ሐዋርያት ሥራ 17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበተሰሎንቄ የተነሣ ሁከት 1 ጳውሎስና ሲላስ በአንፊጶሊስና በአጶሎንያ አልፈው ወደ ተሰሎንቄ ሄዱ፤ እዚያም የአይሁድ ምኲራብ ነበረ። 2 ጳውሎስ እንደ ልማዱ ወደ ምኲራብ ገባ፤ ለሦስት ሰንበትም አከታትሎ ከቅዱሳት መጻሕፍት እየጠቀሰ ለሕዝብ ያስረዳ ነበር። 3 መሲሕ መከራ መቀበልና ከሞት መነሣት እንደሚገባው ገልጦ እያስረዳ “ይህ እኔ የማበሥራችሁ ኢየሱስ መሲሕ ነው” ይል ነበር። 4 ስለዚህ ከእነርሱ አንዳንዶቹ ቃሉን ተረድተው ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ፤ እንዲሁም እግዚአብሔርን የሚያመልኩ እጅግ ብዙ አሕዛብ በከተማው የታወቁ ብዙ ሴቶች ቃሉን ተረድተው ተባበሩ። 5 አይሁድ ግን ቀንተው የሚበጠብጡ ሥራ ፈቶችን ከየመንገዱ ሰበሰቡና አሳደሙ። በከተማው ውስጥ ብጥብጥ እንዲነሣ አደረጉ፤ ጳውሎስንና ሲላስን አውጥተው ለሕዝቡ ለመስጠትም የኢያሶንን ቤት ከበቡ። 6 ነገር ግን እነርሱን ባጡአቸው ጊዜ ኢያሶንንና አንዳንድ አማኞችን ለከተማው ባለሥልጣኖች ለማቅረብ እየጐተቱ ወሰዱአቸው፤ እንዲህም እያሉ ይጮኹ ነበር፤ “እነዚህ ዓለምን ሁሉ ያወኩ ሰዎች አሁን ደግሞ ወደዚህ መጥተዋል! 7 ኢያሶንም ተቀብሎአቸዋል፤ ‘ኢየሱስ የሚባል ሌላ ንጉሥ አለ’ እያሉም የሮምን ንጉሠ ነገሥት ትእዛዝ ይቃወማሉ።” 8 ሕዝቡና የከተማው ባለሥልጣኖች ይህን በሰሙ ጊዜ ተሸበሩ። 9 ኢያሶንንና ሌሎቹንም ዋስ አስጠርተው ለቀቁአቸው። ጳውሎስና ሲላስ በቤርያ 10 ወንድሞች በቶሎ ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ እንዲሄዱ አደረጉአቸው፤ እዚያም በደረሱ ጊዜ ወደ አይሁድ ምኲራብ ገቡ። 11 በቤርያ ያሉት አይሁድ በተሰሎንቄ ካሉት ይልቅ ቅን አመለካከት ያላቸው ስለ ነበሩ ቃሉን በታላቅ ደስታ ተቀበሉ፤ የቃሉንም እውነተኛነት ለማረጋገጥ በየቀኑ ቅዱሳት መጻሕፍትን ይመረምሩ ነበር። 12 ስለዚህ ከእነርሱ ብዙዎች አመኑ፤ ብዙዎች የግሪክ ሀብታሞች ሴቶችና ብዙዎች ግሪካውያን ወንዶችም አመኑ። 13 ነገር ግን በተሰሎንቄ ያሉት አይሁድ ጳውሎስ በቤርያም የእግዚአብሔርን ቃል እንዳበሠረ ባወቁ ጊዜ ወደዚያ መጡና ሕዝቡን አሳድመው ብጥብጥ አስነሡ። 14 በዚህ ጊዜ ወንድሞች በቶሎ ጳውሎስ ወደ ባሕሩ አጠገብ እንዲሄድ አደረጉት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን እዚያው በቤርያ ቀሩ። 15 ጳውሎስን የሸኙት ሰዎች እስከ አቴና አደረሱት “ሲላስና ጢሞቴዎስ ሳይዘገዩ በቶሎ ወደ እኔ ይምጡልኝ” የሚለውንም የጳውሎስን ትእዛዝ ይዘው ወደ ቤርያ ተመለሱ። ጳውሎስ በአቴና 16 ጳውሎስ በአቴና ሆኖ ሲላስንና ጢሞቴዎስን ሲጠብቅ ሳለ በከተማዋ ጣዖት መሙላቱን በተመለከተ ጊዜ በመንፈሱ ተበሳጨ። 17 ስለዚህ በምኲራብ ከአይሁድና እግዚአብሔርንም ከሚያመልኩት ሰዎች ጋር በአደባባይም በየቀኑ ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ይከራከር ነበር። 18 ኤፒኮሮሶችና እስቶይኮች የተባሉ ፈላስፎችም ወደ እርሱ እየመጡ ይከራከሩ ነበር። አንዳንዶቹ “ይህ ለፍላፊ ምን ማለት ይፈልጋል?” ሲሉ፥ ሌሎች ደግሞ “ስለ አዳዲስ አማልክት የሚናገር ይመስላል” ይሉ ነበር፤ ይህንንም ያሉበት ምክንያት ጳውሎስ የኢየሱስንና የትንሣኤውን መልካም ዜና ስላበሠረ ነው። 19 ስለዚህ ጳውሎስን ይዘው አርዮስፋጎስ በተባለው ስፍራ ወደሚሰበሰበው ጉባኤ አመጡትና እንዲህ አሉት፤ “ይህ አንተ የምታስተምረው አዲስ ትምህርት ምን እንደ ሆነ ማወቅ እንችላለንን? 20 አንዳንድ እንግዳ ነገሮችን አሰምተኸናል፤ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ምን እንደ ሆኑ ማወቅ እንፈልጋለን።” 21 ይህን ያሉት የአቴና ነዋሪዎችና በአቴና የሚኖሩ የውጪ አገር ሰዎች ሁሉ አዲስ ነገር በመናገርና በመስማት ብቻ ጊዜያቸውን ማሳለፍ ይወዱ ስለ ነበር ነው። 22 በዚህ ጊዜ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ በተሰበሰበው ጉባኤ ፊት ቆመና እንዲህ አለ፤ “የአቴና ሰዎች ሆይ! በሁሉም በኩል በጣም ሃይማኖተኞች መሆናችሁን ተረድቼአለሁ፤ 23 በከተማችሁ እየተዘዋወርኩ የአምልኮ ስፍራዎቻችሁን ስመለከት ‘ለማይታወቅ አምላክ’ ተብሎ የተጻፈበትን የመሠዊያ ቦታ አገኘሁ፤ እንግዲህ እኔ አሁን የምነግራችሁ ስለዚሁ ሳታውቁ ስለምታመልኩት አምላክ ነው። 24 እርሱ ዓለምንና በዓለም ያለውንም ሁሉ የፈጠረ ነው፤ የሰማይና የምድርም ጌታ ነው፤ እርሱ በሰው እጅ በተሠራ ቤተ መቅደስ አይኖርም፤ 25 ሕይወትንና እስትንፋስን፥ ሌሎችንም ነገሮች ለሰው ሁሉ የሚሰጥ እርሱ ስለ ሆነ ምንም ነገር አይጐድለውም፤ የሰውም ርዳታ አያስፈልገውም። 26 እርሱ የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ፤ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩም አደረገ፤ የተወሰኑ ዘመኖችንና የሚኖሩባቸውንም ቦታዎች መደበላቸው። 27 ይህንንም ያደረገው ሰዎች ጌታን እንዲፈልጉና በመመራመርም ፈልገው እርሱን ማግኘት እንዲችሉ ነው፤ ሆኖም እርሱ ከእኛ ከእያንዳንዳችን ሩቅ ነው ማለት አይደለም። 28 ‘ሕይወት የምናገኘውና የምንንቀሳቀሰው፥ የምንኖረውም በእርሱ ነው፤’ ይህም የእናንተ ባለ ቅኔዎች ‘እኛ ሁላችን የእርሱ ልጆች ነን’ እንዳሉት ነው። 29 እንግዲህ እኛ የእርሱ ልጆች ከሆንን ‘እግዚአብሔር በሰው ጥበብና አሳብ ከወርቅ ወይም ከብር ወይም ከድንጋይ የተሠራውን ቅርጽ ይመስላል’ ብለን ማሰብ አይገባንም። 30 እንግዲህ ሰዎች በቀድሞ ዘመን ባለማወቅ ያደረጉትን እግዚአብሔር ችላ ብሎ አልፎታል፤ አሁን ግን በየአገሩ ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡ አዞአል፤ 31 እርሱ በመረጠው ሰው አማካይነት በዓለም ሁሉ ላይ በእውነት የሚፈርድበትን ቀን ወስኖአል፤ ይህንንም ለሁሉም ያረጋገጠው ያን የመረጠውን ሰው ከሞት በማስነሣቱ ነው።” 32 “ከሞት መነሣት” የሚለውን ቃል በሰሙ ጊዜ አንዳንዶች አፌዙበት፤ ሌሎች ግን “ስለዚህ ጉዳይ ስትናገር ሌላ ጊዜ እንሰማለን” አሉት። 33 ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ከጉባኤው ወጥቶ ሄደ፤ 34 አንዳንድ ሰዎች ግን ከእርሱ ጋር ተባበሩና አመኑ፤ ካመኑትም ሰዎች መካከል የአርዮስፋጎስ ጉባኤ አባል የሆኑት ዲዮናስዮስ የተባለ ሰውና ደማሪስ የተባለች አንዲት ሴት፥ ሌሎችም ይገኙባቸዋል። |