2 ቆሮንቶስ 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየጳውሎስ ራእይ 1 ምንም እንኳ በመመካት ጥቅም ባይገኝበት መመካት ካስፈለገ ጌታ በሰጠኝ መገለጥና ራእይ እመካለሁ። 2 የክርስቶስ የሆነ አንድ ሰው ዐውቃለሁ፤ ይህ ሰው ከዐሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ተወሰደ፤ (የተወሰደውም ከነሥጋው ይሁን ወይም አይሁን አላውቅም፤ እግዚአብሔር ያውቃል።) 3 ነገር ግን ይህ ሰው ወደ ገነት እንደ ተወሰደ ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ከነሥጋው ይሁን ወይም አይሁን አላውቅም፤ እግዚአብሔር ያውቃል፤ 4 እርሱ ወደ ገነት ተነጥቆ በሰው ቃል ሊገለጥና ሰውም ሊናገረው የማይችለውን ነገር ሰማ። 5 እንደዚህ ባለው ሰው እመካለሁ፤ ስለ ራሴ ግን ከደካማነቴ በቀር ሌላ የምመካበት ነገር የለም። 6 ታዲያ፥ እኔ እውነት ስለምናገር መመካት ብፈልግም ሞኝ አልሆንም፤ ነገር ግን ማንም በእኔ ላይ ከሚያየውና ከእኔ ከሚሰማው በላይ ግምት እንዳይሰጥ ብዬ ከመመካት እቈጠባለሁ። 7 ከነዚህ ከተገለጡልኝ ታላላቅ ነገሮች የተነሣ እንዳልታበይ ሥጋዬን እንደ እሾኽ የሚወጋ ሥቃይ ተሰጠኝ፤ ይህም የሰይጣን መልእክተኛ በመሆን እየጐሸመ በማሠቃየት እንዳልታበይ ያደርገኛል። 8 ይህ የሚያሠቃየኝ ነገር ከእኔ እንዲወገድልኝ ጌታን ሦስት ጊዜ ለመንኩት። 9 ነገር ግን እርሱ “የእኔ ኀይል ፍጹም ሆኖ የሚገለጠው በአንተ ደካማነት ስለ ሆነ ጸጋዬ ይበቃሃል” አለኝ፤ ስለዚህ የክርስቶስ ኀይል በእኔ ላይ እንዲሆን ከምን ጊዜውም ይልቅ በደካማነቴ ደስ እያለኝ ልመካ እወዳለሁ። 10 ኀይል የማገኘው ደካማ በምሆንበት ጊዜ ስለ ሆነ ስለ ክርስቶስ ስደክም፥ ስሰደብ፥ ስቸገር፥ ስሰደድ፥ ስጨነቅ ደስ ይለኛል። የጳውሎስ ስለ ቆሮንቶስ ሰዎች ማሰብ 11 እንደ ሞኝ ተናገርኩ! ታዲያ፥ እንዲህ እንድናገር ያደረጋችሁኝ እናንተ ናችሁ፤ እኔን ማመስገን የሚገባችሁ እናንተ ነበራችሁ፤ እኔ ማንነቴ ያልታወቀ ሰው ብሆንም እንኳ ታላላቅ ከተባሉት ሐዋርያት በምንም አላንስም። 12 እኔ እውነተኛ ሐዋርያ መሆኔን የሚያስረዱት ነገሮች እኔ በመካከላችሁ ሳለሁ በትዕግሥት የፈጸምኳቸው ሥራዎች ናቸው፤ እነዚህም ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ተአምራትም ናቸው። 13 በእናንተ ላይ ሸክም ሳልሆን ከመቅረቴ በቀር ከሌሎች አብያተ ክርስቲያን እናንተን ያሳነስኳችሁ በምንድን ነው? ይህም ጥፋት ሆኖ ከተቈጠረ ይቅር በሉኝ! 14 ወደ እናንተ ለመምጣት ስዘጋጅ አሁን ሦስተኛዬ ጊዜዬ ነው፤ እኔ ሸክም ልሆንባችሁ አልፈልግም፤ እኔ የምፈልገው እናንተን እንጂ ገንዘባችሁን አይደለም። ለልጆቻቸው ሀብት ማከማቸት የሚገባቸው ወላጆች ናቸው እንጂ ልጆች ለወላጆቻቸው ሀብት አያከማቹም። 15 ስለ እናንተ እንኳን ገንዘቤን ራሴንም አሳልፌ ብሰጥ እጅግ በጣም ደስ ይለኛል፤ ታዲያ፥ እኔ ይህን ያኽል አብዝቼ ስወዳችሁ እናንተ የምትወዱኝ እንዲህ በጥቂቱ ነውን? 16 ያም ሆነ ይህ ሸክም አልሆንኩባችሁም፤ ለመሆኑ በተንኰልና በማታለል የያዝኳችሁም ይመስላችኋል። 17 ከላክሁላችሁ ሰዎች በአንዱ እንኳ አማካይነት ተጠቀምኩባችሁን? 18 ቲቶ ወደ እናንተ እንዲመጣ ለመንኩት፤ ያንን ወንድማችንንም ከእርሱ ጋር ላክሁት፤ ታዲያ፥ ቲቶስ ተጠቀመባችሁን? እኔና እርሱ ያገለገልናችሁ በአንድ መንፈስ አልነበረምን? አካሄዳችንስ አንድ አልነበረምን? 19 ሁላችሁም እስከ አሁን የምታስቡት እኛ በእናንተ ፊት ስለ ራሳችን እንደምንከላከል አድርጋችሁ ነውን? እኛ በክርስቶስ ሆነን የምንናገረው በእግዚአብሔር ፊት ነው፤ ወዳጆቼ ሆይ! እኛ ይህን ሁሉ የምንናገረው እናንተን ለማነጽ ብለን ነው። 20 እኔ ወደዚያ በምመጣበት ጊዜ ምናልባት ልትሆኑ እንደምፈልገው ሳትሆኑ፥ እኔም እናንተ እንደምትፈልጉት ሳልሆን እንገናኝ ይሆናል ብዬ እፈራለሁ፤ እንዲሁም በእናንተ ዘንድ ጥል፥ ቅናት፥ ቊጣ፥ ራስ ወዳድነት፥ የሰው ስም ማጥፋት፥ ሐሜት፥ ትዕቢትና ሁከት ይኖሩ ይሆናል ብዬ እፈራለሁ። 21 እንደገና ወደ እናንተ ስመጣ አምላኬ ምናልባት በእናንተ ፊት ያዋርደኛል ብዬ እፈራለሁ፤ ከዚህ ቀደም ኃጢአት ሠርተው በዚሁ በሠሩት ርኲሰት፥ ዝሙትና፥ ስድነት ንስሓ ስላልገቡት ሰዎች ሐዘን ላይ እወድቃለሁ ብዬ እፈራለሁ። |