2 ዜና መዋዕል 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 የሰሎሞን አባት ንጉሥ ዳዊት ቤተ መቅደስ የሚሠራበትን ስፍራ በኢየሩሳሌም በሞሪያ ተራራ ለይ አስቀድሞ አዘጋጅቶ ነበር፤ ይህም ስፍራ እግዚአብሔር ለንጉሥ ዳዊት የተገለጠበት፥ ኢያቡሳዊው ኦርና አውድማ አድርጎ ይጠቀምበት የነበረ ነው። 2 ሰሎሞን በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ በሁለተኛው ወርና በሁለተኛው ቀን የቤተ መቅደሱን ሥራ ጀመረ፤ 3 ንጉሥ ሰሎሞን ያሠራው ቤተ መቅደስ ርዝመቱ ኻያ ሰባት ሜትር ሲሆን፥ ወርዱ ዘጠኝ ሜትር ነበር፤ 4 በመግቢያው በር ያለው በረንዳም ቁመቱ ኀምሳ አራት ሜትር ሲሆን፥ ወርዱ ልክ እንደ ቤተ መቅደሱ ወርድ ዘጠኝ ሜትር ነው፤ ውስጡም በንጹሕ ወርቅ እንዲለበጥ አደረገ። 5 የቤተ መቅደሱ ዋና ክፍል በጥድ እንጨትና በንጹሕ ወርቅ የተለበጠ ሆኖ የዘንባባና የሰንሰለት ቅርጽ ተስሎበት ነበር። 6 ንጉሥ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን እጅግ ውብ በሆነ የከበረ ድንጋይና ከፋርዋይም አገር በመጣ ወርቅ አስጊጦት ነበር። 7 የቤተ መቅደሱን ግድግዳዎች፥ የጣራውን ክፈፎች፥ መቃኖችና መዝጊያዎቹን በወርቅ ለበጣቸው፤ በግድግዳዎቹም ላይ የኪሩቤልን ምስሎች ቀረጸባቸው። 8 ቅድስተ ቅዱሳን ተብሎ የሚጠራው የውስጠኛው ክፍል ርዝመት ዘጠኝ ሜትር ሲሆን፥ ወርዱ ልክ እንደ ርዝመቱ ዘጠኝ ሜትር ነው፤ የቅድስተ ቅዱሳኑም ግንቦች ኻያ ሺህ ኪሎ ያኽል ክብደት ባለው ንጹሕ ወርቅ ተለብጠው ነበር። 9 ምስማሮቹን ለማሠራት አምስት መቶ ሰባ ግራም ወርቅ ፈጅቶበታል፤ የፎቁ ክፍሎች ግንቦችም በወርቅ ተለብጠው ነበር። 10 ንጉሥ ሰሎሞን ሠራተኞቹ የኪሩቤል ምስሎችን ቀርጸው በወርቅ እንዲለብጡአቸውና በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ እንዲያቆሙአቸው አዘዘ። 11-13 ኪሩቤል በቅድስተ ቅዱሳን መግቢያ ትይዩ ጐን ለጐን ቆመው ነበር፤ እያንዳንዱ ኪሩብም ሁለት ክንፎች ነበሩት፤ የእያንዳንዱም ክንፍ ርዝመት ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ነበር፤ ሁለቱ ክንፎች በየአቅጣጫው የተዘረጉ ሆነው በክፍሉ መኻል ላይ እርስ በርሳቸው ይነካካሉ፤ ሌሎቹ ሁለቱ ክንፎቻቸው ደግሞ እያንዳንዱ በየአቅጣጫው ያለውን ግድግዳ የሚነካ ሲሆን፥ የእነዚህ የተዘረጉ ክንፎች ጠቅላላ ወርድ ዘጠኝ ሜትር ያኽል ነበር። 14 ለቅድስተ ቅዱሳኑ ከበፍታና ከሌላም ዐይነት ጨርቅ የተሠራ መጋረጃ ተደርጎለት ነበር፤ የመጋረጃውም ቀለም ሰማያዊ፥ ሐምራዊና ቀይ ሲሆን በላዩም ላይ የኪሩቤል ምስሎች ተቀርጸውበት ነበር። ከነሐስ የተሠሩ ሁለት ምሰሶዎች ( 1ነገ. 7፥15-22 ) 15 ንጉሥ ሰሎሞን የእያንዳንዱ ቁመት ዐሥራ አምስት ሜትር ተኩል የሆነ ሁለት ምሰሶዎችን ሠርቶ፥ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አቆማቸው፤ በእያንዳንዱም ምሰሶ ጫፍ ላይ ቁመታቸው ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር የሆነ ሁለት ጉልላቶች ነበሩ፤ 16 የምሰሶዎቹም ጫፎች የመርበብ ቅርጽ ባላቸው ሰንሰለቶችና ከነሐስ በተሠሩ ቊጥራቸው አንድ መቶ በሆነ የሮማን ፍሬ አምሳል የተሠራ ቅርጽ ተስሎባቸው ነበር፤ 17 ምሰሶዎቹም የቆሙት በቤተ መቅደሱ መግቢያ በር ግራና ቀኝ ነበር፤ በደቡብ በኩል የቆመው ምሰሶ “ያኪን” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፥ በሰሜን በኩል የቆመው ደግሞ “ቦዔዝ” ተብሎ ይጠራ ነበር። |