Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዘዳግም 33 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ሙሴ የእስራኤልን ነገድ ሁሉ እንደ ባረከ

1 የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ ከመሞቱ በፊት የእስራኤልን ሕዝብ የባረከበት ቃለ በረከት ይህ ነው፦

2 ሙሴም እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር ከሲና ተራራ መጣ፤ ከኤዶም ላይ እንደ ንጋት ፀሐይ አበራ፤ ከፋራንም ተራራ ላይ አንጸባረቀ፤ በስተቀኙ የእሳት ነበልባል ነበር፤ ከእርሱም ጋር አእላፍ መላእክት ነበሩ።

3 እግዚአብሔር በእውነት ሕዝቡን ይወዳል፤ ቅዱሳኑን ሁሉ ይጠብቃል፤ እነርሱም በእግሩ ሥር ተንበርክከው ይሰግዳሉ፤ መመሪያውንም ይቀበላሉ፤

4 የእስራኤል ሕዝብ ርስት የሆነውን፥ ሙሴ የሰጠንን ሕግ ይጠብቃሉ።

5 የእስራኤል ነገዶችና የሕዝቡ መሪዎች በተሰበሰቡ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ነገሠ።”

6 ሙሴ ሰለ ሮቤል ነገድ እንዲህ አለ፦ “ምንም እንኳ ብዛቱ ጥቂት ቢሆን፥ ጌታ ሆይ የሮቤል ነገድ ይኑር እንጂ አይሙት።”

7 ስለ ይሁዳ ነገድም እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፥ የይሁዳን ነገድ ጩኸት ስማ፤ ከሌሎች ነገዶች ጋር እንዲተባበር አድርግ፤ የበረታ ኀይል ስጣቸው፤ ከጠላቶቻቸው ጋር በሚዋጉበት ጊዜ ርዳቸው።”

8 ስለ ሌዊም ነገድ እንዲህ አለ፦ “ጌታ ሆይ! በቱሚምና በዑሪም አማካይነት በማሳና በመሪባ ውሃ ዘንድ ተከራክረህ ለፈተንካቸው ለአገልጋዮችህ ለሌዋውያን ፈቃድህን ግለጥ።

9 እነርሱ ለአንተ ሲሉ ወላጆቻቸውን ረስተዋል፤ ከዘመዶቻቸው ተለይተዋል፤ ልጆቻቸውን ትተዋል፤ ቃልህን አክብረዋል። ቃል ኪዳንህንም ጠብቀዋል፤

10 ሥርዓትህን ለያዕቆብ፥ ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራሉ፤ በፊትህ ዕጣን ያጥናሉ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም በመሠዊያህ ላይ ያቀርባሉ።

11 አምላክ ሆይ! ሀብታቸውን ባርክ፤ የእጃቸውን ሥራ ተቀበል፤ የጠላቶቻቸውን ኀይል አድክም፤ የሚጠሉአቸውም ዳግመኛ እንዳያንሰራሩ አድርግ!”

12 ስለ ብንያምም ነገድ እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር የሚወደው ያለ ስጋት ይረፍ፤ ኀያሉ አምላክ ቀኑን ይጠብቀዋል። በእግዚአብሔር ጥበቃም ሥር ይኖራል።”

13 ስለ ዮሴፍም ነገድ እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር ከላይ በሰማይ በሚዘንብ ዝናብ፥ ከታችም ከጥልቀት በሚገኘው ውሃ፥ ምድራቸውን ይባርክ።

14 እንዲሁም በፀሐይ በበሰለ ምርጥ ፍሬ የተመላ ይሁን፤ በየወቅቱም ብዙ ምርት ይስጥ።

15 እንዲሁም ከጥንት የነበሩ ተራሮቻቸውና ከኮረብቶቻቸው በተትረፈረፈ ምርጥ ምርት የበለጸጉ ይሁኑ፤

16 ምድራቸው ምርጥ በሆነ ነገር ሁሉ የተመላ ይሁን፤ በሚቃጠለው ቊጥቋጦ ውስጥ ከተገለጠው አምላክ ጸጋ ይብዛለት። ከወንድሞቹ መካከል ግንባር ቀደም ለሆነው ልዑል ለዮሴፍ ይደረግለት።

17 የዮሴፍ ግርማ እንደ ኰርማ አስፈሪ ነው፤ ቀንዶቹም እንደ ጐሽ ቀንዶች ጠንካሮች ናቸው፤ በእነርሱም ሕዝቦችን ይወጋል፤ እስከ ምድር ዳርቻም ያባርራል፤ የኤፍሬም ዐሥር ሺሆች የምናሴም ሺሆች እንደዚያው ናቸው።”

18 ስለ ዛብሎን ስለ ይሳኮር ነገዶችም እንዲህ አለ፦ “ዛብሎን በመርከብ ስትጓዝ ደስ ይበልህ፤ ይሳኮርም በቤትህ ሆነህ ደስ ይበልህ።

19 ሕዝቦችን ወደ ተራራ ጠርተው እዚያ ትክክለኛ የሆነውን መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ ከባሕር ሀብትን፥ ከአሸዋም ድብቅ የሀብት ክምችትን ያገኛሉ።”

20 ስለ ጋድ ነገድም እንዲህ አለ፦ “የጋድን ግዛት ያሰፋ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ ጋድ ክንድን ወይም ግንባርን ለመስበር፥ እንደ አንበሳ ያደባል።

21 የመሪነት ድርሻ ስለ ተቀመጠለት፥ ለራሱ የተሻለውን መሬት መረጠ፤ የሕዝብ አለቆች በተሰበሰቡ ጊዜ የእግዚአብሔርን ፈቃድና ሥርዓቱን ለእስራኤል ፈጸመ።”

22 ስለ ዳንም ነገድ እንዲህ አለ፦ “ዳን እንደ አንበሳ ደቦል ነው፤ እርሱ ከባሳን ይዘላል።”

23 ስለ ንፍታሌም ነገድ እንዲህ አለ፦ “ንፍታሌም በጌታ ዘንድ በጣም ተወዳጅ ነው፤ በእግዚአብሔር በረከትም ተሞልቶአል፤ ግዛቱም እስከ ባሕሩና ወደ ደቡብ የተዘረጋ ነው።”

24 ስለ አሴር ነገድም እንዲህ አለ፦ “አሴር ከሌሎች ነገዶች ሁሉ ይበልጥ የተባረከ ይሁን፤ እርሱም በወንድሞቹ ዘንድ የተወደደ ይሁን፤ ምድሩም በወይራ ዛፍ የበለጸገች ትሁን።

25 የከተሞችህ በሮች በብረትና በናስ የተጠናከሩ ይሁኑ። በዘመንህ ሁሉ ኀይል ይኑርህ።”

26 የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በሰማያዊ ግርማው አንተን ለመርዳት በሰማይና በደመና ላይ እንደ እኛ አምላክ እንደ እግዚአብሔር ማንም የለም

27 ዘለዓለማዊ አምላክ መጠጊያህ ዘለዓለማዊ ክንዶቹ ደጋፊዎች ናቸው፤ ጠላትን ከፊትህ ያባርራል፤ እንድትደመስሳቸውም ያደርጋል።

28 ስለዚህ የያዕቆብ ዘሮች ከሰማይ ጠል በሚወርድባት፥ እህልና የወይን ጠጅ በሞላባት ምድር ዋስትና አግኝተው በሰላም ይኖራሉ።

29 እስራኤል ሆይ! የእርዳታህ ጋሻ፥ የድልህ ሰይፍ መዳንን ከእግዚአብሔር ያገኘ፥ እንዳንተ ያለ ሕዝብ ከቶ የለም፤ ምንኛ የታደልክ ነህ! ጠላቶች እየተለማመጡ ወደ አንተ ሲመጡ ጀርባቸውን ትረግጣለህ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios