Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዕዝራ 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የቤተ መቅደሱ ሥራ እንደገና መቀጠሉ

1 በዚያን ጊዜ ሁለቱ ነቢያት፥ ሐጌና የዒዶ ልጅ ዘካርያስ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምድር ለሚኖሩ አይሁድ፥ ስለ ቤተ መቅደሱ ሥራ ጉዳይ በእስራኤል አምላክ ስም ትንቢት ተናገሩላቸው።

2 የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የኢዮጼዴቅ ልጅ ኢያሱም የነዚህን ነቢያት የትንቢት ቃል በሰሙ ጊዜ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ መሥራታቸውን እንደገና ቀጠሉ፤ ሁለቱ ነቢያትም ይረዱአቸው ነበር።

3 በዚያን ጊዜ የኤፍራጥስ ምዕራባዊ ክፍል ገዢ የነበረው ታተናይና ሽታርቦዝናይ እንዲሁም ተባባሪዎቻቸው የሆኑ ባለሥልጣኖች ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፦ “ይህን ቤተ መቅደስ ለመሥራትና ቅጽሩንም ለማደስ ማን ፈቀደላችሁ?” ሲሉ ጠየቁአቸው።

4 ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የተባበሩአቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር ለማወቅም ጠየቁ።

5 ነገር ግን የአይሁድ መሪዎችን እግዚአብሔር ይጠብቃቸው ስለ ነበር ለፋርስ ባለ ሥልጣኖች ለዳርዮስ መልእክት ጽፈው መልስ እስከሚያገኙ ድረስ ሥራውን ከመቀጠል አልከለከሉአቸውም።

6 የኤፍራጥስ ምዕራባዊ ክፍል ገዢ የነበረው ታተናይና ሽታርቦዝናይ እንዲሁም ተባባሪዎቻቸው የሆኑ ለንጉሥ ዳርዮስ የጻፉት ደብዳቤ የሚከተለው ነው፦

7 “ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ዳርዮስ! ግዛትዎ ሰላም ይሁን፤

8 ወደ ይሁዳ ምድር ሄደን የታላቁ አምላክ ቤተ መቅደስ በድንጋይና በጠርብ እንጨት ሲሠራ ማየታችን ለግርማዊነትዎ የታወቀ ይሁን፤ ሥራውም በሽማግሌዎቹ መሪነት በጥንቃቄና በፍጥነት እየተሠራ ነው።

9 “እኛም የሕዝቡን መሪዎች ‘ይህን ቤተ መቅደስ እንደገና መልሳችሁ ለመሥራትና ቅጽሮቹንም ለማደስ ማን ፈቀደላችሁ?’ ብለን ጠየቅናቸው፤

10 የዚህ ሥራ መሪዎችም እነማን እንደ ሆኑ እንገልጥልህ ዘንድ የስም ዝርዝራቸውን ጠይቀናል።

11 “እነርሱም እንዲህ ሲሉ አስረድተውናል፤ ‘እኛ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የታላቁ እግዚአብሔር አገልጋዮች ነን፤ ስለዚህም ለእርሱ ከብዙ ዘመን በፊት በአንድ ታላቅ የእስራኤል ንጉሥ ተሠርቶለት የነበረውን ቤተ መቅደስና ቅጽር እንደገና መልሰን በመሥራት ላይ እንገኛለን፤

12 ነገር ግን የቀድሞ አባቶቻችን ይህን የሰማይ አምላክ በማስቈጣታቸው ምክንያት በከለዳውያን ሥርወ መንግሥት የባቢሎን ንጉሠ ነገሥት በሆነው በናቡከደነፆር ጦር እንዲሸነፉ አደረገ፤ ቤተ መቅደሱ ፈራረሰ፤ ሕዝቡም ተማርኮ ወደ ባቢሎን ተወሰደ።

13 ከዚህም በኋላ ቂሮስ የባቢሎን ንጉሠ ነገሥት በሆነ በመጀመሪያው ዓመት ይህን ቤተ መቅደስ መልሰን መሥራት እንድንችል በዐዋጅ የፈቀደልን ንጉሠ ነገሥቱ ቂሮስ ራሱ ነው።

14 ናቡከደነፆር በዚሁ በኢየሩሳሌም ተሠርቶ ከነበረው ከቀድሞው ቤተ መቅደስ ማርኮ የወሰዳቸውንና በባቢሎን ማምለኪያ ስፍራው ውስጥ ያኖራቸውን ከወርቅና ከብር የተሠሩ ንዋያተ ቅድሳትም ሁሉ ቂሮስ መልሶ አስረክቦናል፤ ንዋያተ ቅድሳቱንም ያስረከበን የይሁዳ ገዢ አድርጎ በሾመው ሼሽባጻር ተብሎ በሚጠራው ሰው አማካይነት ነው።

15 ይኸው አገረ ገዢው ሼሽባጻር እነዚህን ንዋያተ ቅድሳት መልሶ በማምጣት በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ ውስጥ ያኖር ዘንድ፥ እንዲሁም ቤተ መቅደሱ ቀድሞ በነበረበት ስፍራ ላይ ተመልሶ እንዲሠራ ያደርግ ዘንድ፥ ንጉሠ ነገሥቱ ቂሮስ አዞታል።

16 ስለዚህም ሼሽባጻር መጥቶ መሠረቱን ጣለ፤ ከዚያም በኋላ የሕንጻው ሥራ እንዲቀጥል ተደርጎ፥ ይኸው እስከ አሁን በመሠራት ላይ ነው፤ ነገር ግን የቤተ መቅደሱ ሕንጻ ገና አልተፈጸመም።’

17 “ንጉሥ ሆይ! እንግዲህ በእርግጥ ይህ ቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም ይሠራ ዘንድ ንጉሥ ቂሮስ የሰጠው ትእዛዝ መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ በባቢሎን ቤተ መንግሥት የጽሑፍ ማስረጃዎችን አስመርምረህ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ዐይነት ውሳኔ ቢሰጥ እንደምትፈቅድ ታስታውቀን ዘንድ እንለምናለን።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios