ዘፀአት 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእስራኤላውያን በግብጽ ሲኖሩ የደረሰባቸው ግፍና በደል 1 እያንዳንዱ ከቤተሰቡ ጋር ሆኖ ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብጽ የገቡት፥ እስራኤል ተብሎ የተጠራው የያዕቆብ ልጆች ስሞች እነዚህ ናቸው፦ 2 ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ 3 ይሳኮር፥ ዛብሎን፥ ብንያም፥ 4 ዳን፥ ንፍታሌም፥ ጋድና አሴር። 5 በቀጥታ ከያዕቆብ የተገኙት የተወላጆቹ ጠቅላላ ብዛት ሰባ ሲሆን፥ ዮሴፍ ግን ቀደም ብሎ በግብጽ ይኖር ነበር። 6 በዘመናት ውስጥ ዮሴፍ፥ ወንድሞቹና የዚያ ትውልድ አባቶች ሁሉ ሞቱ። 7 ሆኖም የእነርሱ ዘሮች የሆኑ እስራኤላውያን ተዋልደው ቊጥራቸው ከመብዛቱ የተነሣ የግብጽን ምድር ሞሉአት፤ እጅግም ብርቱዎች ሆኑ። 8 ከዚህ ሁሉ በኋላ ዮሴፍ ያደረገውን ነገር የማያውቅ አዲስ ንጉሥ በግብጽ ተነሣ። 9 እርሱም ለሕዝቡ እንዲህ አለ፦ “እነሆ፥ እነዚህ እስራኤላውያን ቊጥራቸው በዝቶአል፤ የኀይላቸውም ብርታት አስጊ ሆኖብናል፤ 10 ከዚህም የተነሣ ከጠላቶቻችን ጋር ተባብረው ከወጉን በኋላ ከአገሪቱ አምልጠው መሄድ ይችላሉ፤ ስለዚህ ቊጥራቸው እየበዛ እንዳይሄድ ኑ፤ አንድ ዘዴ እንፈልግ።” 11 ከዚህ በኋላ በብርቱ ሥራ ይጨቊኑአቸው ዘንድ ጨካኞች የሆኑ አሠሪዎችን ሾሙባቸው፤ በዚህም ሁኔታ ዕቃ ማከማቻ የሆኑትን ፊቶምና ራምሴ የተባሉትን ከተሞች ለፈርዖን ሠሩ። 12 ነገር ግን እስራኤላውያን በተጨቈኑ መጠን ቊጥራቸው ይበልጥ እየበዛና በምድሪቱም ላይ እየተስፋፉ ሄዱ፤ ከዚህም የተነሣ ግብጻውያን እስራኤላውያንን ፈሩአቸው። 13 ርኅራኄ በጐደለውም ጭካኔ በባርነት አሠሩአቸው። 14 ጭቃ በማቡካት፥ ጡብ በማዘጋጀትና በእርሻ ውስጥ በጭካኔ ከባድ ሥራ በማሠራት ሕይወታቸው መራራ እንዲሆን አደረጉ። 15 ከዚህ በኋላ የግብጽ ንጉሥ የዕብራውያን ሴቶችን የሚረዱ ጺጳራና ፉሐ ተብለው የሚጠሩትን ሁለት አዋላጆች እንዲህ አላቸው፤ 16 “የዕብራውያንን ሴቶች በምታዋልዱበት ጊዜ የሚወለደው ሕፃን ወንድ ከሆነ ወዲያውኑ ግደሉት፤ ሴት ከሆነች ግን በሕይወት እንድትኖር ተዉአት”። 17 አዋላጆቹ ግን እግዚአብሔርን በመፍራት የግብጽ ንጉሥ እንዳዘዛቸው አላደረጉም፤ ወንዶችንም ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ ተዉአቸው። 18 ከዚህ በኋላ የግብጽ ንጉሥ አዋላጆቹን አስጠርቶ “ወንዶች ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ ያደረጋችኹበት ምክንያት ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃቸው። 19 እነርሱም “የዕብራውያን ሴቶች እንደ ግብጻውያን ሴቶች አይደሉም፤ እነርሱ ብርቱዎች ስለ ሆኑ አዋላጆች ወደ እነርሱ ገና ከመምጣታቸው በፊት ያለምንም ችግር ይወልዳሉ” ሲሉ መለሱለት። 20-21 አዋላጆቹ እግዚአብሔርን ስለ ፈሩ እግዚአብሔርም ለእነርሱ መልካም ነገር አደረገላቸው፤ ለያንዳንዳቸውም ቤተሰብ ሰጣቸው፤ በዚህም ዐይነት የእስራኤል ሕዝብ በቊጥር እየበዙና ብርቱዎችም እየሆኑ ሄዱ። 22 ከዚህም በኋላ ንጉሡ “ከዕብራውያን የሚወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ እያነሣችሁ ዓባይ ወንዝ ውስጥ ጣሉ፤ ሴቶች ልጆች ግን በሕይወት ይኑሩ” ሲል ለሕዝቡ ጥብቅ ትእዛዝ አስተላለፈ። |