Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዘዳግም 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የእስራኤል ሕዝብ ከሲና ተነሥተው እንዲጓዙ የተሰጠ መመሪያ

1 ከዮርዳኖስ ማዶ አራባ በሚባል ምድረ በዳ በሱፍ ፊት ለፊት በአንድ በኩል ፋራን፥ በሌላ በኩል ጦፌል፥ ላባን፥ ሐጼሮትና ዲዛሃብ መካከል ሳሉ ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገው ንግግር ይህ ነው።

2 ከሲና ተራራ ተነሥቶ በኤዶም ተራራ በኩል ወደ ቃዴስ በርኔ ለመድረስ ዐሥራ አንድ ቀን ይፈጃል።

3 ግብጽን ለቀው ከወጡ በኋላ አርባኛው ዓመት በገባ በዐሥራ አንደኛው ወር መጀመሪያ ቀን ሙሴ ለሕዝቡ ያስረዳቸው ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘውን ቃል ሁሉ ነገራቸው።

4 ይህም የሆነው በሐሴቦን ከተማ ነግሦ ይገዛ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሲሖንንና በዐስታሮትና በኤድረዒ ከተሞች ሆኖ ይገዛ የነበረውን የባሳንን ንጉሥ ዖግን ድል ካደረገ በኋላ ነው።

5 ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ በሞአብ ምድር ሙሴ የሚከተለውን የእግዚአብሔር ሕግ እንዲህ እያለ መግለጥ ጀመረ፤

6 “በሲና ተራራ ላይ በነበርንበት ጊዜ እግዚአብሔር አምላካችን እንዲህ አለን፦ ‘እነሆ፦ በዚህ ተራራ ላይ ለረጅም ጊዜ ቈይታችኋል፤

7 ሰፈራችሁን ነቅላችሁ ወደ ተራራማው የአሞራውያን አገር፥ ወደ ጐረቤትም ወደ አራባ በደጋውና በቈላው አገር፥ በኔጌብ፥ በሜዲቴራኒያን ባሕር ጠረፍ በኩል፥ በከነዓናውያን አገርና በሊባኖስ በኩል አድርጋችሁ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ሂዱ።

8 እነሆ፥ ምድሪቱ በፊታችሁ ናት፤ እኔ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻችሁ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ፥ እንዲሁም ለዘሮቻቸው ላወርሳቸው የተስፋ ቃል የገባሁላቸውን ምድር ሄዳችሁ ውረሱ።’ ”


ሙሴ የሕዝብ መሪዎችን መሾሙ
( ዘፀ. 18፥13-27 )

9 ሙሴ ለሕዝቡ እንዲህ አለ፤ “ገና በሲና ተራራ በነበርንበት ጊዜ እንዲህ ስል ነግሬአችሁ ነበር፤ ‘እናንተን የመምራት ኀላፊነት ለእኔ ይበዛብኛል፤ ይህን ሁሉ ብቻዬን ላደርግ አልችልም፤

10 እግዚአብሔር አምላካችሁ ቊጥራችሁን አብዝቶአል፤ እነሆ፥ አሁን ቊጥራችሁ እንደ ሰማይ ከዋክብት ብዙ ነው፤

11 አሁንም የቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ሺህ ጊዜ እጥፍ በመጨመር ቊጥራችሁን አብዝቶ ያበልጽጋችሁ!

12 ነገር ግን በመካከላችሁ የሚነሣውን ጠብና ክርክር ለማስወገድ ይህን ከባድ ኀላፊነት ብቻዬን እንዴት ልሸከም እችላለሁ?

13 ከእያንዳንዱ ነገድ የማስተዋል ጥበብ ያላቸውንና የሥራ ልምድ ያላቸውን ሰዎች ምረጡ፤ እኔም በእናንተ ላይ እሾማቸዋለሁ።’

14 እናንተም ‘ያቀረብከው ሐሳብ መልካም ነው’ ብላችሁ መልስ ሰጥታችሁኝ ነበር፤

15 ስለዚህም ከእያንዳንዱ ነገድ የመረጣችኋቸውን የሥራ ልምድ ያላቸውን ዐዋቂዎች መሪዎች ተቀብዬ ሾምኩላችሁ። ከእነርሱም አንዳንዶቹ የሺህ አለቆች፥ አንዳንዶቹ የመቶ አለቆች፥ አንዳንዶቹም የኀምሳና የዐሥር አለቆች ሆነው የተሾሙ ነበሩ። ለነገዶችም ሁሉ ሌሎችንም ሹማምንት ሾምኩ።

16 “በዚያን ጊዜ እነርሱን እንዲህ ብዬ ነገርኳቸው፤ ‘በሕዝባችሁ መካከል የሚነሣውን የጠብና የክርክር አቤቱታ አድምጡ፤ በራሳችሁ ሕዝብ ወይም በእናንተ ውስጥ በሚኖሩት መጻተኞች መካከል ስለሚነሣው ጠብና ክርክር ሁሉ በትክክል ፍረዱ።

17 በምትሰጡትም ውሳኔ አድልዎ አታድርጉ፤ ስለ ማንኛውም ታላቅም ሆነ ታናሽ ሰው ያለ አድልዎ በእኩልነት ፍረዱ። ፍርድ የእግዚአብሔር ስለ ሆነ ማንንም አትፍሩ፤ ለእናንተ የሚከብድባችሁ ነገር ቢኖር ወደ እኔ አምጡት፤ እኔም ውሳኔ እሰጥበታለሁ፤’

18 እናንተም ልታደርጉት ስለሚገባው ነገር ሁሉ በዚያኑ ጊዜ ነገርኳችሁ።


ከቃዴስ በርኔ ሰላዮች ወደ ተስፋይቱ ምድር መላካቸው
( ዘኍ. 13፥1-33 )

19 “ከዚያም እግዚአብሔር አምላካችን እንዳዘዘን ከሲና ተነሥተን እናንተ ባያችሁት አስቸጋሪ በረሓ በተራራማው በአሞራውያን አገር በኩል አድርገን ወደ ቃዴስ በርኔ መጣን።

20 እንዲህ ብዬ ነገርኳችሁ፤ ‘እግዚአብሔር ሊያወርሰን የተሰፋ ቃል ወደገባልን ኮረብታማ ወደሆነችው ወደ አሞራውያን ምድር እነሆ፥ ደርሳችኋል፤

21 ተመልከቱ፤ አገሪቱ ይህችውላችሁ፤ የቀድሞ አባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔርም ባዘዘው መሠረት ገብታችሁ ውረሱአት፤ በመፍራትም ተስፋ አትቊረጡ።’

22 “ነገር ግን እናንተ ወደ እኔ መጥታችሁ ‘ምድሪቱን የሚሰልሉ ሰዎችን በፊታችን እንላክ፤ እነርሱም ወደዚያች ምድር የሚያደርሰንን ትክክለኛ መንገድና ምን ዐይነት ከተሞችም እንዳሉ አጥንተው ሊነግሩን ይችላሉ’ አላችሁኝ።

23 “ይህንንም ማድረግ መልካም መስሎ ስለ ታየኝ ከእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ሰው በመምረጥ ዐሥራ ሁለት ሰዎችን ላክሁ።

24 እነርሱም ኮረብታማ ወደሆነችው አገር ዘልቀው በመግባት እስከ ኤሽኮል ሸለቆ ተዘዋውረው አጠኑአት።

25 በዚያም ካገኙት ፍሬ ጥቂቱን ይዘውልን መጡ፤ እግዚአብሔር አምላካችን ሊሰጠን ያቀዳት ምድር እጅግ ለም መሆንዋንም አስረዱን።

26 “ነገር ግን እናንተ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ በማመፅ ወደዚያች ምድር መግባትን አልወደዳችሁም።

27 እርስ በርሳችሁም እንዲህ ብላችሁ አጒረመረማችሁ፤ ‘እግዚአብሔር ጠልቶናል፤ ከግብጽ ምድርም ያወጣን እነዚህ አሞራውያን ይገድሉን ዘንድ በእጃቸው አሳልፎ ሊሰጠን ፈልጎ ነው፤

28 ታዲያ እዚያ የምንሄደው ለምንድን ነው? እንፈራለን፤ የላክናቸውም ሰዎች በዚያ የሚኖሩት ሁሉ ብርቱዎችና በቁመታቸውም ከእኛ ይበልጥ ረጃጅሞች መሆናቸውን፥ እንዲሁም ርዝመታቸው እስከ ሰማይ የሚደርስ የግንብ ቅጽሮች ባሉአቸው ከተሞች የሚኖሩ መሆናቸውን ነገሩን፤ እጅግ ግዙፋን የሆኑ የዔናቅ ልጆችንም አይተዋል።’

