መክብብ 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔርን ለማምለክ የሚደረግ አክብሮት 1 ወደ እግዚአብሔር ቤት በምትገባበት ጊዜ ለአረማመድህ ጥንቃቄ አድርግ፤ እዚያ ሄዶ ደጉን ከክፉ ለይተው የማያውቁ ሞኞች ሰዎች እንደሚያደርጉት መሥዋዕት ከማቅረብ ይልቅ የምክር ቃላትን ለመስማት ዝግጁ ሆኖ መገኘት ይበልጣል። 2 ከመናገርህ በፊት አስብ፤ ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ለመስጠት በችኰላ ስእለት አታድርግ፤ እግዚአብሔር በሰማይ አንተ ግን በምድር መሆንህን በማሰብ የምትናገረው ቃል የተመጠነ ይሁን። 3 ስለ አንድ ነገር ብታስብ ስለ እርሱ ታልማለህ፤ ብዙ ከመናገር የተነሣ ትሳሳታለህ፤ 4 ስለዚህ እግዚአብሔር በሞኞች አይደሰትም፤ ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ለመስጠት በተሳልክ ጊዜ ወዲያውኑ የተሳልከውን ለመፈጸም ዝግጁ ሁን፤ 5 ተስለህ የማትፈጽመው ከሆነ ግን ቀድሞውንም ባትሳል የተሻለ ነው። 6 ወደ ኃጢአት እንዳይመራህ ለአንደበትህ ከገደብ ያለፈ ነጻነት አትስጠው፤ በዚህ ዐይነት “ይህን የተናገርኩት ሳላውቅ ነው” ብለህ በእግዚአብሔር አገልጋይ ፊት ይቅርታ ከመጠየቅ ትድናለህ፤ አለበለዚያ ግን የደከምክበትን ያጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔርን ቊጣ በገዛ እጅህ እንደ መጋበዝ ይሆንብሃል። 7 ብዙ ሕልምና ብዙ ልፍለፋ ከንቱ ነው፤ ከዚህስ ይልቅ እግዚአብሔርን ፍራ። የኑሮ ከንቱነት 8 በአንድ አገር ግፍ ሲሠራና መብት በመንፈግ ፍትሕ ሲጓደል ባየህ ጊዜ አትደነቅ፤ እያንዳንዱ ገዥ የበላይ ተመልካች አለው፤ ከሁሉም በላይ የሆነ ሌላ ተመልካች ደግሞ አለ። 9 የመሬት ምርት መጨመር ሁሉንም ይጠቅማል፤ ንጉሡ ራሱ ከእርሻው ይጠቀማል። 10 ብርን የሚወድ ብር አግኝቶ አይጠግብም፤ ሀብታም ለመሆን የሚፈልግም ሰው ትርፍ አግኝቶ በቃኝ አይልም፤ ይህም ከንቱ ነው። 11 ሀብት ሲበዛ በዚያው መጠን በላተኛው ይበዛል፤ ታዲያ፥ አይቶ ከመደሰት በቀር ለባለቤቱ ምን የሚተርፈው ነገር አለ? 12 የጉልበት ሥራ የሚሠራ ሰው ብዙም ሆነ ጥቂት ቢመገብ የሰላም እንቅልፍ አግኝቶ ያድራል፤ የባለ ጸጋ ሰው የሀብት ብዛት ግን ሀብቱ እንቅልፍ ይነሣዋል። 13-14 በዚህ ዓለም እጅግ የሚያሳዝን ክፉ ነገር ደግሞ አየሁ፤ ይኸውም ሰዎች ለክፉ ቀን ይጠቅመናል ብለው ሀብት ያከማቻሉ፤ ነገር ግን በአንድ መጥፎ አጋጣሚ ሀብታቸውን ያጡና ለልጆቻቸው የሚተላለፍ ምንም ነገር ሳይተርፋቸው ይቀራል። 15 ሰው ሁሉ ራቁቱን እንደ ተወለደ ባዶ እጁን ተመልሶ ይሄዳል፤ የቱንም ያኽል በሥራ ቢደክም ይዞት የሚሄደው ነገር የለም። 16 ራቁቱን እንደ ተወለደ ራቁቱን መሄዱ እጅግ የሚያሳዝን ነው፤ ድካሙ ሁሉ ነፋስን እንደ መጨበጥ ከንቱ ከሆነ ጥቅሙ ምንድን ነው? 17 ዕድሜውንም የሚፈጽመው ጨለማ በወረሰው ሕይወት፥ በሐዘን፥ በሚያስጨንቅ ሐሳብ፥ በብስጭትና በሕመም ነው። 18 እንግዲህ እኔ የተመለከትኩት የተሻለ ነገር ቢኖር ሰው በዚህ ዓለም ሳለ እግዚአብሔር በሰጠው አጭር ዕድሜ የደከመበትን ሁሉ በመብላትና በመጠጣት መደሰቱ ነው፤ የሰው ዕድል ፈንታም ይኸው ብቻ ነው። 19 እግዚአብሔር ለሰው ሀብትና ብልጽግናን መስጠቱ የደከመበትን ድርሻ አግኝቶ በመብላትና በመጠጣት ደስ እንዲለው ፈቅዶለት ነው፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። 20 እግዚአብሔርም በዚህ ሁሉ የልብ ደስታን ስለ ሰጠው በዕድሜው ማጠርና መርዘም ከመጠን በላይ አይጨነቅም። |