ሐዋርያት ሥራ 14 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምጳውሎስና በርናባስ በኢቆንዮን 1 በኢቆንዮን ጳውሎስና በርናባስ አብረው ወደ አይሁድ ምኲራብ ገቡ፤ በዚያም ብዙ አይሁድና ከአሕዛብ እጅግ ብዙ ሰዎች እስኪያምኑ ድረስ አስተማሩ። 2 ያላመኑት አይሁድ ግን አሕዛብን አነሣሥተው በወንድሞች ላይ ጥላቻ እንዲፈጠር አደረጉ። 3 ስለዚህ ጳውሎስና በርናባስ የጌታን ነገር በድፍረት እየተናገሩ እዚያ ብዙ ጊዜ ቈዩ፤ ጌታም ተአምራትና ድንቅ ነገሮች በእነርሱ እጅ እንዲደረጉ ሥልጣን በመስጠት፥ የእርሱ የጸጋ ቃል እውነተኛ መሆኑን ያረጋግጥ ነበር። 4 የከተማው ነዋሪዎች ግን፥ በሁለት ተከፍለው ግማሹ ከአይሁድ ጋር ግማሹም ከሐዋርያት ጋር ሆኑ። 5 አሕዛብና አይሁድ ከአለቆቻቸው ጋር ሆነው ጳውሎስንና በርናባስን ሊያንገላቱአቸውና በድንጋይ ሊወግሩአቸው ፈለጉ፤ 6 ጳውሎስና በርናባስ ይህን ባወቁ ጊዜ ልስጥራና ደርቤ ወደሚባሉት ወደ ሊቃኦንያ ከተሞችና በዙሪያቸው ወዳለው አገር ሸሽተው ሄዱ። 7 እዚያም ወንጌልን ሰበኩ። ጳውሎስና በርናባስ በልስጥራና በደርቤ 8 በልስጥራ እግሩ የሰለለ አንድ ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው ከተወለደ ጀምሮ ሽባ ስለ ነበር በእግሩ ሄዶ አያውቅም፤ 9 ይህ ሰው ጳውሎስ በሚናገርበት ጊዜ ተቀምጦ ያዳምጥ ነበር፤ ጳውሎስ ሰውየውን ትኲር ብሎ ተመለከተና ለመዳን የሚያበቃው እምነት እንዳለው ባየ ጊዜ፥ 10 “ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም!” ሲል በታላቅ ድምፅ ተናገረ፤ ሰውየውም ብድግ አለና መራመድ ጀመረ። 11 ሰዎቹም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ፥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “አማልክት በሰው አምሳል ሆነው ወደ እኛ ወርደዋል!” በማለት በሊቃኦንያ ቋንቋ ተናገሩ። 12 በርናባስንም “ድያ” አሉት፤ ዋናው ተናጋሪ ጳውሎስ ስለ ነበረ እርሱን “ሄርሜን” አሉት። 13 ከከተማው ውጪ ያለው የድያ ቤተ መቅደስ ካህን ኮርማዎችንና የአበባ ጒንጒኖችን ወደ ከተማው በር አምጥቶ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ለጳውሎስና ለበርናባስ መሥዋዕት ሊያቀርብላቸው ፈለገ። 14 ሐዋርያቱ ጳውሎስና በርናባስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ በሐዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ወደ ሕዝቡ ሮጡና እየጮኹ እንዲህ አሉ፦ 15 “እናንተ ሰዎች ለምን ይህን ታደርጋላችሁ? እኛም እንደ እናንተ ሰዎች ነን፤ እኛ እዚህ የመጣነው እናንተ ከዚህ ከከንቱ ነገር ሁሉ ርቃችሁ ሰማይን፥ ምድርን፥ ባሕርንና በውስጣቸው የሚገኙትን ሁሉ ወደ ፈጠረው ወደ ሕያው አምላክ እንድትመለሱ መልካም ዜና ልናበሥርላችሁ ነው፤ 16 ባለፉት ዘመኖች ሕዝቦች ሁሉ በገዛ ራሳቸው መንገድ እንዲሄዱ እግዚአብሔር ትቶአቸዋል፤ 17 ይሁን እንጂ እርሱ እንዴት ያለ ቸር አምላክ መሆኑን የሚመሰክር መልካም ሥራ ማድረጉን አላቋረጠም፤ ከሰማይ ዝናብን አዘነበላችሁ፤ የመከር ወራትንም ሰጣችሁ፤ በምግብና በደስታ ልባችሁን አረካ።” 18 ሐዋርያት ይህን ያኽል ቢናገሩም እንኳ ሕዝቡ ለእነርሱ መሥዋዕት እንዳያቀርብ ያስተዉት በብዙ ችግር ነው። 19 አይሁድ ግን ከአንጾኪያና ከኢቆንዮን ወደዚያ መጥተው ሕዝቡን አሳደሙና ጳውሎስን በድንጋይ እንዲወግሩት አደረጉ፤ የሞተ መስሎአቸውም ጐትተው ከከተማ አወጡት። 20 ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በዙሪያው በቆሙ ጊዜ ጳውሎስ ተነሣና ወደ ከተማ ገባ፤ በማግስቱም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤ ሄደ። ጳውሎስና በርናባስ በሶርያ ወደምትገኘው አንጾኪያ መመለሳቸው 21 ጳውሎስና በርናባስ በደርቤ ወንጌልን አስተምረው ብዙ ሰዎችን አማኞች ካደረጉ በኋላ በልስጥራና በኢቆንዮን አልፈው በጵስድያ ወደምትገኘው አንጾኪያ ሄዱ። 22 በእነዚያም አገሮች ሁሉ አማኞች በእምነታቸው እንዲጸኑ በማበረታታትና በመምከር “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ብዙ መከራ መቀበል አለብን” እያሉ አስተማሩአቸው። 23 በየቤተ ክርስቲያኑም ሽማግሌዎችን ሾሙላቸው፤ ከጾሙና ከጸለዩም በኋላ ላመኑበት ጌታ ዐደራ ሰጡአቸው። 24 በጵስድያም አልፈው ወደ ጵንፍልያ ሄዱ፤ 25 በጴርጌም የእግዚአብሔርን ቃል ካስተማሩ በኋላ ወደ አጣልያ ሄዱ፤ 26 ከዚያም ስለ ፈጸሙት ሥራ ለእግዚአብሔር ጸጋ ዐደራ ወደ ተሰጡበት ወደ አንጾኪያ በመርከብ ሄዱ። 27 እዚያም በደረሱ ጊዜ አማኞችን በአንድነት ሰብስበው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ሆኖ ያደረገውን ሁሉና አሕዛብም እንዲያምኑ እንዴት አድርጎ በር እንደ ከፈተላቸው ነገሩአቸው። 28 እዚያም ከአማኞች ጋር ብዙ ጊዜ ቈዩ። |