1 ነገሥት 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ኢዮርብዓም መሥዋዕት ለማቅረብ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ በእግዚአብሔር ትእዛዝ የተላከ አንድ ነቢይ እነሆ ከይሁዳ መጥቶ እዚያ ደረሰ፤ 2 ነቢዩም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ያንን መሠዊያ በመቃወም እንዲህ ሲል የትንቢት ቃል ተናገረበት፦ “መሠዊያ! መሠዊያ ሆይ! እግዚአብሔር ስለ አንተ የሚለው ቃል ይህ ነው፦ ‘እነሆ ለዳዊት ቤተሰብ ኢዮስያስ ተብሎ የሚጠራ ልጅ ይወለዳል፤ እርሱም በኮረብታ ላይ ለተሠራው ለአሕዛብ መሠዊያ አገልጋዮች ሆነው መሥዋዕት የሚያቀርቡብህን ካህናት በአንተው ላይ ያርዳቸዋል፤ የሰዎችንም አጥንት በአንተ ላይ ያቃጥላል። 3 እግዚአብሔር ይህን ምልክት ይሰጣል፤ ይህ መሠዊያ ተሰባብሮ ይወድቃል፤ በእርሱ ላይ ያለውም ዐመድ ይበተናል፤ ይህንንም የትንቢት ቃል በእኔ አማካይነት የተናገረው ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ይህ እንደ ተፈጸመ ወዲያውኑ ትገነዘባለህ’ ” አለ። 4 ንጉሥ ኢዮርብዓምም ይህን በሰማ ጊዜ እጁን አንሥቶ ወደ ነቢዩ በማመልከት! “ያዙት!” የሚል ትእዛዝ ሰጠ፤ የንጉሡም ክንድ ወዲያውኑ ድርቅ ብሎ ሽባ ስለ ሆነ የዘረጋውን እጁን መመለስ አልቻለም። 5 የእግዚአብሔርም ነቢይ በእግዚአብሔር ስም በተናገረው የትንቢት ቃል መሠረት በእግዚአብሔር የተሰጠውም ምልክት ተፈጸመ፤ መሠዊያው ወዲያውኑ ተሰባብሮ ወደቀ፤ ዐመዱም መሬት ላይ ፈሰሰ። 6 ንጉሡ ኢዮርብዓም “እባክህ እጄን ያድንልኝ ዘንድ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልኝ!” ሲል የእግዚአብሔርን ነቢይ ለመነው። የእግዚአብሔርም ነቢይ ወደ እግዚአብሔር ጸልዮለት የንጉሡ እጅ ዳነች። እንደ ቀድሞም ሆነች። 7 ከዚህም በኋላ ንጉሡ ነቢዩን “ና ከእኔ ጋር አብረህ ወደ ቤቴ ግባ፤ እህልም ቅመስ፤ ስጦታ እሰጥሃለሁ” አለው። 8 የእግዚአብሔር ነቢይ ግን “የሀብትህን እኩሌታ ብትሰጠኝ እንኳ ወደ ቤትህ አልሄድም፤ ከአንተ ጋር እህል ውሃም አልቀምስም። 9 ምንም ዐይነት እህል ውሃ እንዳልቀምስና ወደ ቤቴ ስመለስም በመጣሁበት መንገድ እንኳ እንዳልሄድ እግዚአብሔር አዞኛል” ሲል መለሰለት። 10 ስለዚህም እርሱ ወደ ቤቴል የመጣበትን መንገድ በመተው በሌላ መንገድ ተመልሶ ሄደ። ሽማግሌው የቤትኤል ነቢይ 11 በዚያን ጊዜ በቤትኤል የሚኖር አንድ ሽማግሌ ነቢይ ነበር፤ ወንዶች ልጆቹ ወደ እርሱ ቀርበው፥ ከይሁዳ የመጣው ነቢይ በቤትኤል ስላደረገውና በንጉሥ ኢዮርብዓምም ላይ ስለ ተናገረው ቃል ሁሉ አወሩለት፤ 12 አባታቸውም “ታዲያ ያ የእግዚአብሔር ነቢይ ከዚያ ተነሥቶ በየትኛው መንገድ ሄደ” ሲል ጠየቃቸው፤ እነርሱም የሄደበትን መንገድ በማመልከት አሳዩት፤ 13 ከዚህም በኋላ እርሱ “አህያዬን ጫኑልኝ!” አላቸው፤ ልጆቹም አህያውን ጭነውለት ሽማግሌው ነቢይ በአህያው ላይ ተቀምጦ፥ 14 ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ነቢይ የሄደበትን መንገድ አቅጣጫ ይዞ ተከተለው፤ በአንድ የወርካ ዛፍ ሥር ተቀምጦም አገኘው። ሽማግሌውም “ከይሁዳ የመጣኸው የእግዚአብሔር ነቢይ አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው። እርሱም “አዎ እኔ ነኝ” ሲል መለሰለት። 15 ሽማግሌውም “ወደ ቤቴ መጥተህ ከእኔ ጋር እህል ብላ” አለው። 16 ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ነቢይ ግን እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ከአንተ ጋር አብሬ ወደ ቤት መሄድም ሆነ ግብዣህን መቀበል አልችልም፤ በዚህም ከአንተ ጋር ምንም ዐይነት እህል ውሃ አልቀምስም፤ 17 በዚህ ቦታ ምንም ዐይነት እህል ውሃ እንዳልቀምስ በመጣሁበት መንገድ እንኳ ተመልሼ እንዳልሄድ እግዚአብሔር አዞኛል።” 18 ከዚህ በኋላ ከቤትኤል የመጣው ሽማግሌ ነቢይ “እኔም እንዳንተው ነቢይ ነኝ፤ ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ወስጄ እንዳስተናግድህ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ነግሮኛል” አለው፤ ሽማግሌው ነቢይ የተናገረው ግን በመዋሸት ነበር። 19 ስለዚህ ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ነቢይ ከሽማግሌው ነቢይ ጋር አብሮት ወደ ቤቱ ሄደ፤ ከእርሱም ጋር ተመገበ። 20 በገበታም ቀርበው ሳሉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ሽማግሌው ነቢይ መጣ፤ 21 ከይሁዳ ለመጣው የእግዚአብሔር ሰው እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘አምላክህ እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዝ ባለመታዘዝ የእግዚአብሔርን ቃል አላከበርክም። 22 ይህን በማድረግ ፈንታ እኔ በዚያ ምንም ዐይነት እህል ውሃ እንዳትቀምስ ወዳዘዝኩህ ቦታ ተመልሰህ በላህ፤ ይህንንም በማድረግህ ምክንያት ትገደላለህ፤ ሬሳህም በቤተሰብህ መቃብር አይቀበርም።’ ” 23 ከተመገቡም በኋላ ሽማግሌው ነቢይ ከይሁዳ መልሶ ላመጣው የእግዚአብሔር ነቢይ አህያውን ጫነለት፤ 24 እርሱም በአህያው ላይ ተቀምጦ ሄደ፤ በመንገድም አንበሳ አገኘውና ገደለው፤ ሬሳውም በመንገድ ላይ ተጋደመ፤ አህያውና አንበሳውም በሬሳው አጠገብ ቆመው ነበር። 25 አንዳንድ ሰዎች በዚያ በኩል ሲያልፉ አጠገቡ ከቆመው አንበሳ ጋር ሬሳው በመንገድ ላይ ተጋድሞ አዩ፤ ሽማግሌው ነቢይ ወደሚኖርበት ወደ ቤቴል ከተማ መጥተው አወሩ። 26 ሽማግሌው ነቢይ ይህን በሰማ ጊዜ “ያ ሰው የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ያልጠበቀው ነቢይ መሆን አለበት! ስለዚህም እግዚአብሔር ለአንበሳ አሳልፎ ሰጥቶታል ማለት ነው” አለ። 27 ከዚህም በኋላ ልጆቹን “አህያዬን ጫኑልኝ!” አላቸው፤ እነርሱም ጫኑለት፤፥ 28 በአህያው ላይ ተቀምጦ ሄደ፤ የነቢዩንም ሬሳ አህያውና አንበሳው እስከ አሁን በአጠገቡ እንደ ቆሙ በመንገድ ላይ ተጋድሞ አገኘው። አንበሳውም የነቢዩን ሬሳ አልበላም፤ በአህያውም ላይ አደጋ አልጣለበትም ነበር። 29 ሽማግሌው ነቢይ ሬሳውን አንሥቶ በአህያው ላይ ጫነው፤ እንዲለቀስለትና እንዲቀበር ወደ ቤትኤል መልሶ ወሰደው። 30 ሽማግሌውም ነቢይ በገዛ ራሱ ቤተሰብ መቃብር ቀበረው፤ እነርሱም “ወንድሜ ሆይ! ወንድሜ ሆይ!” እያሉ አለቀሱለት። 31 ከቀብሩም ሥነ ሥርዓት በኋላ ሽማግሌው ነቢይ ለልጆቹ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ ስሞት በዚሁ መቃብር ቅበሩኝ፤ ሬሳዬንም ከእርሱ ሬሳ አጠገብ አጋድሙት፤ 32 በቤትኤል በሚገኘው መሠዊያ ላይና በሰማርያ ታናናሽ ከተሞች በየኮረብታው ባሉት የማምለኪያ ስፍራዎች ላይ ከእግዚአብሔር በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት ይህ የእግዚአብሔር ነቢይ የተናገረው የትንቢት ቃል በእርግጥ ይፈጸማል።” መቅሠፍትን ያስከተለ የኢዮርብዓም አስከፊ ኃጢአት 33 ይህም ሁሉ ሆኖ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም ከሚያደርገው ክፉ ነገር ሁሉ አልተመለሰም፤ ይልቁንም እርሱ በሠራቸው መሠዊያዎች የሚያገለግሉ ከሌዊ ዘር ውጪ ከሆኑ ቤተሰቦች መምረጡን ቀጥሎ ካህን ለመሆን ከፈለገ ማንኛውንም ሰው ይሾመው ነበር፤ 34 ይህም ኃጢአቱ ለሥረወ መንግሥቱ መጥፋትና በሙሉ ለመደምሰሱ ምክንያት ሆነ። |