Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዘፀአት 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ለ. ጓጒንቸር

1 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ፈርዖን ሄደህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገረው፤ ‘ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ፤

2 እምቢ ብትል ግን ሀገርህን ለመቅጣት በጓጒንቸር እሸፍናታለሁ።

3 የዐባይ ወንዝ በጓጒንቸሮች የተሞላ ስለሚሆን፥ ከዚያ እየወጡ ወደ ቤተ መንግሥትህ፥ ወደ መኝታ ቤትህ፥ ወደ አልጋህ፥ ወደ መኳንንትህና ወደ ሕዝብህ ቤቶች፥ እንዲሁም ወደ ምድጃህና ወደ ቡኾ ዕቃዎችህ ሳይቀር ይገባሉ፤

4 ጓጒንቸሮቹ በአንተና በሕዝብህ፥ በመኳንንትህም ሁሉ ላይ ይመጡባችኋል።’ ”

5 እግዚአብሔርም ሙሴን “ጓጒንቸሮች ወጥተው መላውን የግብጽ ምድር ይሸፍኑ ዘንድ በወንዞች፥ በመስኖ ቦዮችና በኲሬዎች ሁሉ ላይ በትሩን እንዲዘረጋ ለአሮን ንገረው” አለው።

6 ስለዚህም አሮን በግብጽ ውሃ ሁሉ ላይ በትሩን ዘረጋ፤ ጓጒንቸሮችም ወጥተው ምድሪቱን አለበሱአት።

7 ነገር ግን አስማተኞችም እንደዚሁ በአስማታቸው ተጠቅመው ጓጒንቸሮች በግብጽ ምድር ላይ እንዲመጡ አደረጉ።

8 ንጉሡም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ “ጓጒንቸሮቹን ከእኔና ከሕዝቤ ዘንድ እንዲያርቅ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልኝ፤ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ ሕዝባችሁን እለቃለሁ” አላቸው።

9 ሙሴም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “በደስታ እጸልይልሃለሁ፤ ለአንተና ለመኳንንትህ ለሕዝብህም የምጸልይበትን ሰዓት ብቻ ወስንልኝ፤ ከዚያም በኋላ ጓጒንቸሮቹ ከአንተና ከቤትህ ሁሉ ርቀው በዐባይ ወንዝ ብቻ ተወስነው እንዲኖሩ አደርጋለሁ” አለው።

10 ንጉሡም “እንግዲያውስ ነገውኑ ጸልይልኝ” አለ። ሙሴም እንዲህ አለ፤ “እንዳልከው አደርጋለሁ፤ አንተም እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር ያለ ሌላ አምላክ እንደሌለ በዚያን ጊዜ ታውቃለህ።

11 ጓጒንቸሮቹ ከአንተና ከቤትህ ሁሉ፥ ከመኳንንትህና ከሕዝብህም ሁሉ ዘንድ ይወገዳሉ፤ በዐባይ ወንዝ ውስጥ ካልሆነ በቀር፥ በሌላ ቦታ አይገኙም።”

12 ከዚህ በኋላ ሙሴና አሮን ከንጉሡ ፊት ወጥተው ሄዱ፤ በንጉሡ ላይ ያመጣቸውንም ጓጒንቸሮች ያስወግድለት ዘንድ ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።

13 ሙሴ በጸለየውም መሠረት እግዚአብሔር በየቤቱ፥ በየቅጽር ግቢውና በየመስኩ ያሉት ጓጒንቸሮች ሁሉ ሞቱ።

14 ጓጒንቸሮቹም ሁሉ በየስፍራው ተከመሩ፤ ምድሪቱም በግማት ተሞላች።

15 ንጉሡ ጓጒንቸሮቹ መሞታቸውን ባየ ጊዜ እግዚአብሔር እንዳለው ልቡን አደንድኖ አልሰማቸውም።


ሐ. ተናካሽ ትንኝ

16 እግዚአብሔር ሙሴን “የምድሩን ትቢያ በበትሩ እንዲመታ ለአሮን ንገረው፤ በግብጽም አገር ሁሉ ትቢያው ወደ ተናካሽ ትንኝነት ይለወጣል” አለው።

