Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ሐዋርያት ሥራ 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ጴጥሮስ ወደ አሕዛብ ለምን እንደ ሄደ ማስረዳቱ

1 በይሁዳ ምድር የሚገኙ ሐዋርያትና ወንድሞች አሕዛብ የእግዚአብሔርን ቃል መቀበላቸውን ሰሙ።

2 ጴጥሮስ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ በሄደ ጊዜ በግዝረት አስፈላጊነት የሚያምኑ የአይሁድ ክርስቲያኖች፥

3 “ስለምን ወዳልተገረዙ ሰዎች ቤት ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ?” በማለት ወቀሱት።

4 ጴጥሮስ ግን እንዲህ ሲል ሁሉንም ነገር በተከታታይ ማስረዳት ጀመረ፦

5 “እኔ በኢዮጴ ከተማ በጸሎት ላይ ሳለሁ በተመስጦ ራእይ አየሁ፤ ያየሁትም ትልቅ የመጋረጃ ጨርቅ የሚመስል ነገር በአራት ማእዘን ተይዞ ከሰማይ ሲወርድና ወደ እኔ ሲመጣ ነው፤

6 እርሱን ትኲር ብዬ ስመለከት በመጋረጃው ጨርቅ ላይ እንስሶችን፥ የዱር አራዊትን፥ በልባቸው የሚሳቡ ፍጥረቶችንና በሰማይ የሚበርሩ ወፎችን አየሁ፤

7 ‘ጴጥሮስ ሆይ! ተነሥና እያረድክ ብላ!’ የሚለኝንም ድምፅ ሰማሁ፤

8 እኔ ግን ‘አይሆንም ጌታ ሆይ! ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ ነገር በአፌ ገብቶ አያውቅም’ አልኩ።

9 ነገር ግን ሁለተኛ ጊዜ፥ ‘እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ ርኩስ ነው ማለት አይገባህም’ የሚል መልስ ከሰማይ ሰማሁ።

10 ይህም ሦስት ጊዜ ከሆነ በኋላ ያ ጨርቅ የሚመስል ነገር በሙሉ ወደ ሰማይ ተወሰደ።

11 እነሆ፥ በዚያን ጊዜ ከቂሳርያ ወደ እኔ የተላኩ ሦስት ሰዎች እኔ ወደነበርኩበት ቤት ደረሱ።

12 ያላንዳች ማመንታት ከእነርሱ ጋር እንድሄድም መንፈስ ቅዱስ ነገረኝ፤ እነዚህ ስድስት ወንድሞችም ከእኔ ጋር ነበሩ፤ ከእነርሱም ጋር አብረን ቆርኔሌዎስ ወደ ተባለው ሰው ቤት ገባን።

13 እርሱም መልአክን በቤቱ ውስጥ ቆሞ እንዳየና ‘ወደ ኢዮጴ ሰው ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤

14 እርሱ አንተና ቤተሰብህ ሁሉ የምትድኑበትን ቃል ይነግርሃል’ እንዳለው ነገረን።

15 እኔም መናገር በጀመርኩ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያ በእኛ ላይ እንደ ወረደ ዐይነት በእነርሱ ላይ ወረደ።

16 በዚያን ጊዜ ‘ዮሐንስ በውሃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ’ በማለት ጌታ የተናገረውን ቃል አስታወስኩ።

17 እኛ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ባመንን ጊዜ እግዚአብሔር ለእኛ የሰጠውን ስጦታ ለእነርሱም ከሰጣቸው፤ ታዲያ፥ እግዚአብሔርን ለመከልከል የምችል እኔ ማን ነኝ!”

18 እነርሱም ይህንን በሰሙ ጊዜ የሚመልሱትን አጥተው ዝም አሉ፤ “እንግዲህ እግዚአብሔር ለአሕዛብም ለአዲስ ሕይወት የሚያበቃቸውን ንስሓ ሰጥቶአቸዋል፤” በማለትም እግዚአብሔርን አመሰገኑ።


አማኞች በአንጾኪያ “ክርስቲያን” መባላቸው

19 እስጢፋኖስ ተወግሮ በሞተ ጊዜ በተነሣው ስደት ምክንያት የተበተኑት አማኞች እስከ ፊንቄና እስከ ቆጵሮስ እስከ አንጾኪያም ሄዱ፤ ቃሉንም ለአይሁድ ብቻ እንጂ ለሌሎች አይናገሩም ነበር።

20 ይሁን እንጂ ከቆጵሮስና ከቀሬና የመጡ አንዳንድ አማኞች ወደ አንጾኪያ በሄዱ ጊዜ ለግሪኮች ጭምር ስለ ጌታ ኢየሱስ መልካም ዜናን አበሠሩ።

21 ጌታም በኀይሉ ይረዳቸው ነበር፤ ብዙ ሰዎችም አምነው ወደ ጌታ ተመለሱ።

22 በኢየሩሳሌም የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ይህን ስለ ሰማች በርናባስን ወደ አንጾኪያ ላከችው።

23 እርሱም ሄዶ እግዚአብሔር ጸጋውን ለሕዝቡ እንዴት እንደ ሰጠ ባየ ጊዜ ደስ አለው፤ ሁሉም በሙሉ ልብ ጸንተው ለጌታ ታማኞች ሆነው እንዲኖሩም መከራቸው።

24 እርሱ መንፈስ ቅዱስና እምነት የሞላበት ደግ ሰው ስለ ነበረ ቊጥራቸው ብዙ የሆኑ ሰዎች ወደ ጌታ ተመለሱ።

25 ከዚህ በኋላ በርናባስ ሳውልን ለመፈለግ ወደ ጠርሴስ ሄደ።

26 ባገኘውም ጊዜ ወደ አንጾኪያ አመጣው፤ ሁለቱም አንድ ዓመት ሙሉ ከቤተ ክርስቲያን ጋር በአንድነት ሆነው ብዙ ሰዎችን አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም ለመጀመሪያ ጊዜ በአንጾኪያ “ክርስቲያን” ተብለው ተጠሩ።

27 በዚያን ጊዜ አንዳንድ ነቢያት ተብለው የሚጠሩ መምህራን ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ሄዱ፤

28 ከእነርሱም አንዱ አጋቦስ የሚባለው ተነሥቶ በዓለም ሁሉ ታላቅ ራብ እንደሚሆን በመንፈስ ቅዱስ አነሣሽነት ትንቢት ተናገረ፤ ይህም የሆነው በሮም ንጉሠ ነገሥት በቀላውዴዎስ ዘመን ነበር።

29 ስለዚህ በአንጾኪያ የሚኖሩ ምእመናን በይሁዳ ለሚኖሩ ወንድሞች እያንዳንዳቸው እንደየችሎታቸው በማዋጣት ርዳታ እንዲላክ ወሰኑ።

30 መዋጮም አድርገው በበርናባስና በሳውል እጅ ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ላኩ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios