ዘፀአት 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፥ እኔ አንተን ለፈርዖን እንደ አምላክ አደርግሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን እንደ ነቢይ ሆኖ ስለ አንተ ይናገራል፤ 2 እኔ የማዝህን ሁሉ ለአሮን ንገረው፤ እርሱም ከአገሩ እንዲወጡ እስራኤላውያንን ይለቅ ዘንድ ለንጉሡ ይነግረዋል፤ 3 ነገር ግን እኔ የንጉሡን ልብ አደነድናለሁ፤ ከዚህም የተነሣ እኔ የቱንም ያኽል ምልክቶችንና ተአምራትን በግብጽ ምድር ባደርግ፥ 4 እናንተን አይሰማችሁም፤ ከዚያን በኋላ በግብጽ ላይ በታላቅ ፍርድ ብርቱ ቅጣት በማምጣት ሠራዊቴን፥ ሕዝቤን የእስራኤልን ልጆች ከምድረ ግብጽ አስወጣቸዋለሁ። 5 በዚህ ዐይነት የኀይል ክንዴን በእነርሱ ላይ አንሥቼ እስራኤላውያንን ከአገራቸው በማወጣበት ጊዜ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።” 6 ሙሴና አሮንም እግዚአብሔር ያዘዛቸውን ሁሉ ፈጸሙ። 7 ከንጉሡም ጋር በተነጋገሩበት በዚያ ጊዜ ሙሴ የሰማንያ ዓመት ዕድሜ ሲኖረው፥ አሮን ደግሞ ሰማንያ ሦስት ዓመት ሆኖት ነበር። የአሮን በትር 8 እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 9 “ፈርዖን ‘እስቲ ተአምራት በማድረግ ማንነታችሁን ግለጡልኝ’ ቢላችሁ ለአሮን ንገረውና በትሩን ወስዶ በንጉሡ ፊት ይጣለው፤ በዚያን ጊዜ በትሩ ተለውጦ እባብ ይሆናል።” 10 ስለዚህ ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ አሮንም በትሩን በንጉሡና በመኳንንቱ ፊት በጣለው ጊዜ ተለውጦ እባብ ሆነ። 11 ከዚህም በኋላ ፈርዖን ጠቢባኑንና አስማተኞቹን ጠራ፤ እነርሱም በአስማታቸው እንደዚሁ አደረጉ። 12 በትሮቻቸውን ወደ መሬት በጣሉአቸው ጊዜ ተለውጠው እባቦች ሆኑ፤ ነገር ግን የአሮን በትር የእነርሱን በትሮች ሁሉ ዋጠች። 13 ይህም ሁሉ ከሆነ በኋላ ንጉሡ ልቡን በማደንደን ጸና፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ሙሴንና አሮንን ሊሰማቸው አልፈለገም። ግብጽ በተአምራዊ መቅሠፍት ተመታች ሀ. ውሃው ወደ ደም ስለ መለወጡ 14 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ንጉሡ ልቡን በማደንደን ሕዝቡን አለቅም ብሎአል፤ 15 ስለዚህ ጠዋት በማለዳ ወደ ንጉሡ ሂድ፤ ወደ ዐባይ ወንዝ ሲወርድ ወደ እባብነት የተለወጠችውን በትር ይዘህ በወንዙ ዳር ቆመህ ጠብቀው። 16 እንዲህም በለው፥ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር በበረሓ ያገለግሉት ዘንድ ሕዝቡን እንድትለቅ እንድነግርህ ወደ አንተ ልኮኛል፤ አንተ ግን እስከ ዛሬ እምቢ ብለሃል። 17 አሁን ግን በሚያደርገው ነገር የእግዚአብሔርን ማንነት በግድ ታውቃለህ፤ እነሆ፥ እኔ በዚህ በትር የአባይን ወንዝ ውሃ እመታለሁ፤ ውሃውም ወደ ደም ይለወጣል። 18 በውስጡ ያሉ ዓሣዎች ሁሉ ይሞታሉ፤ የዐባይ ውሃ በጣም ከመሽተቱ የተነሣ ግብጻውያን ከዚህ ወንዝ ውሃ ቀድተው መጠጣት አይችሉም።’ ” 19 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “አሮን በትሩን ወስዶ በግብጽ ምድር በሚገኙት ወንዞች፥ ቦዮችና ኲሬዎች ሁሉ ላይ እንዲዘረጋ ንገረው፤ በዚያን ጊዜ ውሃው ሁሉ ተለውጦ ደም ይሆናል፤ ከእንጨትና ከድንጋይ በተሠሩት የውሃ ማጠራቀሚያ ዕቃዎች እንኳ ሳይቀር በግብጽ ምድር የሚገኘው ውሃ ሁሉ ደም ይሆናል።” 20 ሙሴና አሮንም እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ አሮንም በንጉሡና በመኳንንቱ ፊት በትሩን አንሥቶ የወንዙን ውሃ መታው። የወንዙም ውሃ ተለውጦ ደም ሆነ፤ 21 በወንዝ ውስጥ ያሉት ዓሣዎች ሁሉ ሞቱ፤ የዐባይ ወንዝ ውሃ ስለ ገማ ግብጻውያን ሊጠጡት አልቻሉም። በግብጽ ምድር ደም የሌለበት ስፍራ አልነበረም። 22 ከዚህ በኋላ የንጉሡ አስማተኞች በአስማታቸው እንደዚሁ አደረጉ፤ ንጉሡም ልቡን በማደንደን ጸና፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረውም ንጉሡ ሙሴንና አሮንን ማዳመጥ እምቢ አለ። 23 የሆነውን ነገር ሁሉ ከቁም ነገር ሳይቈጥረው ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመልሶ ሄደ። 24 ግብጻውያን ከዐባይ ወንዝ ውሃ መጠጣት ስላልቻሉ የሚጠጣ ውሃ ለማግኘት ከዐባይ ወንዝ ዳር ጒድጓድ ቈፈሩ። 25 እግዚአብሔርም ወንዙን ከመታ በኋላ ሰባት ቀን አለፈ። |