Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ሐዋርያት ሥራ 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


በርናባስና ሳውል በመንፈስ ቅዱስ ተመርጠው ለማስተማር እንደ ተላኩ

1 በአንጾኪያ ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያት ተብለው የሚጠሩ ሰባኪዎችና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም፦ በርናባስ፥ ጥቊር የተባለው ስምዖን፥ የቀሬናው ሉክዮስ፥ የአራተኛው ክፍል ገዢ የሄሮድስ አብሮ ዐደግ የነበረው ምናሔና ሳውል ነበሩ።

2 እነርሱ ጌታን ሲያገለግሉና ሲጾሙ ሳሉ መንፈስ ቅዱስ “እኔ ለመረጥኳቸው ሥራ በርናባስንና ሳውልን ለዩልኝ!” አለ።

3 እነርሱም ጾመውና ጸልየው እጆቻቸውን ከጫኑባቸው በኋላ ላኳቸው።


በርናባስና ሳውል በቆጵሮስ

4 በርናባስና ሳውል በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ሄዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ተጓዙ።

5 ወደ ሰላሚስ ከተማ በደረሱ ጊዜ በአይሁድ ምኲራቦች የእግዚአብሔርን ቃል አስተማሩ፤ ዮሐንስ ማርቆስም ከእነርሱ ጋር ሆኖ ይረዳቸው ነበር።

6 የቆጵሮስን ደሴት አቋርጠው ወደ ጳፉ በደረሱ ጊዜ ባርየሱስ የሚባለውን አንድ አይሁዳዊ ጠንቋይ አገኙ፤ እርሱ ሐሰተኛ ነቢይ ነበር።

7 የሚኖረውም ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አስተዋይ አገረ ገዢ ጋር ነበረ፤ ይህ አገረ ገዢ በርናባስንና ሳውልን አስጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ፈለገ።

8 ነገር ግን በግሪክ ቋንቋ “ኤሊማስ” ተብሎ የሚጠራው ጠንቋይ ባርየሱስ አገረ ገዢው እንዳያምን ፈልጎ በርናባስንና ሳውልን ተቃወማቸው።

9 ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ሰውየውን ትኲር ብሎ ተመለከተውና እንዲህ አለው፦

10 “አንተ የዲያብሎስ ልጅ! የእውነት ሁሉ ጠላት! ማታለልና ክፋት ሁሉ የሞላብህ፥ ቀጥተኛውን የጌታን መንገድ ማጣመም አትተውምን!

11 አሁንም እነሆ፥ የጌታ እጅ ይመታሃል፤ ዕውርም ትሆናለህ፤ ለጥቂት ጊዜም የፀሐይን ብርሃን አታይም።” ወዲያውኑ ዐይኖቹን ጭጋግና ጨለማ ሸፈናቸው፤ እጁን ይዞ የሚመራውንም ሰው ዙሪያውን መፈለግ ጀመረ።

12 አገረ ገዢውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ አመነ፤ ስለ ጌታ በሰማውም ትምህርት ተደነቀ።


በርናባስና ጳውሎስ በጲስድያ ወደምትገኘው አንጾኪያ መሄዳቸው

13 ከዚህ በኋላ ጳውሎስና ጓደኞቹ በመርከብ ተሳፍረው ከጳፉ በጵንፍልያ ወደምትገኘው ወደ ጴርጌ ሄዱ፤ ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ ግን ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ሄደ።

14 እነርሱ ግን ከጴርጌ ተነሥተው በጲስድያ ወደምትገኘው ወደ አንጾኪያ ሄዱ፤ በሰንበት ቀን ወደ አንድ ምኲራብ ገብተው ተቀመጡ።

15 የሕግና የነቢያት መጻሕፍት ከተነበቡ በኋላ የምኲራቡ አለቆች “ወንድሞች ሆይ፥ ሕዝቡን የሚያጽናና የምክር ቃል ካላችሁ ተናገሩ” ብለው ወደነጳውሎስ ሰው ላኩ።

16 ስለዚህ ጳውሎስ ተነሣና ሕዝቡን በእጁ ጠቀሰ፤ እንዲህም ሲል ተናገረ፤ “የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርን የምትፈሩ እናንተ አሕዛብ! ስሙ!

17 የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ የቀድሞ አባቶቻችንን መረጠ፤ በግብጽ አገር በነበሩበት ጊዜም ትልቅ ሕዝብ አደረጋቸው፤ በታላቅ ኀይሉም ከዚያ አገር አወጣቸው።

18 ለአርባ ዓመትም ያኽል በበረሓ ታገሣቸው

19 ከዚያም በኋላ በከነዓን አገር ሰባት መንግሥታትን አጥፍቶ የእነርሱን ምድር አወረሳቸው፤

20 ከዚህም በኋላ ለአራት መቶ ኀምሳ ዓመት ያኽል እስከ ነቢዩ ሳሙኤል ድረስ መሳፍንትን ሰጣቸው።

21 “ከዚያም ቀጥሎ ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው እግዚአብሔርን ለመኑ፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሆነውን የቂስን ልጅ ሳኦልን ለአርባ ዓመት አነገሠላቸው።

22 ሳኦልንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን አነገሠላቸው፤ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲመሰክር፦ ‘እንደ ፍላጎቴ የሚሆንልኝን፤ ፈቃዴንም የሚፈጽመውን፥ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ’ ብሎአል።

23 ከዚህ ሰው ዘር እግዚአብሔር በገባው የተስፋ ቃል መሠረት የእስራኤልን አዳኝ ኢየሱስን አስነሣላቸው።

24 ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ ለእስራኤል ሰዎች ሁሉ የንስሓን ጥምቀት ሰብኮ ነበር።

25 ዮሐንስ ሥራውን በጨረሰ ጊዜ ‘እኔ ማን መሰልኳችሁ? እኔ መሲሕ አይደለሁም፤ ነገር ግን የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የማልበቃ ከእኔ በኋላ ሌላ ይመጣል’ ይል ነበር።

26 “እናንተ ከአብርሃም ዘር የተወለዳችሁ ወንድሞችና እናንተም እግዚአብሔርን የምትፈሩ አሕዛብ! ይህ የመዳን ቃል የተላከው ለእኛ ነው።

27 በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው ኢየሱስ አዳኝ መሆኑን አላወቁም፤ በየሰንበቱም የሚነበቡትን የነቢያት መጻሕፍት ባለማስተዋላቸው በእርሱ ላይ በፈረዱበት ጊዜ ትንቢቱ ተፈጻሚ እንዲሆን አድርገዋል።

28 ምንም እንኳ ለሞት የሚያበቃ ምክንያት ባያገኙበት እርሱን እንዲገድልላቸው ጲላጦስን ለመኑት።

29 ስለ እርሱ የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙበት በኋላ ከመስቀል አውርደው ቀበሩት፤

30 ነገር ግን እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው።

31 ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ከእርሱ ጋር ለመጡትም ብዙ ቀን ታያቸው፤ እነርሱም አሁን በሕዝብ ፊት ምስክሮቹ ናቸው።

32 እኛም ይዘንላችሁ የመጣነው እግዚአብሔር ለአባቶቻችን በተስፋ የሰጠውን መልካም ዜና ነው።

33 እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሞት በማስነሣቱ ይህንኑ ተስፋ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞታል፤ ይህም በሁለተኛው መዝሙር፥ ‘አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፤’ ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።

34 መበስበስ እንዳይደርስበት እግዚአብሔር ከሞት እንዳስነሣው ለማስረዳት፥ ‘ቅዱሱን የታመነ በረከትን ለዳዊት የተሰጠውን ተስፋ እሰጣችኋለሁ’ ብሎ ተናግሮአል።

35 ደግሞም በሌላ መዝሙር፥ ‘ቅዱሱ ልጅህ መበስበስ እንዲደርስበት አታደርገውም’ ይላል።

36 ነገር ግን ዳዊት በሕይወቱ ዘመን አገልግሎቱን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከፈጸመ በኋላ ሞቶአል፤ ከአባቶቹም ጋር ተቀብሮአል፤ መበስበስም ደርሶበታል።

37 እግዚአብሔር ከሞት ያስነሣው ግን መበስበስ አልደረሰበትም።

38 እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! የኃጢአት ይቅርታ የሚገኘው በኢየሱስ መሆኑ እንደ ተሰበከላችሁ ዕወቁ፤

39 በእርሱ የሚያምን ሁሉ በሙሴ አማካይነት የተሰጠው ሕግ ነጻ ሊያወጣው ከማይችለው ኃጢአት ሁሉ ነጻ ይወጣል።

40 ስለዚህ በነቢያት እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤

41 ‘እናንተ ፌዘኞች እዩ! ተደነቁ! ጥፉም! ማንም ሰው ቢያወራላችሁ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እሠራለሁ።’ ”

42 ጳውሎስና በርናባስ ከምኲራብ ሲወጡ ይህንኑ ነገር በሚመጣው ሰንበት እንደገና እንዲነግሩአቸው ሰዎቹ ለመኑአቸው።

43 የምኲራቡ ጉባኤ በተበተነ ጊዜ ብዙ የአይሁድ ወገኖችና ወደ አይሁድ እምነት ገብተው እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሰዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፤ ጳውሎስና በርናባስም ሰዎቹን በማስተማር በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አሳሰቡአቸው።

44 በሚቀጥለው ሰንበት ከከተማው ነዋሪዎች አብዛኞቻቸው የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ተሰበሰቡ፤

45 አይሁድ የሕዝቡን ብዛት ባዩ ጊዜ በቅናት ተሞሉ፤ ንግግሩንም እየተቃወሙ ጳውሎስን ሰደቡት፤

46 ጳውሎስና በርናባስ ግን እንዲህ ሲሉ በድፍረት ተናገሩ፤ “የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ እንዲነገር አስፈላጊ ነው፤ እናንተ አንቀበልም ካላችሁና የዘለዓለም ሕይወት እንደማይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን እነሆ፥ እኛ ዞር ብለን ወደ አሕዛብ እንሄዳለን።

47 ይህንንም የምናደርገው ጌታ፦ ‘መዳንን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንድታመጣ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ’ በማለት ስላዘዘን ነው።”

48 አሕዛብ ይህን በሰሙ ጊዜ ደስ አላቸው፤ የጌታንም ቃል አከበሩ፤ ለዘለዓለም ሕይወት የተመረጡትም ሁሉ አመኑ።

49 የጌታም ቃል በዚያ አገር ሁሉ ተስፋፋ።

50 የአይሁድ መሪዎች ግን የአይሁድ እምነት ተከታዮች የሆኑትን ሀብታሞች ሴቶችና የከተማውን ታላላቅ ሰዎች አሳድመው በጳውሎስና በበርናባስ ላይ ስደት እንዲነሣ አደረጉ፤ ከአገራቸውም አስወጡአቸው።

51 ጳውሎስና በርናባስም በእነርሱ ላይ የእግራቸውን አቧራ አራግፈው ወደ ኢቆንዮን ሄዱ።

52 ደቀ መዛሙርቱም በደስታና በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios