ዘዳግም 28 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበመታዘዝ የሚገኝ በረከት ( ዘሌ. 26፥3-13 ፤ ዘዳ. 7፥12-24 ) 1 “ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ብትታዘዝና ዛሬ እኔ የምሰጥህንም ትእዛዞች ሁሉ በታማኝነት ብትጠብቅ፥ በምድር ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ 2 ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ታዘዝ፤ ከዚህ የሚከተሉት በረከቶች ሁሉ ባለቤት ትሆናለህ፤ 3 “እግዚአብሔር ከተሞችህንና እርሻዎችህን ይባርካል። 4 “እግዚአብሔር ልጆችህን፥ የምድር ፍሬህን፥ የቀንድ ከብትህን፥ የበግንና የፍየል መንጋህን ይባርክልሃል። 5 “እግዚአብሔር የእህል ሰብልህንና ቡሃቃህን ይባርካል። 6 “እግዚአብሔር መግባትህንና መውጣትህን ይባርክልሃል፤ 7 “ጠላቶችህ በአንተ ላይ አደጋ በሚጥሉበት ጊዜ እግዚአብሔር እነርሱን ድል ያደርግልሃል፤ በአንድ አቅጣጫ ይመጡብሃል፤ ነገር ግን በሰባት አቅጣጫ ይሸሻሉ። 8 “እግዚአብሔር አምላክህ ጐተራህንና የእጅህን ሥራ ሁሉ ይባርክልሃል፤ እንዲሁም በሚሰጥህ ምድር ይባርክሃል። 9 “ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ብትታዘዝና ትእዛዞቹንም ሁሉ ብትፈጽም በተስፋ ቃሉ መሠረት ለራሱ የለየህ ወገን ያደርግሃል። 10 ከዚያን በኋላ በምድር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ የእግዚአብሔር ወገን መሆንክን አይተው ይፈሩሃል። 11 እግዚአብሔር ለአንተ ይሰጥህ ዘንድ ለቀድሞ አባቶችህ በማለላቸው ምድር ብዙ ልጆችን፥ ብዙ የቀንድ ከብትና የተትረፈረፈ የእርሻን ሰብል ይሰጥሃል፤ 12 በሰማይ ካለው ክምችት ዝናብን በወቅቱ ይልክልሃል፤ የእጅህንም ሥራ ይባርካል፤ ስለዚህም ለብዙ ሕዝቦች ታበድራለህ፤ አንተ ግን ከማንም አትበደርም፤ 13 አምላክህ እግዚአብሔር በብዙ ሕዝቦች መካከል እንደ ራስ መሪ ያደርግሃል እንጂ እንደ ጅራት ወደ ኋላ እንድትቀር አያደርግህም፤ ዛሬ እኔ የምሰጥህን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች በታማኝነት ብትፈጽም ምንም ዐይነት ውድቀት ሳይደርስብህ ወደፊት ትገሠግሣለህ እንጂ ወደ ኋላ አትቀርም፤ 14 በማናቸውም ሁኔታ ከእነዚህ ትእዛዞች በመውጣት ለባዕዳን አማልክት መስገድና እነርሱን ማገልገል አይገባህም። አለመታዘዝ የሚያስከትለው መርገም ( ዘሌ. 26፥14-46 ) 15 “ነገር ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ባትታዘዝና እኔ ዛሬ የምሰጥህንም ሕጎችና ትእዛዞች በታማኝነት ባትጠብቅ ከዚህ የሚከተለው መርገም ሁሉ ይደርስብሃል፦ 16 “በከተማም፥ በገጠርም የተረገምክ ትሆናለህ። 17 “የእህል ሰብልህና ቡሃቃህ የተረገመ ይሆናል። 18 “ልጆችህ፥ የምድርህ ፍሬ፥ የከብት፥ የበግና የፍየል መንጋህ የተረገመ ይሆናል። 19 “ስትገባና ስትወጣ የተረገምህ ትሆናለህ። 