Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ሐዋርያት ሥራ 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


በክርስቲያኖች ላይ የደረሰ ታላቅ ስደት

1 በዚያን ዘመን ንጉሥ ሄሮድስ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ሰዎችን ማሳደድ ጀመረ፤

2 የዮሐንስን ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ አስገደለው።

3 ይህ ነገር አይሁድን ደስ እንዳሰኛቸው ባየ ጊዜ ጴጥሮስንም ደግሞ አስያዘው፤ ይህም የሆነው አይሁድ የቂጣ በዓልን በሚያከብሩባቸው ቀኖች ነበር።

4 ጴጥሮስን ካስያዘ በኋላ ወደ ወህኒ ቤት አስገባው፤ ከአይሁድ የፋሲካ በዓል በኋላ ለሕዝቡ እስኪያቀርበው ድረስ አራት አራት ሆነው እንዲጠብቁት ለአራት ጭፍሮች አስረከበው።

5 ስለዚህ ጴጥሮስ በወህኒ ቤት ተይዞ ይጠበቅ ነበር፤ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር በጥብቅ ትጸልይ ነበር።


መልአክ ጴጥሮስን ከእስር ቤት እንዳወጣው

6 ሄሮድስ በማግስቱ ጴጥሮስን ለሕዝቡ ሊያቀርበው አስቦ ነበር፤ ጴጥሮስም በዚያች ሌሊት በሁለት ሰንሰለት ታስሮ በሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ሌሎች ወታደሮችም የወህኒ ቤቱን በር ይጠብቁ ነበር።

7 በዚያን ጊዜ የጌታ መልአክ ተገልጦ ታየ፤ በወህኒ ቤቱም ውስጥ ብርሃን በራ፤ መልአኩ የጴጥሮስን ጐን መትቶ ቀሰቀሰውና “በፍጥነት ተነሥ!” አለው፤ ሰንሰለቶቹም ከእጆቹ ላይ ወደቁ።

8 መልአኩም “ልብስህን ልበስ! ጫማህንም አድርግ!” አለው። ጴጥሮስ እንደታዘዘው አደረገ፤ መልአኩም “ነጠላህን ልበስና ተከተለኝ!” አለው።

9 ጴጥሮስም ወጣና ተከተለው፤ ራእይ የሚያይ መሰለው እንጂ መልአኩ ያደረገው ነገር ሁሉ እውነት አልመሰለውም።

10 አንደኛውንና ሁለተኛውን ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚወስደው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ። መዝጊያውም ሰው ሳይነካው እንዲሁ ተከፈተላቸውና ወጥተው በአንድ ስላች መንገድ አልፈው ሄዱ፤ በድንገትም መልአኩ ከጴጥሮስ ተለይቶ ሄደ።

11 ጴጥሮስም ወደ ልቡናው ተመልሶ፥ “ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠባበቁት ከነበረው ነገር ሁሉ ያዳነኝ መሆኑን አሁን ገና በእውነት ዐወቅሁ!” አለ።

12 ይህን ካረጋገጠ በኋላ ብዙ ሰዎች በአንድነት ተሰብስበው ወደሚጸልዩበት ወደ ማርያም ቤት ሄደ፤ ይህችም ማርያም ማርቆስ የተባለው የዮሐንስ እናት ነበረች።

13 ጴጥሮስ እዚያ ደርሶ የውጪውን በር ባንኳኳ ጊዜ ሮዳ የምትባል አንዲት ገረድ ማን እንደ ሆነ ለማወቅ ወደ በሩ መጣች።

14 የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑን ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ ብዛት የተነሣ በሩን ሳትከፍት ሮጣ ወደ ውስጥ ገባችና “ጴጥሮስ በበር ቆሞአል!” ስትል ተናገረች።

15 እነርሱም “አብደሻል!” አሉአት። እርስዋ ግን “በእውነት እርሱ ነው!” ስትል አረጋገጠች፤ እነርሱም እንግዲያውስ “የእርሱ ጠባቂ መልአክ ይሆናል” አሉ።

16 ጴጥሮስ ግን በር ማንኳኳቱን ቀጠለ፤ እነርሱም በሩን ከፍተው ባዩት ጊዜ ተገረሙ።

17 እርሱ ግን ዝም እንዲሉ በእጁ አመልክቶ ጌታ ከወህኒ ቤት እንዴት እንዳስወጣው አወራላቸውና “ይህን ነገር ለያዕቆብና ለቀሩት ምእመናን ንገሩ” አላቸው። ተለይቶአቸውም ወደ ሌላ ቦታ ሄደ።

18 በነጋም ጊዜ ወታደሮቹ “ጴጥሮስ ምን ደርሶበት ይሆን?” በማለት እጅግ ታወኩ።

19 ሄሮድስም በበኩሉ ጴጥሮስን አስፈልጎ ባጣው ጊዜ ዘብ ጠባቂዎችን ከመረመረ በኋላ እንዲገደሉ አዘዘ፤ ከዚህም በኋላ ሄሮድስ ከይሁዳ ወደ ቂሳርያ ሄዶ እዚያ ተቀመጠ።


የሄሮድስ አሟሟት

20 ሄሮድስ በጢሮስና በሲዶና ሰዎች ላይ በጣም ተቈጥቶ ነበር፤ እነርሱም በአንድነት መጡና፤ የንጉሥ ባለሟል ብላስጦስ እንዲተባበራቸው ለምነው እሺ ካሰኙትም በኋላ ንጉሡን ዕርቅ ጠየቁ፤ ይህንንም ያደረጉት አገራቸው ምግብ የምታገኘው ከንጉሡ ግዛት ስለ ነበረ ነው።

21 በተቀጠረው ቀን ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለበሰና በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ለሕዝቡ ንግግር አደረገ።

22 ሕዝቡም “ይህ የአምላክ ድምፅ ነው እንጂ የሰው ድምፅ አይደለም!” እያሉ ጮኹ።

23 ሄሮድስ ለእግዚአብሔር ክብር ሳይሰጥ በመቅረቱ ወዲያውኑ የጌታ መልአክ ቀሠፈውና ተልቶ ሞተ።

24 የእግዚአብሔር ቃል ግን ዘወትር እያደገና እየተስፋፋ ይሄድ ነበር።

25 በርናባስና ሳውል አገልግሎታቸውን ፈጽመው ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ተመለሱ፤ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስንም ከእነርሱ ጋር ይዘውት መጡ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios