ዘፀአት 34 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእንደገና የተሠሩት ሌሎች ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ( ዘዳ. 10፥1-5 ) 1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የመጀመሪያዎቹን የሚመስሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ቅረጽ፤ እኔም አንተ በሰበርካቸው ጽላቶች ላይ የነበሩትን ቃላት እጽፍባቸዋለሁ። 2 ነገ ጠዋት ተዘጋጅተህ ከእኔ ጋር ለመገናኘት ወደ ሲና ተራራ ጫፍ ና። 3 ከአንተ ጋር ማንም ሰው አይምጣ፤ በተራራው በማንኛውም በኩል ቢሆን ማንም ሰው አይታይ፤ በግ ወይም ከብት ማንኛውም እንስሳ በተራራው ግርጌ አይሰማራ።” 4 ስለዚህ ሙሴ ሁለት የድንጋይ ጽላቶችን ልክ እንደ ፊተኞቹ ቀረጸ፤ በማግስቱም ጠዋት በማለዳ ተነሥቶ ልክ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ጽላቶቹን ይዞ ወደ ሲና ተራራ ወጣ። 5 እግዚአብሔርም በደመና ወርዶ ከእርሱ ጋር በዚያ ቆመ፦ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ” ብሎ ቅዱስ ስሙንም አስታወቀው። 6 እግዚአብሔር በፊቱ ሲያልፍ እንዲህ ብሎ ዐወጀ፤ “እኔ እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሐሪ አምላክ ነኝ፤ እኔ ለቊጣ የዘገየሁ፤ ዘለዓለማዊ ፍቅሬና ታማኝነቴ የበዛ ነው፤ 7 ዘለዓለማዊ ፍቅሬንም እስከ ብዙ ሺህ ትውልድ እጠብቃለሁ፤ በደልን መተላለፍንና ኃጢአትን ሁሉ ይቅር እላለሁ፤ ነገር ግን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ድረስ ስለ ወላጆቻቸው ኃጢአት ከመቅጣት አልገታም።” 8 ሙሴም ወዲያውኑ በምድር ላይ ተደፍቶ ሰገደ፤ 9 እንዲህም አለ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፥ በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝቼ ከሆነ ከእኛ ጋር አብረህ እንድትወጣ እለምንሃለሁ፤ ይህ ሕዝብ እልኸኛ ነው፤ ነገር ግን ኃጢአታችንንና ክፉ ሥራችንን ሁሉ ይቅር በል፤ የራስህ ሕዝብ አድርገህ ተቀበለን።” የቃል ኪዳኑ መታደስ ( ዘፀ. 23፥14-19 ፤ ዘዳ. 7፥1-5 ፤ 16፥1-17 ) 10 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ከዚህ በፊት በምድር ላይ በማንኛውም ሕዝብ ዘንድ ሆኖ የማያውቅ ድንቅ ነገር በሕዝብህ ፊት አደርጋለሁ፤ አስፈሪ የሆነ ድንቅ ነገር ስለማደርግ እኔ እግዚአብሔር የማደርጋቸውን ድንቅ ነገሮች በመካከላቸው የምትኖርባቸው ሕዝቦች ሁሉ ያያሉ። 11 ዛሬ ለእናንተ የምሰጠውን ሕግ ጠብቁ፤ እኔም አሞራውያንን፥ ከነዓናውያንን፥ ሒታውያንን፥ ፈሪዛውያንን፥ ሒዋውያንንና ኢያቡሳውያንን ከፊታችሁ አባርራለሁ፤ 12 አጥፊ ወጥመድ ስለሚሆኑባችሁ ከምትሄዱባቸው ሕዝቦች ጋር ቃል ኪዳን አትግቡ። 13 ይልቅስ መሠዊያዎቻቸውን ሰባብሩ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውንም አፈራርሱ፤ አሼራ የተባለች አምላካቸውንም ምስሎች ሰባብራችሁ ጣሉ። 14 “እኔ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ስለ ሆንኩ ከእኔ በቀር ለሌሎች አማልክት አትስገዱ፤ 15 ለከንቱ አማልክታቸው ሲሰግዱና መሥዋዕት ሲሠዉላቸው እንድትተባበሩአቸው ስለሚጠይቁአችሁ፥ እናንተም እነርሱ ለአማልክታቸው የሚያቀርቡትን ምግብ ለመብላት ስለምትፈተኑ፤ በአገሩ ከሚኖሩ ሕዝቦች ጋር ቃል ኪዳን አትግቡ። 