20 “ክፉ ነገር በማድረግ እግዚአብሔርን ስለ ተውክ በምታደርገው ነገር ሁሉ ፈጽመህ እስክትጠፋ ድረስ እርግማንን፥ ሁከትንና ውርደትን ያመጣብሃል። 21 ልትወርሳት ከምትገባባት ምድር ጨርሶ እስኪያጠፋህ የማይለቅህን ቀሣፊ በሽታ እግዚአብሔር ያመጣብሃል። 22 እግዚአብሔር በሚያመነምን በሽታ፥ በትኲሳት፥ በቊስል፥ በኀይለኛ ሙቀትና በድርቅ እስክትጠፋም ድረስ ይመታሃል። ሰብልህንም ለማጥፋት ዋግና አረማሞ ይልክብሃል። 23 ሰማይን ከራስህ በላይ እንደ ነሐስ አጠጥሬ ዝናብ እንዳይዘንብ አደርጋለሁ፤ ምድርንም በድርቅ መትቼ እንደ ብረት የጠነከረች አደርጋለሁ። 24 በዝናብ ፈንታ እስክትጠፋ ድረስ እግዚአብሔር በአንተ ላይ በዐውሎ ነፋስ የሚነዳ ትቢያና አሸዋ ይልክብሃል። 25 “እግዚአብሔር ለጠላቶችህ በአንተ ላይ ድልን ይሰጣቸዋል፤ በአንድ በኩል ትመጣባቸዋለህ፤ ነገር ግን ከእነርሱ ለማምለጥ በሰባት አቅጣጫ ትሸሻለህ፤ በምድር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ በአንተ ላይ የሚደርሰውን ነገር በሚያዩበት ጊዜ በፍርሃት ይሸበራሉ፤ 26 በምትሞትበትም ጊዜ ወፎችና የምድረ በዳ አራዊት ሥጋህን ይበሉታል፤ የሚያባርራቸውም አይኖርም፤ 27 እግዚአብሔር ልትድን በማትችልበት በግብጻውያን የእባጭ በሽታ፥ በኀይለኛ የጨጓራ በሽታ፥ በቊስልና በሚያሳክክ በሽታ ይመታሃል፤ 28 እግዚአብሔር አእምሮ በሚያሳጣ እብደትና ዕውርነት ይመታሃል። 29 በእኩለ ቀን እንደ ዕውር ትደናበራለህ፤ የምትሄድበትንም መንገድ ማግኘት አትችልም፤ የምትሠራውም ነገር ሁሉ አይሳካልህም፤ ዘወትር ጭቈናና ምዝበራ ይደርስብሃል፤ የሚረዳህም ሰው አታገኝም። 30 “ልጃገረድ ለማግባት ታጫለህ፤ ነገር ግን ሌላ ሰው ይደፍራታል፤ ቤት ትሠራለህ፤ ነገር ግን አትኖርበትም፤ ወይን ትተክላለህ፤ ነገር ግን በፍሬው አትጠቀምበትም። 31 ከብትህ በፊትህ፥ ዐይንህ እያየ ይታረዳል፤ ነገር ግን ከሥጋው አትቀምስም፤ አህዮችህ በፊትህ ተስበው ይወሰዳሉ፤ ነገር ግን አይመለሱልህም፤ በጎችህ ለጠላቶችህ ተላልፈው ይሰጣሉ፤ እነርሱን ለማዳን የሚረዳህም የለም፤ 32 ዐይንህ እያየ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ለባዕዳን ይሰጣሉ፤ የልጆችህን መመለስ በከንቱ በመጠባበቅ ዐይንህ ሲንከራተት ይኖራል፤ ነገር ግን ምንም ለማድረግ አትችልም። 33 በከባድ ሁኔታ የደከምክበትን የእህልህን ሰብል የማታውቀው ሕዝብ ይበላዋል፤ አንተ ግን በዘመንህ ሁሉ ግፍና ጭቈና በቀር የሚተርፍህ ነገር የለም። 34 የምታያቸው ትርኢቶች ያሳብዱሃል፤ 35 እግዚአብሔር ቅልጥምህንና ጭንህን በማይፈወስ ቊስል እንዲሸፈን ያደርጋል፤ ብርቱ ቊስልና እባጭ ከራስ ጠጒርህ እስከ እግር ጥፍርህ ይሸፍንሃል። 36 “እግዚአብሔር አንተንና ንጉሥህን ከዚህ በፊት የቀድሞ አባቶችህም ሆኑ አንተ ወዳልነበራችሁበት ባዕድ አገር አፍልሶ ይወስዳችኋል፤ በዚያም ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ ባዕዳን አማልክትን ታመልካላችሁ። 37 እግዚአብሔር በሚበትንህ አገሮች የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ በአንተ ላይ የደረሰውን ነገር አይተው ይደነግጣሉ፤ መቀለጃና መዘባበቻም ያደርጉሃል። 38 “የእህልህን ሰብል አንበጣ ስለሚበላው ብዙ እህል ዘርተህ ጥቂት መከር ብቻ ትሰበስባለህ፤ 39 የወይኑን ሐረግ ትል ስለሚበላው ወይን ተክለህ ትንከባከበዋለህ፤ ነገር ግን የወይን ዘለላ ሰብስበህ አትበላም፤ ወይም ከእርሱ የወይን ጠጅ አትጠጣም፤ 40 የወይራ ዛፍ በምድርህ በየስፍራው ይበቅላል፤ ነገር ግን የወይራው ፍሬ ያለ ጊዜው ስለሚረግፍ የወይራ ዘይት አይኖርህም። 41 ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትወልዳለህ፤ ነገር ግን የጦር ምርኮኞች ሆነው ስለሚወሰዱ ታጣቸዋለህ፤ 42 ዛፎችህንና የእርሻ ሰብልህን ሁሉ ኲብኲባ ይበላዋል። 43 “የአንተ ኀይል እየደከመ ሲሄድ፥ በምድርህ የሚኖሩ የመጻተኞች ኀይል ግን ይበረታል። 44 መጻተኞች ለአንተ ገንዘብ አበዳሪዎች ይሆናሉ፤ አንተ ግን ለእነርሱ የምታበድራቸው ገንዘብ አይኖርህም፤ በመጨረሻም እነርሱ እንደ ራስ መሪ ይሆናሉ፤ አንተ ግን እንደ ጅራት ወደ ኋላ ትቀራለህ። 45 “አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ታዛዥ ሆነህ ስላልተገኘህና እርሱ የሰጠህን ደንቦችና ትእዛዞች ስላልጠበቅህ እነዚህ ሁሉ መቅሠፍቶች ይመጡብሃል፤ ፈጽሞ እስከምትደመሰስ ድረስ ከአንተ አይርቁም፤ 46 እነዚህም ሁሉ እግዚአብሔር በአንተና በዘሮችህ ላይ የሰጠውን የቅጣት ፍርድ ለዘለዓለም ሲያስታውሱ የሚኖሩ ምልክቶች ይሆናሉ። 47 እግዚአብሔር በብዙ መንገድ ባርኮህ ነበር፤ አንተ ግን ደስታና ሐሴት በተሞላበት ልብ ሆነህ አላገለገልከውም፤ 48 ስለዚህም ከእንግዲህ ወዲህ እግዚአብሔር በአንተ ላይ ለሚልካቸው ለጠላቶችህ አገልጋይ ትሆናለህ። በሁሉ ነገር በመቸገርም ትራባለህ፤ ትጠማለህ፤ ትታረዛለህ። ፈጽሞ እስክትጠፋ ድረስ እግዚአብሔር አንተን በጠላቶችህ እንደ ብረት በጠነከረ የአገዛዝ ቀንበር በብርቱ እንድትጨቈን ያደርጋል። 49 እግዚአብሔር ቋንቋቸውን የማታውቀውን የሕዝቦች ሠራዊትን ከሩቅ ምድር ያመጣብሃል፤ እነርሱም እንደ ንስር በአንተ ላይ ይወርዱብሃል፤ 50 እነርሱ ሽማግሌውን የማያከብሩ፥ ለሕፃንም የማይራሩ ጨካኞች ይሆኑብሃል፤ 51 እነርሱ ከብትህንና ሰብልህን ሁሉ ጠራርገው ስለሚበሉት እስክትሞት ድረስ በራብ ትቸገራለህ። እነርሱ አንተ እስክትጠፋ ድረስ ከእህልህ አንዲት ፍሬ፥ ከከብትህ ጥጃ፥ ከበጎችህ መንጋ ጠቦት ከወይንህና ከወይራ ዛፍህ ቅንጣት ፍሬ እንኳ አያስተርፉልህም። 52 እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር የሚገኙትን መኖሪያ ከተሞችህን ሁሉ ይከባሉ፤ አንተ የምትተማመንባቸውን ከፍተኞች የሆኑ ቅጽሮች ያሉአቸውን ምሽጎችህን ሁሉ ይደመስሳሉ። 53 “ጠላቶችህ ከተሞችህን ከበው በሚያስጨንቁህም ጊዜ፥ የምትበላው አጥተህ ግራ ሲገባህ እግዚአብሔር አምላክህ የሰጠህንና የሆድህ ፍሬዎች የሆኑትን ወንዶችና ሴቶች ልጆችህን ሥጋ ለመብላት ትገደዳለህ፤ 54 በመካከላችሁ በመለሳለስና በቅምጥልነት በትውልዱም በመመካት የሚኖረው ሰው እንኳ ለወንድሙ፥ ዐቅፋው ለምትተኛው ሚስቱና ከጥፋት ለተረፉት ልጆቹ ከዚያ ምግብ ለመስጠት ይሰስታል። 55 በዚያ ተስፋ በሚያስቈርጠው በከተሞችህ ሁሉ ላይ በሚደረገው በጠላት ከበባ ወቅት ሌላ ምንም የሚበላው ነገር ስለሌለው ከሚበላው ከልጆቹ ሥጋ ለማናቸውም አይሰጥም። 56 በመለሳለስና በቅምጥልነት በመካከልህ የምትኖር በትውልድዋ የምትመካና ከመለስለስዋ ብዛት እግሮችዋ መሬት ረግጠው የማያውቁ ዐቅፋው ከምትተኛው ባልዋና ከልጆችዋ ትሰስታለች። 57 በዚያ ተስፋ በሚያስቈርጠው፥ በከተሞችህ ሁሉ ላይ በሚደረገው የጠላት ከበባ ወቅት ሌላ ምንም የሚበላ ነገር ስለሌላት በምሥጢር ከምትበላቸው ከማሕፀንዋ ከወጡ ልጆችዋና ከእንግዴልጅዋ ለማንም አትሰጥም። 58 “በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን የእግዚአብሔርን ሕግ ቃላት በጥንቃቄ ባትፈጽሙ፥ አስደናቂና አስፈሪ የሆነውን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ስም ባታከብሩ፥ 59 እግዚአብሔር በአንተና በልጆችህ ላይ አስፈሪ፥ ለብዙ ጊዜ የሚቈይ መቅሠፍትና ከባድ የማይድን በሽታ ያመጣብሃል። 60 በግብጽ ምድር ላይ በወረደ ጊዜ አይተህ ትፈራው የነበረውን ያን አሠቃቂ በሽታ ሁሉ እንደገና በአንተ ላይ ይልካል፤ ከዚያም ደዌ አትፈወስም፤ 61 የእግዚአብሔር ሕግ በተጻፉበት በዚህ መጽሐፍ ያልተጠቀሱ በሽታዎችንና መቅሠፍቶችን ሁሉ እስክትጠፋ ድረስ ይልክብሃል። 62 ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ታዛዦች ሆናችሁ ስላልተገኛችሁ ብዛታችሁ እንደ ሰማይ ከዋክብት ከነበራችሁት ከእናንተ ጥቂቶቹ ብቻ ይተርፋሉ፤ 63 እግዚአብሔር እናንተን ለማበልጸግና ቊጥራችሁንም ለማብዛት እንደ ወደደው ሁሉ እንደገናም እናንተን በማጥፋትና በመደምሰስ ደስ ይለዋል። ከዚህች ከምትወርሱአት ምድር ተነቃቅላችሁ ትጠፋላችሁ። 64 “እግዚአብሔር በመላው ዓለም በሕዝቦች መካከል ከአንድ የምድር ዳርቻ እስከ ሌላው ድረስ ይበትንሃል፤ በዚያም አንተም ሆንክ የቀድሞ አባቶችህ ሰግዳችሁላቸው የማታውቁትን ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን ባዕዳን አማልክት ታመልካለህ። 65 በእነዚያ ሕዝቦች መካከል ዕረፍትና ለእግርህ ማሳረፊያ ቦታ አይኖርህም፤ እግዚአብሔርም የባባ ልብ፥ በናፍቆት የፈዘዘ ዐይን፥ ተስፋ የቈረጠ ስሜት ይሰጥሃል። 66 ሕይወትህ ዘወትር በጭንቀት ላይ ይሆናል፤ የመኖር ዋስትናህም የተረጋገጠ ባለመሆኑ ቀንና ሌሊት በፍርሃት ትዋጣለህ። 67 ልብህን በሚሞላው ፍርሀትና በዐይንህ በምታየው አስደንጋጭ ትርኢት ምክንያት፥ ሲነጋ መቼ በመሸልኝ፥ ሲመሽም መቼ በነጋልኝ ትላለህ። 68 እግዚአብሔር ‘ዳግመኛ ተመልሰህ ወደዚያ አትሄድም’ ብሎ የተናገረ ቢሆንም እንኳ በመርከብ ተሳፍረህ ወደ ግብጽ እንድትመለስ ያደርጋል፤ በዚያም ራስህን ለጠላቶችህ ባሪያ አድርገህ መሸጥ ትፈልጋለህ፤ ነገር ግን ባሪያ አድርጎ ለመግዛት የሚፈልግህ እንኳ አታገኝም።” |