29 “ነገር ግን እኔ እንዲህ ብዬ ነገርኳችሁ፤ ‘ከእነዚህ ሕዝብ የተነሣ አትፍሩ፤ አትሸበሩም፤

30 በዓይናችሁ እያያችሁ በግብጽ እንዳደረገላችሁ ለእናንተ የሚዋጋው በፊታችሁ የሚሄደው አምላካችሁ እግዚአብሔር ነው።

31 እናንተ ወደዚህ ቦታ እስክትመጡ ድረስ አንድ ሰው ልጁን እንደሚንከባከብ በሄዳችሁበት መንገድ ሁሉ አምላካችሁ እግዚአብሔር በምድረ በዳው እንደ ተንከባከባችሁ አይታችኋል።’

32-33 ይህም ሆኖ የምትሰፍሩበትን ቦታ ለመፈለግና የምትሄዱበትን መንገድ ለማሳየት ቀን በደመና ሌሊት በእሳት፥ በፊታችሁ በሚሄደው በአምላካችሁ በእግዚአብሔር አልተማመናችሁም።


እግዚአብሔር እስራኤላውያንን መቅጣቱ
( ዘኍ. 14፥20-45 )

34 “እግዚአብሔርም የማጒረምረም ጩኸታችሁን ሰምቶ ተቈጣ፤ ስለዚህም እንዲህ ሲል ማለ፤

35 ‘እኔ ለቀድሞ አባቶቻችሁ አወርሳታለሁ ብዬ የተስፋ ቃል ወደገባሁባት ወደዚያች ለም ምድር ከዚህ ክፉ ትውልድ መካከል አንዳችሁም አትገቡባትም።

36 ወደዚያች ምድር መግባት የሚችል የይፉኔ ልጅ ካሌብ ብቻ ነው፤ እርሱ በፍጹም ልቡ ታማኝ ሆኖ ስለ ተገኘ ያቺን የጐበኛትን ምድር ለእርሱና ለዘሮቹ እሰጣለሁ።’

37 በእናንተው ምክንያት እግዚአብሔር በእኔም ላይ እንኳ ተቈጥቶ እንዲህ አለኝ፤ ‘ሙሴ፥ አንተም ራስህ እንኳ ወደዚያች ምድር አትገባም፤

38 ነገር ግን የአንተ ረዳት የሆነው የነዌ ልጅ ኢያሱ ወደ ምድሪቱ ይገባል፤ ምድሪቱን ይወርሱ ዘንድ እስራኤልን የሚመራ እርሱ ስለ ሆነ አበረታታው።’

39 “ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ለሁላችንም እንዲህ አለ፤ ‘በጠላቶቻችን ይማረካሉ ያላችኋቸው ሕፃናትና ክፉና ደጉን ለይተው የማያውቁ ልጆቻችሁ ብቻ ወደዚያች ምድር ይገባሉ፤ ምድሪቱን ለእነርሱ እሰጣለሁ፤ እነርሱ ይወርሱአታል።

40 እናንተ ግን ወደ ቀይ ባሕር የሚወስደውን መንገድ በመከተል ወደ በረሓው ተመልሳችሁ ሂዱ።’

41 “እናንተም ‘ሙሴ ሆይ፥ እኛ እግዚአብሔርን በድለናል፤ አሁን ግን አምላካችን እግዚአብሔር ባዘዘን መሠረት እንዋጋለን’ ብላችሁ መለሳችሁ፤ ኮረብታማይቱን አገር መውረር ቀላል መስሎአችሁ ከእናንተ እያንዳንዱ ለውጊያ ተዘጋጀ።

42 “እግዚአብሔር ግን ‘እኔ ከእናንተ ጋር ስለማልሆን ለመዋጋት አትውጡ፤ ይህ ካልሆነ ጠላቶቻችሁ ድል ይመቱአችኋል’ በላቸው አለኝ።

43 እግዚአብሔር ያለኝንም ለእናንተ ነገርኳችሁ፤ እናንተ ግን እምቢተኞች ሆናችሁ፤ በእርሱም ላይ ዐምፃችሁ በትዕቢታችሁ ብዛት ወደ ኮረብታማይቱ አገር ዘመታችሁ፤

44 በነዚያ ኮረብታዎች ላይ የሚኖሩ አሞራውያንም መጥተው ተጋጠሙአችሁ፤ ሠራዊታቸውም እንደ ንብ መንጋ ግር ብለው መጥተው እስከ ሆርማ ድረስ አሳደዱአችሁ፤ ኮረብታማ በሆነችው በኤዶም አገርም ድል አደረጉአችሁ።

45 ስለዚህም ይረዳችሁ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር በመጮኽ አለቀሳችሁ፤ ነገር ግን ጩኸታችሁን ሊያዳምጥና ሊረዳችሁ አልወደደም።

46 ስለዚህም በቃዴስ ለረጅም ጊዜ ቈያችሁ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios