠቱ

6 ከዚህ በኋላ ዳርዮስ የሚከተለውን መልእክት አስተላለፈ፦ “የኤፍራጥስ ምዕራባዊ ክፍል ገዢ ለሆንከው ለታተናይ፥ ለሸታርቦዝናይና በኤፍራጥስ ምዕራብ ለሚገኙ ተባባሪዎቻችሁ ሁሉ፦ ከቤተ መቅደሱ ራቁ፤

7 ሥራውን ከማደናቀፍ ተቈጠቡ፤ የይሁዳ ክፍለ ሀገር ገዢና የአይሁድ መሪዎች ቀድሞ በነበረበት ስፍራ ላይ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መልሰው ይሥሩ።

8 በዚሁ አጋጣሚ ይልቁንም የቤተ መቅደሱን ሥራ እንድታግዙአቸው አዝዣችኋለሁ። ስለዚህም አስፈላጊው የማሠሪያ ገንዘብ ሁሉ ከኤፍራጥስ ምዕራባዊ ክፍል ከተሰበሰበው የመንግሥት ግብር ሳይዘገይ ወጪ እየሆነ ይሰጣቸው፤ ሥራውም መሰናከል አይገባውም።

9 ከዚህም ሁሉ ጋር በኢየሩሳሌም የሚገኙት ካህናት በሚነግሩአችሁ መሠረት በየዕለቱ በሰማይ ለሚኖረው አምላክ ለሚያቀርቡት መሥዋዕት የሚፈልጓቸውን ኰርማዎች፥ በጎችን ወይም ጠቦቶችን፥ እንዲሁም ለመባ የሚሆነውን ስንዴ፥ ጨው፥ የወይን ጠጅና የወይራ ዘይት ሁሉ ስጡአቸው።

10 ይህም ሁሉ የሚሆንበት ምክንያት የሰማይ አምላክ በደስታ የሚቀበለውን መሥዋዕት ሁሉ በማቅረብ ለእኔና ለልጆቼ ሕይወት እንዲጸልዩልን ነው፤

11 ከዚህም ሌላ ማስታወቅ የምፈልገው ነገር ይህን መመሪያ የማይቀበልና የማይታዘዝ ማንም ሰው ቢኖር ከቤቱ የእንጨት ምሰሶዎች አንዱ ተነቅሎ በአንዱ ጫፍ በኩል እንዲሾል ከተደረገ በኋላ በሰውነቱ ላይ ይሰካበት፤ ቤቱም ፈራርሶ የጉድፍ መጣያ ይሁን።

12 ይህን ትእዛዝ ባለመቀበል በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማፍረስ የሚሞክረውን ማንኛውንም ንጉሥ ወይም ሕዝብ የስሙ መጠሪያ ይሆን ዘንድ የመረጠ አምላክ ያስወግደው፤ ይህን ትእዛዝ ያስተላለፍኩ እኔ ዳርዮስ ስለ ሆንኩ በሙሉ መፈጸም አለበት።”


የቤተ መቅደሱ የምረቃ በዓል

13 ከዚህ በኋላ አገረ ገዢው ታተናይ፥ ሸታርቦዝናይና የእነርሱም ተባባሪዎች የሆኑ ባለሥልጣኖች ንጉሠ ነገሥቱ እንዳዘዛቸው ሁሉንም ነገር ፈጸሙ።

14 የአይሁድ መሪዎች፥ ነቢያቱ ሐጌና ዘካርያስ እያበረታቱአቸው የቤተ መቅደሱን ሥራ አፋጠኑት፤ በእስራኤል አምላክ ፈቃድ የፋርስ ነገሥታት ቂሮስ፥ ዳርዮስና አርጤክስስ ባዘዙትም መሠረት የቤተ መቅደሱን ሥራ ፈጸሙ፤

15 የቤተ መቅደሱን ሥራ የፈጸሙትም ዳርዮስ ንጉሠ ነገሥት በሆነ በስድስተኛው ዓመት አዳር ተብሎ የሚጠራው ወር በገባ በሦስተኛው ቀን ነበር።

16 ከዚህም ቀጥሎ የእስራኤል ሕዝብ፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ፥ እንዲሁም ከምርኮ የተመለሱት ሌሎችም ሰዎች ሁሉ፥ የቤተ መቅደሱን ምረቃ በዓል በደስታ አከበሩ።

17 እነርሱም ሁሉ ለበዓሉ የሚሆኑትን አንድ መቶ ወይፈኖችን፥ ሁለት መቶ በጎችንና አራት መቶ ጠቦቶችን ለመሥዋዕት አቀረቡ፤ ለኃጢአት ስርየት መሥዋዕት የሚሆኑም ዐሥራ ሁለት ፍየሎችን በእያንዳንዱ ነገድ ስም አቀረቡ።

18 በሙሴ መጽሐፍ በተጻፈውም መመሪያ መሠረት በኢየሩሳሌም ለተሠራው ቤተ መቅደስ አገልግሎት፥ ካህናቱን በየክፍላቸው፥ ሌዋውያኑን በየቡድናቸው አደራጁ።


የፋሲካ በዓል

19 ከምርኮ የተመለሱት ሰዎች የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል አከበሩ።

20 ካህናቱና ሌዋውያኑም ሁሉ በሥርዓቱ መሠረት ራሳቸውን አነጹ፤ ሌዋውያኑም በፋሲካው በዓል አከባበር ላይ ከምርኮ ለተመለሱት ሕዝብና ለካህናቱ፥ እንዲሁም ለራሳቸው የቀረቡትን እንስሶች ዐረዱ።

21 መሥዋዕቱንም ሁሉ ከምርኮ የተመለሱት እስራኤላውያን እንዲሁም በዚያች ምድር የሚኖሩትን የአሕዛብን ሥርዓት ትተው የነበረውን ልማድ ትተው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሁሉ እንዲመገቡት ተደረገ።

22 እግዚአብሔር ራሱ በአሦር ንጉሠ ነገሥት ዘንድ መወደድን አግኝተው የእስራኤል አምላክ የሚመሰገንበትን ቤተ መቅደስ እንደገና መሥራት ይችሉ ዘንድ በሥራቸው ሁሉ እንዲረዳቸው ስላደረገላቸው የቂጣን በዓል ሰባት ቀን ሙሉ በታላቅ ደስታ አከበሩ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios