Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዕዝራ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ቤተ መቅደሱ እንደገና እንዳይሠራ የተደረገ ተቃውሞ

1 የይሁዳና የብንያም ሕዝብ ጠላቶች የሆኑ ነዋሪዎች ከምርኮ የተመለሱት ሰዎች ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመሥራት ላይ መሆናቸውን ሰሙ።

2 ወደ ዘሩባቤልና ወደ ጐሣ መሪዎችም ቀርበው “ቤተ መቅደሱን ከእናንተ ጋር አብረን እንሥራ፤ ይህንኑ እናንተ የምታመልኩትን እግዚአብሔር እኛም እናመልከዋለን፤ የአሦር ንጉሠ ነገሥት አስራዶን ወደዚህ አገር ከላከንም ጊዜ ጀምሮ መሥዋዕት ስናቀርብለት ቈይተናል” አሉአቸው።

3 ነገር ግን ዘሩባቤል፥ ኢያሱና የጐሣ መሪዎች ሁሉ እነዚህን ሰዎች፦ “ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ስለምንሠራው ቤተ መቅደስ የእናንተ ርዳታ አያስፈልገንም፤ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ቂሮስ ባዘዘን መሠረት እኛው ራሳችን እንሠራዋለን” ሲሉ መለሱላቸው።

4 ከዚህም በኋላ የምድሪቱ ነዋሪዎች የሆኑት ሕዝቦች አይሁድን በማስፈራራትና ተስፋ ለማስቈረጥ በመሞከር ቤተ መቅደሱን እንዳይሠሩ ሊከለክሉአቸው ተነሣሡ።

5 ለፋርስ መንግሥት ባለሥልጣኖች ጉቦ በመስጠትም በእነርሱ ላይ ተጽዕኖ ሊያደርጉባቸው ሞከሩ፤ ከቂሮስ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ዳርዮስ እስከ ተነሣበት ዘመን ድረስ ይህን ከማድረግ አልተቈጠቡም ነበር።


ኢየሩሳሌም እንደገና እንዳትሠራ የተደረገ ሌላ ተቃውሞ

6 ይልቁንም አርጤክስስ ንጉሠ ነገሥት በሆነበት ዘመን መጀመሪያ ላይ፥ ጠላቶቻቸው በይሁዳና በኢየሩሳሌም ይኖሩ በነበሩት እስራኤላውያን ላይ በጽሑፍ የተቀናበረ ክስ መሠረቱባቸው።

7 አርጤክስስ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ሆኖ በተነሣበትም ዘመን፥ እንደገና ቢሽላም፥ ሚትረዳት፥ ጣብኤልና ሌሎቹ የእነርሱ ግብረ አበሮች የክስ ደብዳቤ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ጻፉባቸው፤ ይህም ደብዳቤ የተጻፈው በሶርያ ፊደልና ቋንቋ ሲሆን ተተርጒሞ በንባብ እንዲሰማ የተላከ ነበር።

8 እንዲሁም አገረ ገዢው ረሑምና የአውራጃው ጸሐፊ ሺምሻይ፥ ስለ ኢየሩሳሌም ጉዳይ ከዚህ የሚከተለውን ደብዳቤ ወደ ንጉሥ አርጤክስስ ጻፉ፤

9 ከአገረገዢ ረሑምና ከአውራጃው ጸሐፊ ሺምሻይ፥ እንዲሁም ተባባሪዎቻቸው ከሆኑት ዳኞችና ቀድሞ በዔላም ምድር በኤሬክ፥ በባቢሎንና በሱሳ ይኖሩ ከነበሩት ሌሎችም ባለ ሥልጣኖች ሁሉ፥

10 ታላቁና ኀያሉ ንጉሠ ነገሥት አሰናፈር ከየተወለዱበት አገር በማዛወር በሰማርያ ከተማና ከኤፍራጥስ ምዕራባዊ ክፍል በየአውራጃው እንዲሰፍሩ ካደረጋቸው ከሌሎችም ሕዝቦች ጋር በመተባበር የተጻፈ ሲሆን።

11 የደብዳቤውም ፍሬ ነገር ይህ ነው፤ በኤፍራጥስ ምዕራባዊ ክፍል ከሚኖሩ አገልጋዮቹ ለንጉሠ ነገሥት አርጤክስስ የተላከ።

12 “ከግርማዊነትዎ ዘንድ የመጡት አይሁድ እዚህ ኢየሩሳሌም የደረሱ መሆናቸው በግርማዊነትዎ ዘንድ የታወቀ ይሁን። ያቺን ዐመፀኛና ክፉ ከተማ እንደገና በመሥራት ላይ ናቸው፤ ቅጽሮቹን በመጠገንና የቤተ መቅደስዋንም መሠረት በመጣል ላይ ናቸው።

13 ስለዚህም ንጉሥ ሆይ! ይህች ከተማ እንደገና ከተሠራችና የቅጽሮችዋም ሥራ ከተጠናቀቀ፥ ሕዝቡ ግብር መክፈላቸውን ያቆማሉ፤ ለግርማዊነትዎ የሚቀርበውም የንጉሣዊ ቤተ መንግሥት ገቢ ሊቀነስ የሚችል መሆኑን ይታወቅ፤

14 እኛም የቤተ መንግሥቱ ጥቅም ተካፋዮች በመሆናችን አለመከበርዎን እያየን ዝም ማለትን ስላልወደድን ይህን ሐሳብ እናቀርባለን፤

15 ስለዚህ የቀድሞ አባቶችዎ ታሪክ ያለባቸው መዛግብት እንዲመረመሩ ትእዛዝ ይሰጡ ዘንድ እናሳስባለን፤ ይህ በሚደረግበት ጊዜ ይህች ከተማ ዘወትር ዐመፀኛ እንደ ነበረችና ከጥንት ጀምሮ ለነገሥታትና በየክፍላተ ሀገሩ ለሚገኙ አገረ ገዢዎች ምን ያኽል አስቸጋሪ እንደ ነበረች ማስረጃ ያገኛሉ፤ ከጥንት ጀምሮ ሕዝቦችዋ ዐመፀኞች ነበሩ፤ ከዚህ በፊት ከተማይቱ እንድትደመሰስ የተደረገበትም ምክንያት ይኸው ነበር።

16 ከዚህም የተነሣ፥ ይህች ከተማ እንደገና ከተሠራችና የቅጽሮችዋም ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ ግርማዊነትዎ ከኤፍራጥስ ማዶ በሚገኙት ክፍላተ ሀገሮች ላይ ምንም ይዞታ እንደማይኖርዎ እንገልጻለን።”

17 ንጉሠ ነገሥቱም ለዚህ ደብዳቤ ከዚህ የሚከተለውን መልስ ላከ፦ “ለአገረ ገዢው ረሑም፥ ለአውራጃ ጸሐፊው ሺምሻይ፥ እንዲሁም በሰማርያና ከኤፍራጥስ በስተ ምዕራብ ለሚኖሩ ተባባሪዎችህ ሁሉ፥ ሰላም ለእናንተ ይሁን።

18 “የላካችሁልኝ ደብዳቤ ተተርጒሞ በንባብ ሰምቼዋለሁ፤

19 በእርሱም መነሻነት ጥብቅ ምርምርና ጥናት እንዲደረግ ትእዛዝ ሰጥቻለሁ፤ ከጥናቱም የተገኘው ውጤት ኢየሩሳሌም ከጥንት ጀምሮ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ስታምፅ የኖረች ዐመፀኞችና አስቸጋሪዎች ሰዎች የሞሉባት ከተማ እንደ ነበረች ያስረዳል፤

20 ይህም ሁሉ ሆኖ፥ ኢየሩሳሌም ከኤፍራጥስ በስተ ምዕራብ ያሉትን አገሮች ሁሉ በማስገበር ቀረጥና ግብር የሚያስከፍሉ ኀያላን ነገሥታት ነግሠውባት ነበር።

21 ስለዚህ እኔ ሌላ ትእዛዝ እስካስተላልፍ ድረስ እነዚያ ሰዎች ከተማይቱን እንደገና መሥራታቸውን ያቆሙ ዘንድ እዘዙ።

22 በመንግሥታችን ላይ ምንም ችግር እንዳይደርስ ኀላፊነታችሁን ቸል እንዳትሉ ተጠንቀቁ።”

23 ንጉሠ ነገሥቱ አርጤክስስ የላከው የመልስ ደብዳቤም መጥቶ ለረሑም፥ ለሺምሻይና ለተባባሪዎቻቸው ሁሉ እንደ ተነበበላቸው፥ ወዲያውኑ ወደ ኢየሩሳሌም ገሥግሠው በመምጣት ሕዝቡን በማስገደድ የኢየሩሳሌምን ከተማ እንደገና ከመሥራት አገዱአቸው፤

24 ስለዚህ ዳርዮስ በፋርስ እስከ ነገሠበት እስከ ሁለተኛው ዓመት ድረስ የቤተ መቅደሱ ሥራ በመቋረጡ በጅምር ቀርቶ ነበር።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios