Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ሐዋርያት ሥራ 25 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ጳውሎስ ወደ ሮም ንጉሠ ነገሥት ይግባኝ ማለቱ

1 ፊስጦስ ወደ ግዛቱ ወደ ቂሣርያ ገብቶ ሦስት ቀን ከቈየ በኋላ ከዚያ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ።

2-3 እዚያም የካህናት አለቆችና አንዳንድ ታላላቅ የአይሁድ ወገኖች በጳውሎስ ላይ ክሳቸውን አቀረቡ፤ “ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም በማስመጣት ለእኛ መልካም ነገር አድርግልን” ሲሉም ለመኑት፤ ይህንንም ያሉበት ምክንያት ጳውሎስን በመንገድ ጠብቀው ሊገድሉት ስለ ፈለጉ ነው።

4 ፊስጦስ ግን “ጳውሎስ በቂሳርያ በእስር ቤት እየተጠበቀ ነው፤ እኔም አሁን በቶሎ ተመልሼ ወደዚያ እሄዳለሁ፤

5 ባለሥልጣኖቻችሁ ከእኔ ጋር ወደ ቂሳርያ ይሂዱ፤ ጳውሎስ ያደረገው በደል ካለ እዚያ ይክሰሱት” አላቸው።

6 ፊስጦስ ከስምንት ወይም ከዐሥር ቀኖች ያልበለጠ ጊዜ ከእነርሱ ጋር ካሳለፈ በኋላ ወደ ቂሳርያ ሄደ፤ እዚያ በደረሰ ጊዜ በማግስቱ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀመጠና ጳውሎስን እንዲያቀርቡት አዘዘ።

7 ጳውሎስ በቀረበ ጊዜ ከኢየሩሳሌም የመጡት አይሁድ ከበውት ቆሙና ማስረጃ ሊያገኙለት የማይችሉትን ብዙ ከባድ ክስ አቀረቡበት፤

8 ጳውሎስም “እኔ በአይሁድ ሕግ ላይም ሆነ በቤተ መቅደስ ወይም በሮም ንጉሠ ነገሥት ላይ ያደረግኹት በደል የለም” ሲል የመከላከያ መልሱን ሰጠ።

9 ፊስጦስ ግን አይሁድን ደስ ለማሰኘት ፈልጎ ጳውሎስን “ወደ ኢየሩሳሌም ሄደህ ስለዚህ ጉዳይ እዚያ በእኔ ፊት ልትፋረድ ትፈልጋለህን?” አለው።

10 ጳውሎስ ግን እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፤ “እነሆ! እኔ ልፋረድበት በሚገባኝ በሮም ንጉሠ ነገሥት የፍርድ ወንበር ፊት ቆሜአለሁ፤ አንተም በደንብ እንደምታውቀው በአይሁድ ላይ ያደረግኹት ምንም በደል የለም፤

11 በደለኛ ከሆንኩ ወይም በሞት የሚያስቀጣ በደል ካደረግሁ ከሞት ልዳን አልልም፤ ነገር ግን የእነርሱ ክስ ከንቱ ከሆነ ማንም ለእነርሱ አሳልፎ ሊሰጠኝ አይችልም፤ እኔ ወደ ሮማ ንጉሠ ነገሥት ይግባኝ ብዬአለሁ።”

12 በዚያን ጊዜ ፊስጦስ ከአማካሪዎቹ ጋር ተነጋገረና “ወደ ሮማ ንጉሠ ነገሥት ይግባኝ ካልክ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ትሄዳለህ” አለው።


ጳውሎስ በአግሪጳና በበርኒቄ ፊት መቅረቡ

13 ከጥቂት ቀን በኋላ ንጉሥ አግሪጳና በርኒቄ ፊስጦስን “እንኳን ደኅና መጣህ” ለማለት ወደ ቂሳርያ መጡ።

14 እዚያም ብዙ ቀን በመቀመጣቸው ፊስጦስ የጳውሎስን ጉዳይ እንዲህ ሲል ለንጉሥ አግሪጳ ገለጠ፤ “ፊልክስ አስሮ የተወው እዚህ አንድ ሰው አለ፤

15 እኔ በኢየሩሳሌም በነበርኩበት ጊዜ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች የዚህን ሰው ጉዳይ ካመለከቱኝ በኋላ እንድፈርድበት ጠየቁኝ።

16 እኔ ግን ‘ተከሳሽ ከከሳሾች ፊት ቆሞ ለተከሰሰበት ነገር የመከላከያ መልስ ሳይሰጥ ተከሳሹን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሥርዓት አይደለም’ ብዬ መለስኩላቸው።

17 ስለዚህ ከሳሾቹ ተሰብስበው ወደዚህ በመጡ ጊዜ ሳልዘገይ በማግስቱ በፍርድ ወንበር ተቀመጥሁና ጳውሎስን በፊቴ እንዲያቀርቡት አዘዝኩ፤

18 ከሳሾቹም ለመናገር አጠገቡ በቆሙ ጊዜ እኔ ክፉ ነገር ሠርቶአል ብዬ የገመትኩትን ያኽል ለክስ የሚያበቃ ምንም ነገር አላቀረቡበትም።

19 ነገር ግን ከእርሱ ጋር ይከራከሩበት የነበረው ስለ ሃይማኖታቸውና ሞቶ ስለ ነበረው ጳውሎስ ግን ‘ሕያው ነው’ ስለሚለው ኢየሱስ ነው።

20 እኔም እንዲህ ዐይነቱን ነገር መመርመር ስለ ቸገረኝ ጳውሎስን ‘ወደ ኢየሩሳሌም ሄደህ እዚያ በዚህ ነገር ልትፋረድ ትወዳለህን?’ አልኩት።

21 እርሱ ግን ጉዳዩ በሮም ንጉሠ ነገሥት እንዲታይለት ፈልጎ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ይግባኝ በማለቱ ወደ እዚያ እስክልከው ድረስ በእስር ቤት እንዲቈይ አዘዝኩ።”

22 አግሪጳም ፊስጦስን “እኔም ይህ ሰው ሲናገር መስማት እፈልጋለሁ” አለው። ፊስጦስም “ነገ ትሰማዋለህ” አለው።

23 ስለዚህ በማግስቱ አግሪጳና በርኒቄ ልብሰ መንግሥታቸውን ለብሰውና በታላቅ ግርማ ሆነው በጦር አለቆችና በከተማው ታላላቅ ሰዎችም ታጅበው መጡና ወደ ፍርድ አዳራሽ ገቡ፤ ከዚያም በኋላ ፊስጦስ ጳውሎስን አስጠራ።

24 እንዲህም አለ፤ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! እናንተም ከእኛ ጋር ያላችሁ ሰዎች ሁሉ! አይሁድ ‘ይህ ሰው ከእንግዲህ ወዲህ በሕይወት መኖር አይገባውም’ በማለት እየጮኹ በኢየሩሳሌምም፥ በዚህም እንዲፈረድበት የጠየቁኝ ይህ የምታዩት ሰው ነው።

25 እኔ ግን በሞት የሚያስቀጣው ምንም በደል አላገኘሁበትም፤ እርሱ ወደ ሮም ንጉሠ ነገሥት ይግባኝ በማለቱ ወደዚያ ልልከው ወሰንኩ።

26 ይሁን እንጂ ስለ እርሱ ለጌታዬ የምጽፈው የተረጋገጠ ነገር የለኝም፤ ስለዚህ ከተመረመረ በኋላ የምጽፈው ነገር እንዳገኝ ብዬ በፊታችሁ ይልቁንም ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! በፊትህ አቅርቤዋለሁ።

27 እስረኛ ወደ በላይ ሲላክ፥ የተከሰሰበትን ምክንያት አለመግለጥ ሞኝነት መስሎ ታይቶኛል።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios