2 ዜና መዋዕል 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምቤተ መቅደሱን ለመሥራት የተደረጉ ዝግጅቶች ( 1ነገ. 5፥1-18 ) 1 ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስና ለራሱ ቤተ መንግሥት ለመሥራት ወሰነ፤ 2 ስለዚህም ዕቃን የሚያጓጒዙ ሰባ ሺህ፥ ድንጋይ የሚፈልጡ ሰማኒያ ሺህ ሰዎችን በሥራ ላይ አሰማራ፤ ሥራውን የሚቈጣጠሩ ደግሞ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎችን መደበ። 3 ከዚህም በኋላ ለጢሮስ ንጉሥ ኪራም የሚከተለውን መልእክት ላከ፤ “አባቴ ንጉሥ ዳዊት ቤተ መንግሥቱን በሠራበት ጊዜ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ትልክለት እንደ ነበር ለእኔም ላክልኝ፤ 4 አሁን እኔ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስን ለመሥራት በመዘጋጀት ላይ ነኝ፤ ይህም ቤተ መቅደስ እኔና ሕዝቤ በእግዚአብሔር ፊት ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን የምናጥንበት የተቀደሰውን ኅብስት ሳናቋርጥ ለእግዚአብሔር የምናቀርብበት፥ በየቀኑ ጠዋትና ማታ፥ እንዲሁም በሰንበቶች፥ በወር መባቻዎችና በሌሎችም በተቀደሱ በዓላት እግዚአብሔር አምላካችንን ለማክበር የሚቃጠለውን መሥዋዕት የምናቀርብበት የተቀደሰ ስፍራ ይሆናል፤ የእስራኤል ሕዝብ ይህን ለዘለዓለም እንዲያደርጉ እግዚአብሔር አዞአል። 5 የእኛ አምላክ ከሌሎች አማልክት ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ስለ ሆነ ታላቅ ቤተ መቅደስ ልሠራለት ዐቅጃለሁ። 6 እንደ እውነቱ ከሆነ ለእግዚአብሔር በቂ የሚሆን ቤተ መቅደስን ለመሥራት የሚችል ማንም የለም፤ የሰማይና የምድር ስፋት እንኳ እግዚአብሔርን ሊይዘው አይችልም፤ ታዲያ ለእግዚአብሔር ዕጣን ለማጠን የሚበቃ ቤት ከመሥራት በቀር ለእርሱ ማደሪያ ሊሆን የሚችል ቤተ መቅደስ ለመሥራት የምሞክር እኔ ማን ነኝ? 7 እንግዲህ ቅርጽን የማውጣት፥ ወርቅን፥ ብርን፥ ነሐስንና ብረትን የማቅለጥ፥ ሰማያዊ፥ ሐምራዊና ቀይ ልብስ የመሥራት ችሎታ ያለውን ብልኀተኛ ሰው ላክልኝ፤ እርሱም አባቴ ዳዊት ከመረጣቸው በይሁዳና በኢየሩሳሌም ካሉት ብልኀተኞች ሰዎች ጋር ይሠራል። 8 የአንተ እንጨት ቈራጮች እጅግ የሠለጠኑ መሆናቸውን ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ ከሊባኖስ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት የዝግባና የሰንደል እንጨት ላክልኝ። 9 ይህ እኔ ልሠራ ያቀድኩት ቤተ መቅደስ ሰፊና እጅግ የተዋበ መሆን ስለሚገባው እኔም ብዙ እንጨት ቈርጠው በማዘጋጀት የአንተን ሰዎች የሚረዱ፥ የእኔን ሰዎች ወደ አንተ ለመላክ ዝግጁ ነኝ። 10 እንጨት ለሚቈርጡ ለሠራተኞችህ ስንቅ የሚሆን ሁለት ሚሊዮን ኪሎ ስንዴ፥ ሁለት ሚሊዮን ኪሎ ገብስ፥ አራት መቶ ሺህ ሊትር የወይን ጠጅና አራት መቶ ሺህ ሊትር የወይራ ዘይት እልክልሃለሁ።” 11 ንጉሥ ኪራምም ለንጉሥ ሰሎሞን በደብዳቤ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለሚወድ አንተ በእነርሱ ላይ እንድትነግሥ አደረገ።” 12 ንጉሥ ኪራምም በመቀጠል፦ “ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስንና ለራሱ ቤተ መንግሥትን የሚሠራ በጥበብ፥ በማስተዋልና፥ በብልኀት የተሞላ ልጅን ለንጉሥ ዳዊት የሰጠ፥ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን!” አለ። 13 “እነሆ ጥበበኛና በእጅ ሥራ የሠለጠነ ሑራም አቢ ተብሎ የሚጠራ ብልኀተኛ ሰው ልኬልሃለሁ። 14 የሑራም አቢ እናት ከዳን ነገድ ስትሆን፥ አባቱም የጢሮስ ተወላጅ ነው፤ ሑራም አቢ ከወርቅ፥ ከብር፥ ከነሐስ፥ ከብረት፥ ከድንጋይና ከእንጨት ልዩ ልዩ ነገሮችን የመሥራት ችሎታ አለው፤ እንዲሁም ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ጨርቅና ከበፍታ የተለያየ ልብስ መሥራት ይችላል፤ ከዚህም ሌላ ልዩ ልዩ ቅርጽ ማውጣትና በተሰጠውም ንድፍ መሠረት ሁሉን ነገር መሥራት ይችላል፤ ስለዚህ ይህን ሰው በእጅ ሥራ ከሠለጠኑ ከአንተ ሰዎችና ከእነዚያ ለአባትህ ይሠሩ ከነበሩ ሰዎች ጋር እንዲሠራ አድርገው። 15 እንግዲህ ልትልክልን በሰጠኸን ቃል መሠረት ስንዴውን፥ ገብሱን፥ የወይን ጠጁንና የወይራ ዘይቱን ላክልን፤ 16 እኛም የምትፈልገውን ግንድ ሁሉ ከሊባኖስ ተራራዎች ቈርጠን አንድ ላይ በማሰር በባሕር ላይ ተንሳፍፎ እስከ ኢዮጴ እንዲደርስ እናደርጋለን፤ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ልትወስደው ትችላለህ።” የቤተ መቅደሱ ሥራ አጀማመር ( 1ነገ. 6፥1-38 ) 17 ንጉሥ ሰሎሞን ከዚህ በፊት አባቱ ዳዊት ባደረገው ዐይነት በእስራኤል ምድር የሚኖሩትን የውጪ አገር ሰዎች ቈጠረ፤ በዚህም ዐይነት በግዛቱ ውስጥ አንድ መቶ ኀምሳ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ መጻተኞች መኖራቸው ተረጋገጠ፤ 18 ከእነርሱም መካከል ሰባው ሺህ ዕቃ እንዲያጓጒዙ፥ ሰማኒያው ሺህ በተራራዎች ላይ ድንጋይ እንዲፈልጡ አደረገ፤ ደግሞም ሥራው በትክክል መካሄዱን የሚቈጣጠሩ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎችን ሾመ። |