መክብብ 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምጥበበኛ ሰው ሊያደርገው የሚገባ ነገር 1 እንጀራህን በውሃ ላይ ጣል፤ ከብዙ ቀንም በኋላ መልሰህ ታገኘዋለህ። 2 ወደ ፊት በዓለም ላይ ምን ዐይነት ክፉ ነገር እንደሚመጣ አታውቅም፤ ስለዚህ ያለህን ሀብት በሰባት ወይም በስምንት ቦታ ከፋፍለህ አኑር። 3 ደመና ብዙ ውሃ ባዘለ ጊዜ በምድር ላይ ያዘንበዋል፤ ዛፍ ወደ ደቡብም ሆነ ወደ ሰሜን ቢወድቅ በዚያው በወደቀበት ስፍራ ይኖራል። 4 ነፋስን የሚጠብቅ አይዘራም፤ ደመናን የሚመለከት አያጭድም። 5 የነፋስን አካሄድና የሰውም ሕይወት አፈጣጠር በእናቱ ማሕፀን እንዴት እንደሚጀመር እንደማታውቅ የሁሉ ነገር ፈጣሪ እግዚአብሔር ሥራውን እንዴት እንደሚያከናውን ማወቅ አትችልም። 6 ጧትም ሆነ ማታ ዘር መዝራትህን አታቋርጥ፤ ሁሉም ይበቅል ወይም አይበቅል እንደ ሆነ የትኛው አዘራር እንደሚሻል ለይተህ ማወቅ አይቻልህም። 7 ብርሃን ታይቶ አይጠገብም፤ ስለዚህ የቀንን ብርሃን እያዩ መደሰት መልካም ነው። 8 ሰው የቱንም ያኽል ብዙ ዓመት ቢኖር በዚያው በተሰጠው በዕድሜው ዘመን ሁሉ ደስ ሊለው ይችላል፤ ሆኖም የዚህ ዓለም ነገር ሁሉ ከንቱ መሆኑንና ወደፊት የሚመጣበትም የጨለማ ዘመን ዘለዓለማዊ እንደ ሆነ አይዘንጋ። ለወጣቶች የሚሆን ምክር 9 ወጣት ሆይ! ወጣትነት እጅግ ግሩም ስለ ሆነ በወጣትነትህ ዘመን ደስ ይበልህ፤ በልብህም ሐሤት አድርግ፤ ዐይንህ የሚያየውንና ልብህ የሚመኘውን ሁሉ ፈጽም፤ ሆኖም ስለዚህ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንደሚያመጣህ ዕወቅ። 10 የወጣትነትና የብርቱ ጐልማሳነት ጊዜ ቶሎ ስለሚያልፍ ሐዘንን ከልብህ፥ ጭንቀትንም ከአእምሮህ አስወግድ። |