Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ሐዋርያት ሥራ 22 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 “ወንድሞቼና አባቶቼ ሆይ! እነሆ፥ አሁን የማቀርብላችሁን መከላከያ ስሙኝ!”

2 በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገር በሰሙ ጊዜ በይበልጥ ጸጥ አሉ፤ ጳውሎስም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፦

3 “እኔ በኪልቅያ በምትገኘው በጠርሴስ ከተማ የተወለድኩ አይሁዳዊ ነኝ፤ ያደግኹት ግን በዚህች በኢየሩሳሌም ከተማ ነው። አስተማሪዬም ገማልያል ነበር፤ የአባቶችን ሕግ ጠንቅቄ የተማርኩና ልክ ዛሬ እናንተ እንደምታደርጉት እግዚአብሔርን በመንፈሳዊ ቅናት የማገለግል ነበርኩ።

4 የክርስትናን እምነት የሚከተሉትን ሁሉ እስከ ሞት የማሳድድ ሰው ነበርኩ፤ ወንዶችንና ሴቶችን እያሰርኩ ወደ ወህኒ ቤት እንዲገቡ አደርግ ነበርኩ።

5 ይህም እውነት መሆኑን የካህናት አለቃውና የሽማግሌዎች ሸንጎ በሙሉ ይመሰክሩልኛል። እንዲያውም በደማስቆ ያሉትን እነዚህን ሰዎች አስሬ ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣትና ለማስቀጣት የሚያስችለኝን በደማስቆ ወደሚገኙት ወገኖቻቸው የጻፉትን ደብዳቤ የተቀበልኩት ከእነርሱ ነው።


ጳውሎስ ወደ ክርስቶስ እንዴት እንደ ተመለሰ መተረኩ
( ሐ.ሥ. 9፥1-19 ፤ 26፥12-18 )

6 “እኔ ወደ ደማስቆ ስሄድና ወደ ከተማው ስቀርብ እኩለ ቀን ላይ በድንገት ታላቅ ብርሃን ከሰማይ በዙሪያዬ አንጸባረቀ።

7 በዚያን ጊዜ በመሬት ላይ ወደቅኹ፤ ‘ሳውል! ሳውል! ለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚል ድምፅ ሰማሁ።

8 እኔም ‘ጌታ ሆይ! አንተ ማን ነህ?’ አልኩ፤ እርሱም ‘እኔ አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ’ አለኝ።

9 ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች ብርሃኑን አዩ እንጂ እርሱ ሲያነጋግረኝ ድምፁን አልሰሙም።

10 እኔም ‘ጌታ ሆይ! ምን ላድርግ?’ አልኩ። ጌታም ‘ተነሥተህ ወደ ደማስቆ ሂድ፤ ልታደርገው የሚገባህ ነገር ሁሉ እዚያ ይነገርሃል’ አለኝ።

11 ከብርሃኑ ማንጸባረቅ የተነሣ ማየት ስላልቻልኩ አብረውኝ የነበሩት ሰዎች እጄን ይዘው እየመሩኝ ወደ ደማስቆ አደረሱኝ።

12 “እዚያ ሐናንያ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው በደማስቆ በሚኖሩት አይሁድ ሁሉ የተመሰገነ፥ ሕግ አክባሪና መንፈሳዊ ሰው ነበረ።

13 እርሱ ወደ እኔ መጥቶ አጠገቤ ቆመና ‘ወንድሜ ሳውል ሆይ! ዐይንህ እንደገና ይይልህ!’ አለኝ፤ በዚያኑ ቅጽበት ዐይኔ አየ፤ እርሱንም ተመለከትኩት።

14 እርሱም እንዲህ አለኝ፤ ‘የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን እንድታውቅ ጻድቁን እንድታይና ድምፁንም እንድትሰማ አስቀድሞ መርጦሃል።

15 ይህንንም ያደረገው ስላየኸውና ስለ ሰማኸው በሰው ሁሉ ፊት የእርሱ ምስክር እንድትሆን ነው።

16 ታዲያ፥ አሁን ምን ትጠብቃለህ? ተነሥና የእርሱን ስም በመጥራት ተጠመቅ፤ ከኃጢአትህም ታጠብ።’

17 “ከዚህ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሼ በቤተ መቅደስ በምጸልይበት ጊዜ በተመስጦ ራእይ አየሁ።

18 ጌታም ተገልጦልኝ ‘አንተ ስለ እኔ የምትሰጠውን ምስክርነት ስለማይቀበሉ ሳትዘገይ በፍጥነት ከኢየሩሳሌም ውጣ’ አለኝ፤

19 እኔም እንዲህ አልኩ፤ ‘ጌታ ሆይ! በየምኲራቡ እየሄድኩ በአንተ ያመኑትን ሁሉ እንዳሰርኩና እንደ ደበደብኩ እነርሱ ራሳቸው ያውቃሉ።

20 የአንተ ምስክር የነበረው እስጢፋኖስ በተገደለ ጊዜ እኔም ራሴ በገዳዮቹ አጠገብ ቆሜ ከእነርሱ ጋር በነገሩ ተስማምቼ ነበር፤ ልብሳቸውንም እጠብቅ ነበር፤’

21 ጌታም ‘በሩቅ ወዳሉ ወደ አሕዛብ ስለምልክህ ተነሥና ሂድ!’ አለኝ።”


ጳውሎስ የሮም ዜጋ መሆኑን መግለጡ

22 እስከዚህ ድረስ ሕዝቡ ሁሉ የጳውሎስን ንግግር ያዳምጡ ነበር፤ ከዚህ በኋላ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፦ “እንዲህ ዐይነቱ ሰው ከምድር ላይ ይወገድ! እንዲህ ዐይነቱ ሰው በሕይወት መኖር አይገባውም!” እያሉ ጮኹ።

23 እነርሱ እየጮኹ ልብሳቸውን ያውለበልቡና ዐፈር ወደ ሰማይ ይበትኑ ነበር።

24 አዛዡ ይህን ባየ ጊዜ ጳውሎስን ወደ ወታደሮች ሰፈር እንዲያስገቡት አዘዘ፤ ሕዝቡ በእርሱ ላይ ስለምን ይህን ያኽል እንደሚጮኹ ለማወቅም እየተገረፈ እንዲመረመር አዘዘ።

25 ነገር ግን በጠፍር ወጥረው ሊገርፉት ሲዘጋጁ ጳውሎስ አጠገቡ የቆመውን የመቶ አለቃ “የሮም ዜግነት ያለውን ሰው ያለ ፍርድ ልትገርፉት ተፈቅዶላችኋልን?” አለው።

26 የመቶ አለቃው ይህን በሰማ ጊዜ ወደ አዛዡ ሄደና “ምን ልታደርግ ነው? ይህ ሰው እኮ የሮም ዜጋ ነው!” አለው።

27 ስለዚህ አዛዡ ወደ ጳውሎስ ቀረብ አለና “እስቲ ንገረኝ፤ አንተ የሮም ዜጋ ነህን?” አለው፤ እርሱም “አዎ፥ ነኝ፤” አለ።

28 አዛዡም “እኔ ይህን ዜግነት የገዛሁት በብዙ ገንዘብ ነው” አለ፤ ጳውሎስም “እኔ ግን በሮም ዜግነት ተወልጄአለሁ” አለ።

29 ስለዚህ እነዚያ ሊመረምሩት ተዘጋጅተው የነበሩት ሰዎች ወዲያውኑ ከእርሱ ራቁ፤ አዛዡም የሮም ዜጋ የሆነውን ሰው በሰንሰለት ማሰሩን በተገነዘበ ጊዜ ፈራ።


ጳውሎስ በአይሁድ ሸንጎ ፊት መቅረቡ

30 በማግስቱ አዛዡ፥ አይሁድ ጳውሎስን የከሰሱበት ትክክለኛ ምክንያት ምን እንደ ሆነ ለማወቅ ፈለገ፤ ስለዚህ የካህናት አለቆችና የሸንጎው አባሎች በሙሉ እንዲሰበሰቡ አዘዘ፤ ጳውሎስንም ከእስራቱ ፈቶ ወሰደና በፊታቸው አቀረበው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios