Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዘፀአት 16 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እግዚአብሔር ለሕዝቡ መናንና ድርጭቶችን ማዝነቡ

1 መላው የእስራኤል ማኅበር ከግብጽ በወጡ በሁለተኛው ወር፥ በዐሥራ አምስተኛው ቀን፥ ከኤሊም ተነሥተው በሲና እና በኤሊም መካከል ወዳለው “ሲን” ተብሎ ወደሚጠራው ምድረ በዳ መጡ።

2 በዚያም ምድረ በዳ ሁሉም ተባብረው በሙሴና በአሮን ላይ በማጒረምረም እንዲህ አሉ፦

3 “ምነው በግብጽ ሳለን እግዚአብሔር በገደለን ኖሮ፥ በዚያ ሌላው ቢቀር ሥጋም ሆነ ሌላ ምግብ የፈለግነውን ያኽል መመገብ እንችል ነበረ፤ እናንተ ግን ሁላችንም በራብ እንድናልቅ ወደዚህ በረሓ አወጣችሁን።”

4 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ እኔ ለሁላችሁም የሚበቃ ምግብ ከሰማይ ላዘንብላችሁ ነው፤ ሕዝቡ በየዕለቱ ወጥተው ለዚያው ቀን የሚበቃቸውን ምግብ ይሰብስቡ፤ በዚህ ዐይነት እኔ የምሰጣቸውን መመሪያ ይጠብቁ እንደ ሆነ እፈትናቸዋለሁ።

5 በስድስተኛው ቀን ግን፥ ከሌሎቹ ዕለቶች በአንዱ ቀን የሚሰበስቡትን እጥፍ ሰብስበው ያዘጋጁ።”

6 ስለዚህ ሙሴና አሮን ለመላው የእስራኤል ሕዝብ እንዲህ አሉ፦ “ከግብጽ ምድር ያወጣችሁ እግዚአብሔር መሆኑን በዛሬይቱ ምሽት ታውቃላችሁ፤

7 በማለዳ የእግዚአብሔርን ክብር ታያላችሁ፤ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ማጒረምረማችሁን ሰምቶአል፤ በእኛ ላይ የምታጒረመርሙት እኛ ማን ነን?”

8 ከዚህም በኋላ ሙሴ እንዲህ አለ፦ “በእርሱ ላይ ማጒረምረማችሁን ስለ ሰማ በማታ የምትበሉትን ሥጋና በማለዳ ደግሞ የፈለጋችሁትን ያኽል እንጀራ የሚሰጣችሁ እግዚአብሔር ነው፤ እኛ ምንድን ነን? በእኛ ላይ ስታጒረመርሙ በእግዚአብሔር ላይ ማጒረምረማችሁ ነው።”

9 ሙሴ አሮንን፦ “እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ማጒረምረማችሁን ስለ ሰማ፥ መላው የእስራኤል ማኅበር መጥታችሁ በእግዚአብሔር ፊት ቁሙ ብለህ ንገራቸው” አለው።

10 አሮንም ለመላው ማኅበር በተናገረ ጊዜ ፊታቸውን ወደ በረሓው አዞሩ፤ የእግዚአብሔርም ክብር በደመና ተገለጠ፤

11 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦

12 “እስራኤላውያን በእኔ ላይ ማጒረምረማቸውን ሰምቼአለሁ፤ ስለዚህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘በዛሬው ምሽት ፀሐይ ከመጥለቅዋ በፊት ምግብ የሚሆናችሁን ሥጋ ታገኛላችሁ፤ በማለዳም የምትፈልጉትን ያኽል እንጀራ ታገኛላችሁ፤ በዚያን ጊዜም እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንኩ ታውቃላችሁ።’ ”

13 በምሽትም ብዙ ድርጭቶች እየበረሩ መጥተው ሰፈሩን ሸፈኑት፤ በማለዳ ደግሞ በሰፈሩ ዙሪያ ጤዛ ነበረ፤

14 ጤዛውም ከተነነ በኋላ ደቃቅና ስስ የሆነ ነገር በበረሓማው ምድር ላይ ታየ፤ እርሱም በምድር ላይ ያረፈ ዐመዳይ ይመስል ነበር።

15 እስራኤላውያን ባዩት ጊዜ ምን እንደ ሆነ ባለማወቃቸው “ይህ ነገር ምንድን ነው?” በማለት እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። ሙሴም እንዲህ አላቸው፦ “ይህ እንድትበሉት እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ነው፤

16 ከእናንተ እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያኽል ብቻ እንዲሰበስብ እግዚአብሔር አዞአል፤ ስለዚህ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል አንድ ኪሎ ተኩል ይውሰድ።”

17 እስራኤላውያንም እንደዚሁ አደረጉ፤ አንዳንዶቹ ብዙ አንዳንዶቹ ጥቂት ሰበሰቡ፤

18 በሰፈሩትም ጊዜ ብዙ የሰበሰበው አልተረፈውም፤ ጥቂትም የሰበሰበ አላነሰበትም፤ እያንዳንዱ የሰበሰበው ልክ የሚበቃውን ያኽል ነበር።

19 ሙሴም “ማንም ለዕለት ከሚያስፈልገው አስበልጦ ለነገ ማስተረፍ የለበትም” አለ።

20 አንዳንዶቹ የሙሴን ቃል ባለመስማት ለዕለቱ ከሰበሰቡት ከፍለው አሳደሩ፤ በማግስቱም ጠዋት ተልቶ ተገኘ፤ በስብሶም ሸተተ፤ ሙሴም እጅግ ተቈጣቸው።

21 በየማለዳው እያንዳንዱ የሚበቃውን ያኽል ይሰበስብ ነበር፤ ፀሐይ ከሞቀ በኋላ ግን በመሬት ላይ የቀረው ሁሉ ይቀልጥ ነበር።

22 በስድስተኛው ቀን ለእያንዳንዱ ሦስት ኪሎ ይሰበስቡ ነበር፤ የማኅበሩ መሪዎች ሁሉ መጥተው ስለ ምግቡ ለሙሴ ነገሩት፤

23 እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “የነገው ዕለት ለእርሱ ተለይቶ የተቀደሰ የዕረፍት ቀን እንዲሆን እግዚአብሔር አዞአል፤ ስለዚህ ዛሬውኑ የምትጋግሩትን ጋግሩ፤ የምትቀቅሉትንም ቀቅሉ፤ የተረፈው ተከፍሎ ለነገ ይቀመጥ።”

24 ሙሴም እንዳዘዛቸው የተረፈውን ለሚቀጥለው ቀን አስቀመጡ፤ እርሱም አልሸተተም ወይም አልተላም።

25 ሙሴም እንዲህ አላቸው፦ “ይህን ዛሬውኑ ብሉት፤ ዛሬ ሰንበት ስለ ሆነና እርሱም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የዕረፍት ቀን በመሆኑ በዛሬው ዕለት ምግቡን በሜዳ ላይ አታገኙም።

26 ስለዚህ ስድስት ቀን በተከታታይ ይህን ምግብ ሰብስቡ፤ የዕረፍት ቀን በሆነው በሰባተኛው ቀን ግን ምንም ምግብ አይኖርም።”

27 በሰባተኛው ቀን ከሕዝቡ መካከል ጥቂት ሰዎች ምግብ ለመሰብሰብ ወጡ፤ ነገር ግን ምንም አላገኙም።

28 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እናንተ ትእዛዞቼንና መመሪያዎቼን መፈጸም እምቢ የምትሉት እስከ መቼ ነው?

29 እኔ አንድ የዕረፍት ቀን ሰጥቻችኋለሁ፤ ዘወትር በስድስተኛው ቀን ለሁለት ቀን የሚበቃ ምግብ ስለምሰጣችሁ በሰባተኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው ከቤት ሳይወጣ፥ ባለበት ስፍራ ሁሉ ዕረፍት አድርጎ ይዋል።”

30 ስለዚህ ሕዝቡ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ።

31 እስራኤላውያን ያን ምግብ “መና” ብለው ጠሩት፤ እርሱም እንደ ድንብላል ፍሬ ነጭ የሆነ ነበር፤ ጣዕሙም ከማር ጋር እንደ ተጋገረ ቂጣ ነበር።

32 ሙሴም “እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው፤ ከግብጽ ምድር ባወጣኋችሁ ጊዜ በምድረ በዳ ያበላኋችሁን እንጀራ ያዩ ዘንድ ከእርሱ አንድ አንድ ኪሎ ተኩል ሙሉ ለልጅ ልጆቻችሁ ይጠበቅ።” አለ።

33 ሙሴም አሮንን “አንድ የሸክላ ዕቃ ወስደህ አንድ ኪሎ ተኩል በሚይዝ መስፈሪያ መና አኑርበት፤ ለመጪውም ትውልድ በእግዚአብሔር ፊት ተጠብቆ እንዲኖር አድርግ” አለው።

34 እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት አሮን ለመጪው ትውልድ ተጠብቆ እንዲኖር መናውን በኪዳኑ ታቦት ፊት አኖረው።

35 እስራኤላውያንም ወደሚኖሩባት ወደ ከነዓን ምድር ድንበር እስኪደርሱ ድረስ ለአርባ ዓመት ሙሉ ይህን መና ተመገቡ።

36 በዚያን ጊዜ መደበኛ መስፈሪያዎች ኢፍና ጎሞር ይባሉ ነበሩ። ኢፍ ዐሥራ አምስት ኪሎ ሲመዝን ጎሞር አንድ ኪሎ ተኩል ነበር።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios