Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


መክብብ 10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 የሞቱ ዝንቦች ተቀምሞ የተሠራውን የዘይት ሽቶ ሊያገሙት ይችላሉ፤ እንዲሁም ትንሽ ሞኝነት ታላቅ ጥበብን ያጠፋል።

2 ጥበበኛ መልካም ነገር መሥራቱ፥ ሞኝም መሳሳቱ የተለመደ ተግባር ነው።

3 ሞኝ ሰው በሚተላለፍበት መንገድ ሁሉ ያለ ሐሳብ ይራመዳል፤ ለሰውም ሁሉ ሞኝነቱን ያሳውቃል።

4 ጸጥ ብለህ ብትታገሥ ከባድ ለሆነው በደልህ እንኳ ይቅርታ ማግኘት ስለምትችል አለቃህ በተቈጣህ ጊዜ የሥራ ቦታህን አትልቀቅ፤

5 በዓለም ላይ ሌላም ክፋት አይቻለሁ፤ ይኸውም ገዢዎች የሚፈጽሙት ግፍ ነው።

6 ሞኞች ከፍተኛ ሥልጣን ሲያገኙ ባለጸጎች ግን ችላ ተብለው ዝቅተኛ ስፍራ ይዘዋል።

7 መሳፍንት እንደ አገልጋዮች በእግራቸው ሲሄዱ፥ አገልጋዮች ግን በፈረስ ተቀምጠው ሲጓዙ አየሁ።

8 ጒድጓድን የሚቈፍር ሰው ራሱ ይወድቅበታል፤ ቅጽርንም የሚያፈርስ በእባብ ይነደፋል፤

9 ድንጋይን የሚፈነቅል በፈነቀለው ድንጋይ ራሱ ይጐዳል፤ እንጨትን የሚፈልጥ በፈለጠው እንጨት ይቈስላል።

10 የደነዘ መጥረቢያውን የማይስል ሰው ኀይሉን በከንቱ ይጨርሳል፤ ስለዚህ ጥሩ ውጤት ለማግኘት በጥበብ መሥራት ያስፈልጋል።

11 እባብ ከነከሰህ በኋላ የእባብ ማፍዘዣ ድግምት ምንም አይጠቅምህም።

12 ጥበበኛ ሰው በንግግሩ ክብርን ያገኛል፤ ሞኝ ግን በገዛ ንግግሩ ይጠፋል፤

13 የሞኝ ሰው ንግግር በሞኝነት ተጀምሮ በከባድ እብደት ይደመደማል።

14 ሞኝ ሰው ልፍለፋ ያበዛል። ወደፊት የሚሆነውን የሚያውቅ የለም፤ ሰው ከሞተ በኋላ የሚሆነውን ነገር የሚያስረዳው የለም።

15 ዕውቀት የጐደለው ሞኝ ሰው ወደ ከተማ መውጣት ስለሚሳነው በሥራው ይደክማል።

16 ሕፃን የሆነ ንጉሥና እየደገሱ ገና በማለዳ የሚሰክሩ መሳፍንት ያሉአት አገር ወዮላት

17 በጨዋነት ያደገ ንጉሥና ለስካር ሳይሆን ብርታትና ኀይል ለማግኘት ብቻ በተወሰነ ጊዜ የሚበሉና የሚጠጡ መሪዎች ያሉአት አገር የተባረከች ናት።

18 ሰው ቤቱን ከመጠገን ቸል ቢል ጣራው ይዘብጣል፤ ክዳኑም ያፈሳል።

19 በምግብና በወይን ጠጅ ተድላ ደስታ ይገኛል፤ ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ያለ ገንዘብ አይገኝም።

20 የሚሰማብኝ የለም ብለህ በስውር እንኳ ቢሆን ንጉሥን አትማ፤ በተኛህበት አልጋህ ላይ ሆነህም ባለጸጋን አትስደብ፤ ምሥጢርህን የሰሙ ነገር ጠላፊዎች ክንፍ እንዳለው ወፍ በረው ሊነግሩብህ ይችላሉ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios