ዘፀአት 6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 እግዚአብሔርም ሙሴን “በንጉሡ በፈርዖን ላይ የማደርገውን አሁን ታያለህ፤ በኀይሌ ተገዶ ሕዝቤን ይለቃል፤ በኀያል ክንዴም ተሸንፎ ያባርራቸዋል።” የሙሴ መጠራት 2 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ 3 ሁሉን የምችል አምላክ (ኤልሻዳይ) መሆኔን በማስረዳት ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ተገልጬላቸዋለሁ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በተሰኘው ቅዱስ ስሜ አማካይነት ግን አልተገለጥኩላቸውም። 4 እንደ ስደተኞች ሆነው የሚኖሩባትን የከነዓንን ምድር ላወርሳቸው ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ። 5 እነሆ፥ አሁንም ግብጻውያን ባርያዎች አድርገው የሚያስጨንቁአቸውን የእስራኤላውያንን መራራ ጩኸት ሰምቼአለሁ፤ የገባሁትንም ቃል ኪዳን አስታውሼአለሁ። 6 ስለዚህም ለእስራኤላውያን የምለውን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ግብጻውያን ከሚያደርሱባችሁ የባርነት ጭቈና በማዳን ነጻ አወጣችኋለሁ፤ አሠቃቂ ቅጣት አመጣባቸው ዘንድ የኀይል ክንዴን በእነርሱ ላይ አነሣለሁ፤ እናንተንም እታደጋችኋለሁ፤ 7 የእኔ ሕዝብ አደርጋችኋለሁ፤ እኔም አምላካችሁ እሆናለሁ፤ ከግብጽ ባርነትም ነጻ በማወጣችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ መሆኔን ታውቃላችሁ፤ 8 ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ አወርሳቸው ዘንድ በመሐላ ቃል ኪዳን ወደገባሁባት ምድር አመጣችኋለሁ፤ ርስትም አድርጌ አወርሳችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ” 9 ሙሴም ይህን ሁሉ ለእስራኤላውያን ነገረ፤ እነርሱ ግን በወደቀባቸው ጨካኝ ጭቈና ምክንያት መንፈሳቸው ተሰብሮ ስለ ነበረ ሊያዳምጡት አልፈለጉም። 10 እንደገናም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 11 “ወደ ግብጽ ንጉሥ ሄደህ እስራኤላውያንን ከአገርህ እንዲወጡ ልቀቃቸው ብለህ ንገረው።” 12 ነገር ግን ሙሴ “ወገኖቼ እስራኤላውያን እንኳ አልሰሙኝም፤ ታዲያ፥ ንጉሡ እንዴት ሊሰማኝ ይችላል? እንደምታየኝ እኔ ኰልታፋ ነኝ” ሲል መለሰ። 13 እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን “እስራኤላውያንን ከግብጽ ምድር መርታችሁ እንድታወጡ እኔ ያዘዝኳችሁ መሆኔን ለእስራኤላውያንና ለግብጽ ንጉሥ ንገሩ” ብሎ አዘዛቸው። የሙሴና የአሮን ትውልድ 14 የያዕቆብ በኲር ልጅ ሮቤል፥ ሐኖክ፥ ፋሉ፥ ሔጽሮንና ካርሚ የሚባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነዚህም በየስማቸው የሮቤል ነገድ አባቶች ናቸው። 15 ስምዖን ከከነዓናዊት ሴት የተወለደውን ሻኡልን ጨምሮ ይሙኤል፥ ያሚን፥ ኦሃድ ያኪንና፥ ጾሓር የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነዚህም በየስማቸው የስምዖን ነገድ አባቶች ናቸው። 16 ሌዊ ጌርሾን፥ ቀዓትና መራሪ የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነዚህም በየስማቸው የሌዊ ነገድ አባቶች ናቸው፤ ሌዊ በሕይወት የኖረበት ዘመን 137 ዓመት ነበር። 17 ጌርሾን፥ ሊብኒና ሺምዒ የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም ብዙ ዘሮች ነበሩአቸው። 18 ቀዓት፥ ዓምራም፥ ይጽሐር፥ ኬብሮንና ዑዚኤል የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ ቀዓት በሕይወት የኖረበት ዘመን 133 ዓመት ነው። 19 መራሪ ማሕሊና ሙሺ የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነዚህና ዘሮቻቸው ሁሉ የሌዊ ወገኖች ናቸው። 20 ዓምራም ዮኬቤድ የተባለችውን የአባቱን እኅት አገባ፤ እርስዋም አሮንንና ሙሴን ወለደችለት። ዓምራም በሕይወት የኖረበት ዘመን 137 ዓመት ነው። 21 ይጽሐር ቆሬ፥ ኔፌግና ዚክሪ የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ 22 ዑዚኤልም ሚሻኤል፥ ኤልጻፋንና ሲትሪ የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት። 23 አሮን የነአሶን እኅት የሆነችውን የዓሚናዳብን ልጅ ኤሊሼባን አገባ፤ እርስዋም ናዳብ፥ አቢሁ፥ አልዓዛርና ኢታማር የተባሉትን ወንዶች ልጆች ወለደችለት። 24 ቆሬ አሲር፥ ኤልቃናና አቢያሳፍ የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነዚህም ለቆሬ ዘሮች ሁሉ የነገድ አባቶች ነበሩ። 25 የአሮን ልጅ አልዓዛር የፑቲኤልን ልጅ አገባ፤ እርስዋም ፊኒሐስን ወለደችለት፤ እነዚህ ሁሉ የሌዊ የነገድ አባቶችና አለቆች ነበሩ። 26 ከነዚህ መካከል እግዚአብሔር ሙሴና አሮን “የእስራኤልን ሕዝብ በየነገዳቸው ከግብጽ ምድር መርታችሁ አውጡ” ብሎ ያዘዛቸው ነው። 27 “የእስራኤልን ሕዝብ ልቀቅ” ብለው ከግብጽ ንጉሥ ጋር የተነጋገሩ እነርሱ ናቸው። እግዚአብሔር ለሙሴና ለአሮን የሰጠው ትእዛዝ 28 እግዚአብሔር ሙሴን በግብጽ ምድር በተናገረው ጊዜ፤ 29 “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እኔ የምነግርህን ሁሉ ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖን ንገር” አለው። 30 ሙሴ ግን “እኔ ኰልታፋ ነኝ፤ ታዲያ፥ ንጉሡ እንዴት ሊሰማኝ ይችላል?” ሲል መለሰ። |