Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዘዳግም 29 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እግዚአብሔር በሞአብ ምድር ለእስራኤል የሰጠው ቃል ኪዳን

1 እግዚአብሔር በሲና ካደረገው ቃል ኪዳን በተጨማሪ በሞአብ ምድር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር እንዲያደርግ ሙሴን ያዘዘው ተጨማሪ ቃል ኪዳን የሚከተለው ነው፦

2 ሙሴም የእስራኤልን ሕዝብ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እግዚአብሔር በግብጽ ንጉሥ፥ በመኳንንቱና በመላ ሀገሪቱ ላይ ያደረገውን ሁሉ፥

3 በእነርሱ ላይ ያደረሰባቸውን አሠቃቂ መቅሠፍት፥ የፈጸመውንም ተአምራትና ድንቅ ሥራ ሁሉ ራሳችሁ በዐይናችሁ አይታችኋል።

4 እግዚአብሔር ግን እስከ ዛሬይቱ ዕለት ድረስ ያለፋችሁበትን ሁኔታ የምታዩበት ዐይን፥ የምትሰሙበት ጆሮ፥ የምታስተውሉበት አእምሮ አልሰጣችሁም።

5 አርባ ዓመት ሙሉ በበረሓ ስመራችሁ ልብሳችሁ አላረጀም፤ ጫማችሁም አላለቀም።

6 አምላካችሁ እግዚአብሔር መሆኑን ታውቁ ዘንድ እንጀራ አልበላችሁም ወይን ወይም ጠንካራ መጠጥ አልጠጣችሁም።

7 ወደዚህም ስፍራ በደረስን ጊዜ፥ የሐሴቦን ንጉሥ ሲሖንና የባሳን ንጉሥ ዖግ ሊወጉን መጥተውብን ነበር፤ ነገር ግን እኛ ድል አደረግናቸው፤

8 ምድራቸውንም ወርሰን ለሮቤልና ለጋድ ነገዶች እንዲሁም ለእኩሌታ የምናሴ ነገድ ርስት እንዲሆን አከፋፍለን ሰጥተናል፤

9 ስለዚህም የምትሠሩት ነገር ሁሉ ይሳካላችሁ ዘንድ የዚህን ቃል ኪዳን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ፈጽሙ።

10-11 “እነሆ፥ ዛሬ እናንተ የየነገድ መሪዎቻችሁ፥ ሽማግሌዎቻችሁ፥ ሹሞቻችሁ፥ ሌሎችም የእስራኤል ወንዶች ሁሉና ልጆቻችሁ፥ ሴቶቻችሁ፥ በእናንተ ሰፈር ሆነው እንጨት የሚለቅሙላችሁና ውሃ የሚቀዱላችሁ መጻተኞች፥ ሁላችሁም በእግዚአብሔር አምላካችሁ ፊት ቆማችኋል።

12 የቆማችሁትም ከአምላካችሁ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ለመግባት ነው፤ ይህም ቃል ኪዳን እግዚአብሔር አምላካችሁ ዛሬ ለእናንተ በመሐላ ያረጋገጠው ነው።

13 እግዚአብሔር ይህን ያደረገው በሰጣችሁ ተስፋና ለአባቶቻችሁም ለአብርሃም፥ ለይስሐቅ፥ ለያዕቆብ በመሐላ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት እናንተን የራሱ ሕዝብ አድርጎ ሊመሠርታችሁ ነው።

14 እግዚአብሔር ይህን ሁሉ በመሐላ የጸና ቃል ኪዳን የሚያደርገውም ከእናንተ ጋር ብቻ አይደለም።

15 እርሱ ይህን ቃል ኪዳን የሚገባው ዛሬ በዚህ ስፍራ በፊቱ ከቆምነው ከእኛ ሁሉና ዛሬም ከእኛ ጋር እዚህ ከሌሉት ጋር ነው።

16 “በግብጽ ምድር እንዴት እንደ ኖርንና ባለፋችሁባቸውም ሕዝቦች መካከል እንዴት እንደ መጣን ታውቃላችሁ።

17 በመካከላቸው አጸያፊ የሆነውን፥ የእንጨት፥ የድንጋይ፥ የብርና የወርቅ ጣዖቶቻቸውን አይታችኋል።

18 በዚህ ከቆማችሁት መካከል ማንም ወንድ ወይም ሴት፥ ቤተሰብ ወይም ነገድ ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ፈቀቅ በማለት የሌሎችን ሕዝቦች አማልክት የሚከተል እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ በመካከላችሁ እንደዚህ ያለ መርዘኛና መራራ የሆነ ሥራ የሚሠራ አይኑር፤

19 እንደዚህ ያለው ሰው የዚህን ርግማን ቃላት ሰምቶ ምንም እንኳ በራሴ መንገድ ብቀጥል እኔ እድናለሁ ብሎ በልቡ ቢያስብ በደጎችና በክፉዎች ሰዎች ላይ ጥፋትን ያመጣል።

20 እግዚአብሔር ለእንደዚህ ያለው ሰው ይቅርታ አያደርግም፤ ይልቁንም የእግዚአብሔር ቊጣና ቅናት በእርሱ ላይ እንደ እሳት ይነዳል፤ እግዚአብሔርም እንደዚህ ያለውን ሰው ፈጽሞ እስኪደመስሰው ድረስ በዚህ መጽሐፍ የተጻፉት መቅሠፍቶች ሁሉ ይወርዱበታል።

21 እግዚአብሔር እንደዚህ ያለውን ሰው በዚህ የሕግ መጽሐፍ በተጻፈው የእርግማን ቃል ኪዳን መሠረት ከእስራኤል ነገዶች መካከል አውጥቶ ያጠፋዋል።

22 “በሚመጡት ትውልዶች፥ ዘሮቻችሁና ከሩቅ አገር የመጡ የውጪ አገር ሰዎች እግዚአብሔር በምድራችሁ ላይ ያመጣውን ጥፋትና በሽታ ያያሉ።

23 ምድሪቱም ሁሉ በዲንና በጨው ትሸፈናለች፤ ምንም ነገር አይተከልባትም፤ ምንም ነገር አታበቅልም፤ እግዚአብሔር በኀይለኛ ቊጣው እንደ ደመሰሳቸው እንደ ሰዶምና ገሞራ፥ እንደ አዳማና እንደ ጺባዮ ትሆናለች።

24 በዚያን ጊዜ የመላው ዓለም ሕዝብ እንዲህ ሲል ይጠይቃል፤ ‘እግዚአብሔር በዚህች ምድር ላይ ይህን ሁሉ ስለምን አደረገ? ለብርቱ ቊጣውስ ምክንያት የሆነው ነገር ምንድን ነው?’

25 መልሱም፦ ‘እነርሱ የቀድሞ አባቶቻቸው አምላክ ከግብጽ ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከእነርሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን በማፍረሳቸው ነው።

26 እነርሱ ከዚያ በፊት ሰግደውላቸው የማያውቁትንና እግዚአብሔርም እንዳይሰግዱላቸው የከለከላቸውን ባዕዳን አማልክትን ተከተሉ።

27 ስለዚህም እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ተቈጥቶ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ይህን መቅሠፍት ሁሉ በምድራቸው ላይ አወረደ።

28 እግዚአብሔርም በብርቱ ተቈጣ፤ ከብርቱ ቊጣውም የተነሣ ከምድራቸው ነቃቅሎ ወደ ባዕድ አገር እንዲሰደዱ አደረጋቸው። ስለዚህም እነሆ፥ ዛሬም በዚያው ይገኛሉ።’

29 “እግዚአብሔር አምላካችን ምሥጢር ያደረጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ፤ የተገለጡ ነገሮች ግን እኛና ልጆቻችን ልንጠብቃቸው የሚገባን የሕጉ ቃሎች ሁሉ ናቸው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios