Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ሐዋርያት ሥራ 24 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ጳውሎስ በአይሁድ መከሰሱ

1 ከአምስት ቀን በኋላ የካህናት አለቃው ሐናንያ ከአንዳንድ ሽማግሌዎችና ጠርጠሉስ ከሚባል ጠበቃ ጋር ወደ ቂሳርያ ሄደ፤ እነርሱም ወደ አገረ ገዥው ወደ ፊልክስ ቀርበው ጳውሎስን ከሰሱ፤

2 ጳውሎስ ተጠርቶ በመጣ ጊዜ፥ ጠርጠሉስ እንዲህ ሲል ክሱን ጀመረ፤ “ክቡር ፊልክስ ሆይ! በአንተ አማካይነት ብዙ ሰላም አግኝተናል፤ በመልካም አስተዳደርህም ለሕዝባችን መሻሻል ተገኝቶአል፤

3 እጅግ የተከበርክ ፊልክስ ይህን መልካም አድራጎትህን በየቦታውና በየጊዜው የምንቀበለው ከፍ ባለ ምስጋና ነው።

4 አሁን ግን ጊዜህን ሳላባክን ባጭሩ የምነግርህን በቸርነትህ እንድትሰማን እለምንሃለሁ፤

5 ይህ ሰው መጥፎ በሽታ ሆኖብናል፤ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ላይ ሁከት ያስነሣል፤ ናዝራውያን ለሚባሉት መሪያቸው ነው።

6 ቤተ መቅደስንም ሊያረክስ ሲሞክር ይዘነዋል፤ [በሕጋችንም መሠረት ልንፈርድበት አስበን ነበር፤

7 ነገር ግን የጦር አዛዡ ሉስዮስ መጥቶ በታላቅ ኀይል ከእጃችን ነጥቆ ወሰደው።

8 ከሳሾቹም ወደ አንተ እንዲመጡ አዘዘ፤] ይህን በእርሱ ላይ ያቀረብነውን ክስ ሁሉ እውነት መሆኑን አንተ ራስህ እርሱን መርምረህ ልታረጋግጥ ትችላለህ።”

9 አይሁድ “ይህ ሁሉ ነገር እውነት ነው” እያሉ በክሱ ተስማሙ።


ጳውሎስ በፊልክስ ፊት የመከላከያ ንግግር ማድረጉ

10 አገረ ገዥው ፊልክስ በእጁ ጠቅሶ ጳውሎስ እንዲናገር ፈቀደለት፤ ጳውሎስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ለብዙ ዓመቶች የዚህ አገር ገዢ መሆንክን ስለማውቅ ለቀረበብኝ ክስ መከላከያዬን በአንተ ፊት ሳቀርብ በጣም ደስ እያለኝ ነው፤

11 ለመስገድ ወደ ኢየሩሳሌም ከሄድኩ ከዐሥራ ሁለት ቀን እንደማይበልጥ አንተ ራስህ ማረጋገጥ ትችላለህ፤

12 በቤተ መቅደስም ሆነ በምኲራብ ወይም በከተማ ውስጥ ከማንም ጋር ስከራከር ወይም ሕዝቡን ለሁከት ሳነሣሣ አላገኙኝም፤

13 አሁን ላቀረቡብኝ ክስ ሁሉ ምንም ማስረጃ ሊያቀርቡልህ አይችሉም።

14 ነገር ግን ይህን ልገልጥልህ እወዳለሁ፤ እነርሱ አዲስ መንገድ በሚሉት የሃይማኖት ክፍል እምነት የአባቶቻችንን አምላክ አመልካለሁ፤ በሕግና በነቢያት መጻሕፍት የተጻፈውንም ሁሉ አምናለሁ።

15 እነርሱም ተስፋ እንደሚያደርጉት እኔም ጻድቃንና ኃጥአን ከሞት እንደሚነሡ በእግዚአብሔር ተስፋ አደርጋለሁ።

16 ስለዚህ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ንጹሕ ኅሊና እንዲኖረኝ ዘወትር እተጋለሁ።

17 “ከኢየሩሳሌም ከወጣሁ ብዙ ዓመቶች ካለፉ በኋላ ለወገኖቼ የሚሆን የእርዳታ ገንዘብና ለእግዚአብሔር የሚሰጥ መባ ይዤ መጣሁ።

18 በቤተ መቅደስም ያገኙኝ ይህንኑ ሳደርግ ነው፤ በዚያን ጊዜ የመንጻትን ሥርዓት ፈጽሜ ነበር፤ ከእኔ ጋር ብዙ ሕዝብ አልነበረም፤ ሁከትም አልተነሣም።

19 ነገር ግን ከእስያ የመጡት አይሁድ እዚያ ነበሩ፤ እነርሱ በእኔ ላይ የክስ ምክንያት ካላቸው በአንተ ፊት ቀርበው ይናገሩ።

20 ከዚህ በኋላ በሸንጎው ፊት በቀረብኩ ጊዜ ያደረግኹት በደል እንዳለ እነዚህ የቀረቡ ሰዎች ይናገሩ።

21 እርግጥ በመካከላቸው ቆሜ ‘የሙታን ትንሣኤ አለ በማለቴ ዛሬ ለፍርድ በፊታችሁ ቀርቤአለሁ’ ብዬ ከፍ ባለ ድምፅ ተናግሬአለሁ፤ ከዚህ በቀር ሌላ ያደረግኹት ነገር የለም።”

22 ፊልክስ ግን ስለ ክርስትና እምነት በደንብ ያውቅ ስለ ነበር “የጦር አዛዡ ሉስዮስ በመጣ ጊዜ፥ ስለ ጉዳያችሁ ውሳኔ እሰጣለሁ” ብሎ አሰናበታቸው።

23 ጳውሎስን ይጠብቅ የነበረውንም መቶ አለቃ “እምብዛም ነጻነት ሳትከለክለው በጥንቃቄ ጠብቀው፤ ወዳጆቹም የሚያስፈልገውን ሁሉ ይዘውለት ሲመጡ አትከልክልበት” አለው።


ጳውሎስ በፊልክስና በድሩሲላ ፊት መቅረቡ

24 ከጥቂት ቀኖች በኋላ ፊልክስ ዱሩሲላ ከተባለች አይሁዳዊት ሚስቱ ጋር መጣ፤ ጳውሎስንም አስጠርቶ በኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ማመን ሲናገር ሰማ።

25 ጳውሎስ ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም ፍርድ በተናገረ ጊዜ ፊልክስ ፈርቶ “አሁን ሂድ፤ ሲመቸኝ ሌላ ጊዜ አስጠራሃለሁ” አለው።

26 ፊልክስ ከጳውሎስ ጉቦ ለመቀበል ተስፋ ያደርግ ነበር፤ ስለዚህ ብዙ ጊዜ ጳውሎስን እያስጠራ ያነጋግረው ነበር።

27 ከሁለት ዓመት በኋላ ጶርቅዮስ ፊስጦስ በፊልክስ ቦታ ተተካ፤ ፊልክስ አይሁድን ደስ ለማሰኘት ፈልጎ ጳውሎስን እንደ ታሰረ ተወው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios