ሐዋርያት ሥራ 18 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምጳውሎስ በቆሮንቶስ 1 ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ከአቴና ተነሥቶ ወደ ቆሮንቶስ ሄደ፤ 2 እዚያ የጳንጦስ ተወላጅ የሆነውን አቂላ የሚባል አንድ አይሁዳዊ ሰው አገኘ፤ የሮም ንጉሠ ነገሥት ቀላውዴዎስ አይሁድ ሁሉ ከሮም እንዲወጡ አዞ ስለ ነበረ አቂላ ከሚስቱ ከጵርስቅላ ጋር ከኢጣልያ ገና መምጣቱ ነበር፤ ስለዚህ ጳውሎስ ወደ እነርሱ ሄዶ ተዋወቃቸው፤ 3 የእርሱ ሥራ ልክ እንደ እነርሱ ድንኳን መስፋት ስለ ነበር ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ አብሮአቸው ይሠራ ነበር። 4 በየሰንበቱም በምኲራብ እየተገኘ ንግግር በማድረግ ለአይሁድና ለግሪኮች ያስረዳ ነበር። 5 ሲላስና ጢሞቴዎስ ከመቄዶንያ በመጡ ጊዜ ጳውሎስ “ኢየሱስ መሲሕ ነው” በማለት ለአይሁድ በትጋት እየመሰከረ በማስተማር ጊዜውን ሁሉ ያሳልፍ ነበር። 6 ነገር ግን አይሁድ በተቃወሙትና በሰደቡት ጊዜ የልብሱን ትቢያ አራግፎ “እንግዲህ ቢፈረድባችሁ በራሳችሁ ጥፋት ነው! እኔ ኀላፊነት የለብኝም፤ ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ!” አላቸው። 7 ስለዚህ ከእነርሱ ተለይቶ ቲቶስ ኢዮስጦስ ወደተባለው ሰው ቤት ሄደ፤ ይህ ሰው እግዚአብሔርን የሚያመልክ ነበር፤ ቤቱም በምኲራብ አጠገብ ነበር። 8 ቀርስጶስ የሚባል የምኲራብ አለቃ ከቤተሰቡ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ፤ ብዙ የቆሮንቶስ ሰዎችም ጳውሎስ ሲናገር ሰምተው አመኑና ተጠመቁ። 9 ጌታም ጳውሎስን ሌሊት በራእይ እንዲህ አለው፦ “አትፍራ፤ ተናገር፤ ዝም አትበል፤ 10 እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፤ በዚህች ከተማ ብዙ ሰዎች አሉኝና ጒዳት ሊያደርስብህ የሚችል ማንም የለም።” 11 ስለዚህ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል ለሕዝቡ እያስተማረ አንድ ዓመት ተኩል እዚያ ቈየ። 12 ጋልዮስ የአካይያ ገዢ ሆኖ በተሾመ ጊዜ አይሁድ በአንድነት ተባብረው በጳውሎስ ላይ ተነሡ፤ ወደ ፍርድ ሸንጎ ወሰዱትና፥ 13 “ይህ ሰው ሕግን በሚቃወም መንገድ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ያደርጋል!” አሉ። 14 ጳውሎስ መልስ ለመስጠት ተዘጋጅቶ ሳለ ጋልዮስ አይሁድን እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የአይሁድ ወገኖች! በደል ወይም ከባድ ወንጀል ተፈጽሞባችሁ ቢሆን ኖሮ ክሳችሁን በትዕግሥት በሰማሁ ነበር፤ 15 ነገር ግን ስለ ቃላትና ስለ ስሞች ስለ ሕጋችሁም የምትከራከሩ ከሆነ የራሳችሁ ጉዳይ ነው፤ እኔ በእነዚህ ነገሮች ላይ መፍረድ አልፈልግም።” 16 እንዲህም ብሎ ከፍርድ ሸንጎው አስወጣቸው። 17 በዚህ ጊዜ ሁሉም የምኲራብ አለቃውን ሶስቴንስን ይዘው በሸንጎው ፊት ደበደቡት፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ጋልዮስ ደንታ አልነበረውም። ጳውሎስ ወደ አንጾኪያ መመለሱ 18 ጳውሎስ ከወንድሞች ጋር ብዙ ቀኖች በቆሮንቶስ ከቈየ በኋላ ተሰናብቶአቸው ወደ ሶርያ ሄደ፤ ጵርስቅላና አቂላም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ ነገር ግን ስለት ስለ ነበረበት ከመሄዱ በፊት ክንክሪያ በሚባል ቦታ ራሱን ተላጨ። 19 ወደ ኤፌሶን በደረሱ ጊዜ ጵርስቅላንና አቂላን እዚያ ተዋቸው፤ እርሱ ግን ወደ ምኲራብ ገብቶ ለአይሁድ ንግግር ያደርግ ነበር። 20 ረዘም ላለ ጊዜ ከእነርሱ ጋር እንዲቈይ ቢለምኑትም እሺ አላላቸውም። 21 ነገር ግን “የእግዚአብሔር ፈቃድ ቢሆን ሌላ ጊዜ ወደ እናንተ ተመልሼ እመጣለሁ” አላቸውና ከኤፌሶን በመርከብ ተሳፍሮ ሄደ። 22 ወደ ቂሳርያም በደረሰ ጊዜ ከዚያ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ለቤተ ክርስቲያን ሰዎች ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ተመልሶ ወደ አንጾኪያ ወረደ። 23 እዚያም ጥቂት ጊዜ ቈየ፤ ከዚህ በኋላ በገላትያና በፍርግያ ምድር ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወረ አማኞችን አበረታታ። አጵሎስ በኤፌሶንና በቆሮንቶስ 24 የእስክንድርያ ተወላጅ የሆነ አጵሎስ የተባለ አንድ አይሁዳዊ ወደ ኤፌሶን መጣ፤ እርሱ ቅዱሳት መጻሕፍትን ጠንቅቆ የተማረና ጥሩ የአነጋገር ችሎታ ያለው ሰው ነበረ። 25 ስለ ጌታ መንገድ የተማረና በመንፈስም የተቃጠለ ሆኖ ስለ ኢየሱስ በትክክል ይሰብክና ያስተምር ነበር፤ ይሁን እንጂ እርሱ የሚያውቀው የዮሐንስን ጥምቀት ብቻ ነበር። 26 እርሱ በድፍረት በምኲራብ መናገር ጀመረ፤ ነገር ግን ጵርስቅላና አቂላ በሰሙት ጊዜ ወደ ቤታቸው ወሰዱትና የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ በትክክል አብራርተው ገለጡለት። 27 አጵሎስ ወደ አካይያ ለመሄድ ባሰበ ጊዜ ወንድሞች አሳቡን ደገፉ፤ በአካይያ ያሉ ወንድሞች በመልካም ሁኔታ እንዲቀበሉትም ደብዳቤ ጻፉለት። እዚያም በደረሰ ጊዜ በእግዚአብሔር ጸጋ አማኞች ለመሆን የበቁትን በጣም ረዳቸው። 28 ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን በቅዱሳት መጻሕፍት ቃል እያስረዳ በብርቱ ክርክር አይሁድን ይረታቸው ነበር። |