16 ሴቶች ልጆቻቸውን ለወንዶች ልጆቻችሁ ሚስቶች ብታደርጉ የእነዚያ ሴቶች ልጆች ጣዖት ማምለክን ስለሚከተሉ የእናንተንም ወንዶች ልጆች ጣዖት አምልኮን እንዲከተሉ ያደርጓቸዋል። 17 “ብረት አቅልጣችሁ አማልክት አትሥሩ፤ 18 “ከግብጽ የወጣችሁት በአቢብ ወር ስለ ሆነ የቂጣን በዓል በመጠበቅ በየዓመቱ አክብሩ፤ እንዳዘዝኳችሁ በአቢብ ወር እስከ ሰባት ቀን ቂጣ ብሉ። 19 “በኲር ሆኖ የሚወለድ ወንድ ልጅ ሁሉ የእኔ ነው፤ የማንኛውም እንስሳ ተባዕት ሁሉ በሬም ሆነ በግ የእኔ ነው፤ 20 ነገር ግን የበግ ጠቦት በመተካት የአህያን በኲር ለመዋጀት ትችላላችሁ፤ የማትዋጁት ከሆነ ግን አንገቱን ቈልምሙት፤ በኲር ሆኖ የተወለደውንም ወንድ ልጅ ሁሉ ትዋጃላችሁ። “መባ ሳይዝ ማንም ሰው ባዶ እጁን በፊቴ አይታይ። 21 “ሥራችሁን ሁሉ የምታከናውኑባቸው ስድስት ቀኖች አሉላችሁ፤ በእርሻም ሆነ በመከር ወራት በሰባተኛው ቀን ምንም ሥራ አትሥሩ። 22 “የስንዴአችሁን በኲራት በምትሰበስቡበት ጊዜ የመከርን በዓል አክብሩ፤ የዓመቱ መጨረሻ በሆነው በፍሬ መከር ጊዜ የዳስን በዓል አክብሩ። 23 “በዓመት ሦስት ጊዜ ወንዶች ሁሉ ለእኔ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ይሰግዱ ዘንድ ይምጡ። 24 አሕዛብን ሁሉ አስወግጄ ግዛታችሁን አሰፋለሁ፤ ስለዚህ በእነዚህ በሦስት በዓላት ወቅት ወደ እኔ ስትቀርቡ አገራችሁን ለመውረር የሚመኝ ማንም አይመጣም። 25 “ለእኔ የእንስሶች መሥዋዕት በምትሠዉበት ጊዜ ደሙን እርሾ ካለበት ኅብስት ጋር አታቅርቡልኝ ለፋሲካ በዓል ከታረደው እንስሳ ምንም ሥጋ እስከ ማግስቱ ጠዋት ድረስ አታቈዩ። 26 “በየዓመቱ የመከራችሁን በኲራት ወደ እግዚአብሔር ቤት አምጡ። “የበግም ሆነ የፍየል ግልገል በእናቱ ወተት አትቀቅሉ።” 27 እግዚአብሔር ሙሴን፦ “ከአንተም ሆነ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ቃል ኪዳን የምገባው በዚህ ቃል መሠረት ስለ ሆነ ይህን ቃል በመጽሐፍ ጻፈው” አለው። 28 ሙሴም ምንም ሳይበላና ሳይጠጣ ከእግዚአብሔር ጋር አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየ፤ ጌታም በጽላቶቹ ላይ የቃል ኪዳን ቃላት የሆኑትን ዐሥሩን ትእዛዞች ጻፈ። ሙሴ ከሲና ተራራ መውረዱ 29 ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር ቈይቶ ስለ ነበር፥ ዐሥሩ ትእዛዞች የተጻፉባቸውን ሁለቱን የምስክር ጽላቶች ይዞ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ፊቱ አበራ፤ ለእርሱ ግን ይህ ሁሉ አይታወቀውም ነበር። 30 አሮንና ሕዝቡ ሁሉ ሙሴን ባዩ ጊዜ ፊቱ እንደሚያበራ ተመልክተው ወደ እርሱ ለመቅረብ ፈሩ። 31 ሙሴ ግን ጠራቸው፤ አሮንና የሕዝቡ አለቆች ወደ እርሱ ቀርበው አነጋገራቸው። 32 ከዚያም በኋላ የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ወደ እርሱ መጡ፤ ሙሴም በሲና ተራራ እግዚአብሔር የገለጠለትን ሕግ ሁሉ ሰጣቸው። 33 ሙሴ ከእነርሱ ጋር መነጋገሩን ካበቃ በኋላ ፊቱን በሻሽ ሸፈነ፤ 34 ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር ወደ እግዚአብሔር መገኛ ድንኳን በገባ ቊጥር ሻሹን ከፊቱ ላይ ያነሣ ነበር፤ ከዚያም በሚወጣበት ጊዜ የታዘዘውን ሁሉ ለእስራኤላውያን ይነግራቸው ነበር። 35 እነርሱም ፊቱ ሲያበራ ያዩት ነበር፤ ስለዚህም ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር ወደዚያ እስከሚሄድበት ጊዜ ድረስ ፊቱን በሻሽ ይሸፍን ነበር። |