17 እንደተባሉትም አደረጉ፤ አሮንም እጁን ዘርግቶ በበትሩ የምድሩን ትቢያ መታ፤ በግብጽ አገር ያለውም ትቢያ ሁሉ ወደ ተናካሽ ትንኝነት ተለወጠ፤ ሰዎችንና እንስሶችንም ሁሉ ሸፈነ።

18 አስማተኞቹ በአስማታቸው ተጠቅመው ተናካሽ ትንኝ እንዲፈላ ለማድረግ ሞከሩ፤ ነገር ግን አልተሳካላቸውም፤ ተናካሽ ትንኝም በሰዎችና በእንስሶች ላይ ተሠራጨ።

19 አስማተኞቹም “ይህ የእግዚአብሔር ሥራ ነው!” ብለው ለንጉሡ ነገሩት፤ ንጉሡ ግን ልቡን አደነደነ፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረውም ሙሴንና አሮንን መስማት አልፈለገም።


መ. ተናካሽ ዝንብ

20 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ነገ ጠዋት በማለዳ ወደ ንጉሡ ሄደህ ወደ ወንዝ ሲወርድ አግኘው፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገረው፤ ‘ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ፤

21 እምቢ ብትል ግን በአንተ፥ በመኳንንትህና በሕዝብህ ቤቶች የዝንብ መንጋ እልካለሁ፤ የግብጻውያን ቤቶችና የቆሙበት ምድር በዝንብ መንጋ የተሞላ ይሆናል።

22 ነገር ግን በዚህ ምድር መካከል እኔ እግዚአብሔር መገኘቴን ታውቅ ዘንድ በዚያን ቀን ሕዝቤ የሚኖርባትን የጌሴምን ምድር ከዝንቦቹ መንጋ ነጻ አድርጌ እለያታለሁ።

23 በሕዝብህና በሕዝቤ መካከል ልዩነት እንዲኖር አደርጋለሁ፤ ይህም ተአምር በነገይቱ ዕለት ይፈጸማል።’ ”

24 እግዚአብሔርም የንጉሡ ቤተ መንግሥትና የመኳንንቱ ቤቶች ሁሉ በዝንብ መንጋ እንዲወረሩ አደረገ፤ መላዋም የግብጽ ምድር በዝንብ መንጋ ተበላሸች።

25 ከዚህ በኋላ ንጉሡ ሙሴንና አሮንን ጠርቶ “ሄዳችሁ በዚህች አገር ውስጥ ለአምላካችሁ መሥዋዕት አቅርቡ” አላቸው።

26 ሙሴ ግን እንዲህ አለ፦ “ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የምናቀርበው መሥዋዕት በግብጻውያን ዘንድ አጸያፊ ስለ ሆነ ይህን ማድረግ ተገቢ አይደለም፤ በግብጻውያን ዘንድ አጸያፊ የሆነውን መሥዋዕት በፊታቸው ብናቀርብ በድንጋይ አይወግሩንምን?

27 ስለዚህ እግዚአብሔር በሚያዘን መሠረት የሦስት ቀን መንገድ ወደ በረሓ ተጒዘን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ማቅረብ ይኖርብናል።”

28 ንጉሡም “ርቃችሁ የማትሄዱ ከሆነ በበረሓ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር እንድትሠዉ እለቃችኋለሁ፤ ለእኔም ጸልዩልኝ” አለ።

29 ሙሴም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “በነገው ቀን ዝንቦቹ ከአንተና ከመኳንንቱ ከሕዝቡም ዘንድ እንዲወገዱ ከአንተ እንደ ተለየሁ አሁኑኑ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ ነገር ግን ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ይሠዉ ዘንድ እንዳይሄዱ በመከልከል እንደገና ልታሞኘኝ አይገባም።”

30 ሙሴም ከንጉሡ ፊት ወጥቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤

31 እግዚአብሔርም ሙሴ እንዳለው ሁሉ አደረገ፤ የዝንብ መንጋውም ከንጉሡና ከመኳንንቱ ከሕዝቡም ሁሉ ፊት አንድ ሳይቀር ተወገደ፤

32 ይሁን እንጂ ንጉሡ አሁንም ልቡን በማደንደን የእስራኤልንም ሕዝብ አለቀቀም።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios