Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


መክብብ 6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 በዚህ ዓለም በሰው ሁሉ ላይ የሚደርስ እጅግ የከፋ ነገር ተመለከትኩ።

2 እግዚአብሔር ለሰው ምድራዊ ሀብትንና ብልጽግናን ክብርንም ሁሉ ይሰጠዋል፤ ከሚያስፈልገውም ነገር ሁሉ ምንም አያጐድልበትም፤ ይሁን እንጂ በሚሰጠው ሀብት ሁሉ አይደሰትበትም፤ ይልቁንም እርሱ ደክሞ ያፈራውን ሌላ ሰው ይደሰትበታል። ይህም ከንቱና እጅግ የከፋ በደል ነው።

3 እንግዲህ፥ አንድ ሰው መቶ ልጆች ቢወልድ፥ ረጅም ዕድሜ አግኝቶ ብዙ ዘመን በሕይወት ቢኖርም፥ እንዲደሰትበት ከሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ድርሻውን ሳያገኝ ቀርቶ በመጨረሻም በክብር ለመቀበር ሳይበቃ ቢቀር፥ እኔ ስለ እርሱ አዝናለሁ፤ ከእንደዚህ ያለውም ሰው ይልቅ በእናቱ ማሕፀን ሞቶ የተወለደ ጭንጋፍ ይሻላል አልኩ።

4 ያ ጭንጋፍ ተረስቶ ወደሚቀርበት ጨለማ ስለሚወሰድ ቀድሞውኑ ሳይወለድ ቢቀር በተሻለው ነበር።

5 እርሱ የፀሐይን ብርሃን ሳያይ የሕይወትንም ምንነት ሳያውቅ አንድ ጊዜ ዐርፎአል።

6 ስለዚህ ሁለት ሺህ ዓመት ያለ ደስታ ቢኖር ጥቅሙ ምንድን ነው? ዞሮ ዞሮ ሁለቱም የሚሄዱት ወደ አንድ ተመሳሳይ ስፍራ ነው።

7 ሰው በሥራ መድከሙ የሚበላውን ነገር ለማግኘት ነበር፤ ይሁን እንጂ “በቃኝ!” ማለት አያውቅም።

8 ታዲያ፥ ጥበበኛ ሰው ከሞኝ የሚሻልበት ምን ነገር አለ? ለድኻስ ሕይወትን ለመምራት መቻሉ የሚያተርፍለት ጥቅም ምንድን ነው?

9 ለምኞት ከመገዛት ይልቅ ባለ ነገር መርካት ይሻላል፤ ይህም ደግሞ ከንቱና ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር ነው።

10 ያለ ነገር ሁሉ ስም ተሰጥቶታል፤ የሰዎችም ማንነት ታውቆአል፤ ከእነርሱ በላይ ብርቱ ከሆነው ጋር መቋቋም አይችሉም።

11 ብዙ በተናገርን መጠን ቁምነገሩ ያነሰ ነው፤ ስለዚህ የመናገር ጥቅሙ ምንድን ነው?

12 ከንቱ ሆኖ እንደ ጥላ በሚያልፍ ዘመኑ ለሰው የሚበጀውን ነገር የሚያውቅ ማን ነው? ወይስ ከሞተ በኋላ በዚህ ዓለም ምን እንደሚሆን ለሰው ማን ሊነግረው ይችላል?

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios