Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ሐዋርያት ሥራ 21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱ

1 ከእነርሱ ከተለየን በኋላ በመርከብ ተሳፈርንና በቀጥታ ቆስ ወደምትባል ደሴት ሄድን፤ በማግስቱም ወደ ሩድ ደሴት ደረስን፤ ከዚያም ወደ ጳጥራ ከተማ ሄድን።

2 እዚያም ወደ ፊንቄ አገር የምትሄድ መርከብ አገኘንና በእርስዋ ተሳፍረን፤ ጒዞአችንን ቀጠልን።

3 የቆጵሮስን ደሴት በስተግራችን ትተን ወደ ሶርያ አገር ተጓዝንና ወደ ጢሮስ ወደብ ሄድን፤ መርከቡ ጭነቱን እዚያ ማራገፍ ነበረበት።

4 እዚያ ምእመናንን ፈልገን አገኘንና ከእነርሱ ጋር ሰባት ቀን ቈየን። እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ጳውሎስን “ወደ ኢየሩሳሌም አትሂድ” ብለው ነገሩት።

5 እዚያ የምንቈይበት ጊዜ ሲያልቅ ተለይተናቸው ጒዞአችንን ቀጠልን፤ ሁሉም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር ሆነው እስከ ከተማው ውጪ ድረስ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ከጸለይን በኋላ ተሰነባበትን።

6 ከዚህ በኋላ እኛ በመርከብ ስንሳፈር እነርሱ ወደ ቤታቸው ተመለሱ።

7 ከጢሮስ ተነሥተን ወደ ጴጤሌማይስ ደረስን፤ እዚያ ከአማኞች ጋር ተገናኝተን ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ከእነርሱ ጋር አንድ ቀን አሳለፍን።

8 በማግስቱ ከዚያ ወጥተን ወደ ቂሳርያ ሄድን፤ እዚያ ከሰባቱ ዲያቆናት አንዱ ወደ ሆነው ወደ ወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገባንና ከእርሱ ጋር ተቀመጥን።

9 እርሱ ትንቢት የመናገር ስጦታ ያላቸው አራት ያላገቡ ሴቶች ልጆች ነበሩት።

10 ለብዙ ቀኖች እዚያ በተቀመጥንበት ጊዜ አጋቦስ የሚባል ነቢይ ከይሁዳ ምድር መጣ።

11 ይህ ነቢይ ወደ እኛ ቀረበ፤ የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጆቹንና እግሮቹን አሰረና “መንፈስ ቅዱስ የዚህን መታጠቂያ ባለቤት በኢየሩሳሌም ያሉ አይሁድ እንደዚህ አስረው ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል ይላል” አለ።

12 ይህንን በሰማን ጊዜ እኛም እዚያ የነበሩ ሰዎችም ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ለመንነው።

13 ጳውሎስ ግን “እንደዚህ እያለቀሳችሁ ስለምን ልቤን በሐዘን ትሰብሩታላችሁ? እኔ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመታሰር ብቻ ሳይሆን ለመሞትም ዝግጁ ነኝ” ሲል መለሰ።

14 ምክራችንን አልቀበልም ባለን ጊዜ “እንግዲህ የጌታ ፈቃድ ይሁን” ብለን ተውነው።

15 እዚያ ጥቂት ቀኖች ከቈየን በኋላ ዕቃችንን አዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ሄድን።

16 በቂሳርያ የነበሩ አንዳንድ ምእመናን አብረውን መጡ፤ እነርሱም በምናሶን ቤት እንድናርፍ ወደ እርሱ ቤት መሩን፤ ይህ ሰው ቀደም ብሎ ያመነ፥ የቆጵሮስ ተወላጅ ነበር።


ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ያዕቆብን መጐብኘቱ

17 ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ምእመናን በደስታ ተቀበሉን።

18 በማግስቱ ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ሄደ፤ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሁሉ እዚያ ነበሩ።

19 ጳውሎስ ለሁሉም ሰላምታ ከሰጠ በኋላ በእርሱ አማካይነት እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ሁሉ አንድ በአንድ ተረከላቸው።

20 ይህን በሰሙ ጊዜ ሁሉም ጌታን አመሰገኑ፤ ጳውሎስንም እንዲህ አሉት፦ “ወንድም ሆይ! በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ምእመናን በአይሁድ መካከል እንዳሉና ሁሉም ለሕግ ቀናተኞች እንደ ሆኑ ታውቃለህ፤

21 አንተ በአሕዛብ መካከል የሚኖሩትን አይሁድ ሁሉ ‘ልጆቻችሁን አትግረዙ ወይም ሥርዓቶችን አትፈጽሙ’ እያልክ በማስተማር የሙሴን ሕግ እንዲሽሩ ታደርጋለህ እየተባለ የሚወራውን ሰምተዋል።

22 እንግዲህ ምን ማድረግ ይሻላል? መምጣትህን በእርግጥ ይሰማሉ፤

23 ስለዚህ እኛ የምንልህን አድርግ፤ በእኛ መካከል ስለት ያለባቸው አራት ሰዎች አሉ።

24 እነርሱን ውሰድና ከእነርሱ ጋር ሆነህ ራስህን አንጻ፤ ጠጒራቸውንም እንዲላጩ ለቤተ መቅደስ የሚሰጠውን የመባ ገንዘብ ክፈልላቸው፤ ይህን ብታደርግ በአንተ ላይ የተወራው ሁሉ ከንቱ መሆኑንና አንተም ራስህ ለሕግ ታዛዥ መሆንክህን ሁሉም ያውቃሉ።

25 ከአሕዛብ ወገን ያመኑት ግን ‘ለጣዖት በመሠዋቱ ምክንያት የረከሰ ምግብ አትብሉ፤ ደምም አትብሉ፤ ታንቆ የሞተ እንስሳ ሥጋ አትብሉ፤ ከዝሙት ራቁ’ የሚለውን ውሳኔ የያዘ ደብዳቤ ጽፈን ልከንላቸዋል።”

26 ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ሰዎቹን ወሰደና በማግስቱ ከእነርሱ ጋር ራሱን አነጻ፤ የሚነጹባቸው ቀኖች መቼ እንደሚሆንና ስለ እያንዳንዱም የሚሰጠው የመባ ገንዘብ የሚከፈልበት ጊዜ መቼ እንደሚሆን ለማስታወቅ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ።


ጳውሎስ በቤተ መቅደስ መያዙ

27 ሰባቱ ቀን ሊፈጸም ሲቃረብ ከእስያ የመጡ አይሁድ ጳውሎስን በቤተ መቅደስ በማየታቸው ሕዝቡን ሁሉ አሳድመው ያዙት፤

28 “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! እርዱን! ሕዝባችንንና ሕጋችንን፥ ይህንንም ስፍራ እየተሳደበ በየአገሩ ያለውን ሕዝብ ሁሉ የሚያስተምር ይህ ሰው ነው፤ ይህም አልበቃ ብሎት አሕዛብን ወደ ቤተ መቅደስ በማስገባት ይህን የተቀደሰ ስፍራ አርክሶአል!” እያሉ ጮኹ።

29 ይህንንም ያሉበት ምክንያት ከዚህ ቀደም የኤፌሶኑን ተወላጅ ጥሮፊሞስን ከእርሱ ጋር በከተማ አይተውት ስለ ነበር እርሱን ጳውሎስ ወደ ቤተ መቅደስ ይዞት የገባ መስሎአቸው ነበር።

30 ከተማዋ በሙሉ ታወከች፤ ሕዝቡም ሁሉ እየሮጡ በአንድነት መጡና ጳውሎስን ይዘው እየጐተቱ ከቤተ መቅደስ አወጡት፤ የቤተ መቅደሱ በሮችም ወዲያውኑ ተዘጉ።

31 ሰዎቹ ጳውሎስን ሊገድሉት በፈለጉ ጊዜ “የኢየሩሳሌም ከተማ በሙሉ ታውካለች” የሚል መልእክት ለሮማውያኑ ጦር አዛዥ ደረሰ።

32 ስለዚህ እርሱ ወታደሮችንና የመቶ አለቆችን አስከትሎ በፍጥነት እየሮጠ ወደ ሰዎቹ ሄደ። ሰዎቹም አዛዡንና ወታደሮቹን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መደብደብ ተዉ።

33 አዛዡም ቀርቦ ጳውሎስን ያዘውና በሁለት ሰንሰለት እንዲታሰር አዘዘ፤ ከዚህ በኋላ ማን መሆኑንና ምን እንዳደረገ ለማወቅ ፈልጎ ጠየቀ።

34 ሕዝቡም አንዳንዶቹ አንድ ነገር ሲሉ፥ ሌሎች ሌላ ነገር ይሉ ነበር፤ አዛዡ ከሕዝቡ ጩኸት የተነሣ እርግጠኛውን ነገር ለማወቅ ስላልቻለ ጳውሎስን ወደ ወታደሮቹ ሰፈር እንዲወስዱት አዘዘ።

35 ጳውሎስ ወደ ደረጃው በደረሰ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ በብርቱ ቊጣ ተነሣሥቶ አደጋ ሊያደርስበት በመፈለጉ ወታደሮቹ ተሸክመውት ሄዱ።

36 ሕዝቡም “ይገደል!” እያሉ በመጮኽ ይከተሉት ነበር።


ጳውሎስ የመከላከያ ንግግር ማድረጉ

37 ወታደሮች ወደ ጦር ሰፈራቸው ሊያስገቡት በቀረቡ ጊዜ ጳውሎስ የጦር አዛዡን “አንድ ነገር እንድነግርህ ትፈቅድልኛለህን?” አለው። አዛዡም “የግሪክ ቋንቋ ታውቃለህን?

38 ታዲያ፥ አሁን በቅርቡ ብጥብጥ አስነሥቶና አራት ሺህ ነፍሰ ገዳዮች ይዞ ወደ በረሓ የሸሸው ግብጻዊው አንተ አይደለህምን?” አለ።

39 ጳውሎስም “እኔ በኪልቅያ በምትገኘውና ዝነኛ በሆነችው በጠርሴስ ከተማ የተወለድኩ አይሁዳዊ ነኝ፤ እባክህ ለሕዝቡ እንድናገር ፍቀድልኝ” አለው።

40 እንዲናገር በፈቀደለት ጊዜ ጳውሎስ በደረጃ ላይ ቆሞ ሕዝቡ ዝም እንዲል በእጁ ጠቀሰ፤ ሕዝቡ ጸጥ ባለ ጊዜ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፤

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios