Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


1 ነገሥት 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


በሰሜናዊ ግዛት የሚኖሩ የእስራኤል ነገዶች ማመፅ
( 2ዜ.መ. 10፥1-19 )

1 ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ፤ በዚያም እርሱን ለማንገሥ የፈለጉ በእስራኤል ሰሜናዊ ግዛት የሚኖሩ እስራኤላውያን ተሰብስበው ይጠብቁት ነበር።

2 ከንጉሥ ሰሎሞን በመሸሽ ወደ ግብጽ ኮብልሎ በዚያው በግብጽ ይኖር የነበረው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን ወሬ በሰማ ጊዜ ተመልሶ መጣ፤

3 እርሱንም በእስራኤል ሰሜናዊ ግዛት የሚኖሩ ነገዶች መልእክት ልከው አስጠሩት፤ ከእርሱም ጋር አብረው ወደ ሮብዓም በመቅረብ፥

4 “አባትህ ሰሎሞን በእኛ ላይ ከባድ የአገዛዝ ቀንበር ጭኖ አስጨንቆን ነበር፤ አሁን ይህን ከባድ ሸክም ብታቃልልልንና ኑሮአችንን ብታሻሽልልን እኛ ለአንተ እንገዛልሃለን” አሉት።

5 ሮብዓምም “ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሳችሁ ኑ” አላቸው፤ ስለዚህ ሕዝቡ ሄዱ።

6 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሮብዓም የአባቱ የሰሎሞን አማካሪዎች የነበሩትን ሽማግሌዎች በአንድነት ሰብስቦ “እንግዲህ ለዚህ ሕዝብ መልስ መስጠት እንድችል ምን ትመክሩኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

7 ሽማግሌዎቹም “ዛሬ ለእነዚህ ሰዎች ታዛዥ ሆነህ ብታገለግላቸውና ለጥያቄአቸውም ተስማሚ የሆነ መልስ ብትሰጣቸው፥ እነርሱም ዘወትር በታማኝነት ያገለግሉሃል” ሲሉ መለሱለት።

8 ሮብዓም ግን የሽማግሌዎቹን ምክር ቸል በማለት አብሮ ዐደጎቹ ወደነበሩት፥ አሁን ደግሞ አማካሪዎቹ ወደሆኑት ወጣቶች ዘንድ ሄዶ፤

9 “ላደርገው ስለሚገባኝ ነገር ምን ትመክሩኛላችሁ? የአገዛዝ ቀንበር እንዳቀልላቸው ለጠየቁኝስ ሰዎች ምን መልስ ልስጣቸው?” ሲል ጠየቃቸው።

10 እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “አንተ የምትሰጣቸው መልስ ይህ ነው፤ ‘የእኔ ታናሽ ጣት ከአባቴ ወገብ ይበልጥ ትወፍራለች!

11 አባቴ በእናንተ ላይ ከባድ የአገዛዝ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፤ እኔ ደግሞ ይኸው የአገዛዝ ቀንበር ይበልጥ እንዲከብድባችሁ አደርጋለሁ፤ ይኸውም አባቴ በአለንጋ ይገርፋችሁ ነበር፤ እኔ ግን እንደ ጊንጥ በሚናደፍ ጅራፍ በመግረፍ አሠቃያችኋለሁ!’ ”

12 ከሦስት ቀን በኋላ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ ሮብዓም በሰጣቸው ቀጠሮ መሠረት ተመልሰው ወደ እርሱ መጡ፤

13 ንጉሥ ሮብዓምም ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር ውድቅ አድርጎ ሕዝቡን በማመናጨቅ መናገር ጀመረ፤

14 ወጣቶቹም በሰጡት ምክር መሠረት “አባቴ በእናንተ ላይ ከባድ የአገዛዝ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፤ እኔ ደግሞ ይኸው የአገዛዝ ቀንበር ይበልጥ እንዲከብድባችሁ አደርጋለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ይገርፋችሁ ነበር፤ እኔ ግን እንደ ጊንጥ በሚናደፍ ጅራፍ በመግረፍ አሠቃያችኋለሁ!” ሲል መለሰላቸው።

15 ይህም የሆነበት ምክንያት ከሴሎ በመጣው በነቢዩ አኪያ አማካይነት ስለ ናባጥ ልጅ ስለ ኢዮርብዓም እግዚአብሔር የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው፤ ንጉሥ ሮብዓምም የሕዝቡን ሐሳብ ችላ በማለት ሳይቀበል የቀረበትም ምክንያት እግዚአብሔር ይህን ለውጥ ለማድረግ ስለ ወሰነ ነው።

16 ሕዝቡ፥ ንጉሥ ሮብዓም ጥያቄውን እንዳልተቀበለው በተገነዘበ ጊዜ “ከዳዊት ጋር ምን ድርሻ አለን? ከእሴይ ልጅ ከዳዊት ጋር ምን ድርሻ አለን፤ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ወደየቤትህ ሂድ! ዳዊት ሆይ የራስህን ቤት ጠብቅ!” ብለው መለሱለት። ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ወደየቤቱ ሄደ።

17 ሮብዓምም በይሁዳ ግዛት በሚኖሩት ሕዝብ ላይ ብቻ ነገሠ።

18 ከዚህም በኋላ ንጉሥ ሮብዓም የግዳጅ ሥራ ኀላፊ የነበረውን አዶኒራምን ወደ እስራኤላውያን እንዲሄድ ላከው፤ እነርሱ ግን በድንጋይ ወግረው ገደሉት፤ በዚህን ጊዜ ሮብዓም በፍጥነት ወደ ሠረገላው ገብቶ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ አመለጠ።

19 ከዚያን ጊዜም ጀምሮ ሰሜናዊ ክፍል እስራኤል በሚል ስም በዳዊት ሥርወ መንግሥት ላይ ዐመፀ።

20 እስራኤልም ሁሉ ኢዮርብዓም ከግብጽ ተመልሶ መምጣቱን በመገንዘብ ወደ ጉባኤአቸው ጠርተው በእስራኤል ላይ አነገሡት፤ ለዳዊት ትውልዶች ታማኝ ሆኖ የቀረም የይሁዳ ነገድ ብቻ ነበር።


ሸማዕያ የተናገረው የትንቢት ቃል
( 2ዜ.መ. 11፥1-4 )

21 ሮብዓም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከይሁዳና ከብንያም ነገዶች ተውጣጥተው የተመለሱ አንድ መቶ ሰማኒያ ሺህ ምርጥ ወታደሮች ጠርቶ በአንድነት ሰበሰበ፤ ይህንንም ያደረገው የእስራኤልን ነገዶች ወግቶ ግዛቱን እንደገና በቊጥጥሩ ሥር ለማድረግ ዐቅዶ ስለ ነበር ነው።

22 ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ሸማዕያ መጣ፥

23 ለሮብዓም እንዲሁም ለመላው የይሁዳና የብንያም ነገዶች፥ ለቀሩትም ሰዎች ሁሉ

24 “ወንድሞቻችሁ በሆኑት በእስራኤላውያን ላይ አደጋ አትጣሉ፤ ሁላችሁም ወደየቤታችሁ ሂዱ፤ ይህ የሆነው በእኔ ፈቃድ ነው” ብሎ እንዲነግር አዘዘው። እነርሱም ሁሉ ለእግዚአብሔር ቃል ታዛዦች በመሆን ወደየቤታቸው ተመልሰው ሄዱ።


ኢዮርብዓም ፊቱን ከእግዚአብሔር ወደ ሌላ መመለሱ

25 የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በኮረብታማው በኤፍሬም አገር የምትገኘውን የሴኬምን ከተማ ምሽግ አድርጎ በዚያ ለጥቂት ጊዜ ቈየ፤ ከዚያም በመነሣት የፐኑኤልን ከተማ ምሽግ አድርጎ ሠራ፤

26-27 በሐሳቡም “ይህ ሁሉ ነገር እንዲህ ሆኖ ሳለ፥ የእኔ ሕዝብ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ በቤተ መቅደሱ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ማቅረባቸው የሚቀጥል ከሆነ፥ ለይሁዳ ንጉሥ ለሮብዓም ታማኞች በመሆን ወደ እርሱ ዞረው እኔን ይገድሉኛል፤ መንግሥቱም ወደ ዳዊት ቤት ይመለሳል” አለ።

28 በዚህም ጉዳይ ከመከረበት በኋላ የሁለት ጥጆችን ምስል ከወርቅ አሠርቶ ለሕዝቡ “ከዚህ በፊት ታደርጉት በነበረው ዐይነት ለመስገድ እስከ ኢየሩሳሌም መሄድ ይበቃችኋል፤ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክትህ እነሆ እነዚህ ናቸው!” አለ።

29 ከዚህም በኋላ ከወርቅ የተሠሩት ሁለት የኰርማ ምስሎች አንዱን በቤትኤል፥ ሁለተኛውንም በዳን አቆመ፤

30 ሰዎቹም እስከ ዳን ድረስ በጣዖቱ ፊት ተሰልፈው ሄዱ፤ በዚህም ሁኔታ ጣዖትን በማምለክ ኃጢአት ሠሩ፤

31 እንዲሁም ኢዮርብዓም በኮረብታዎች ላይ የማምለኪያ ስፍራዎችን አዘጋጅቶ የሌዊ ነገድ ካልሆኑ ቤተሰቦች መካከል ማንኛውንም ሰው ካህን አድርጎ ሾመ።


በቤትኤል የተጀመረው የጣዖት አምልኮ መወገዝ

32 ኢዮርብዓም በይሁዳ በሚደረገው በዓል ዐይነት ስምንተኛ ወር በገባ በዐሥራ አምስተኛው ቀን የባዕድ አምልኮ በዓል እንዲደረግ ወሰነ፤ ከወርቅ ላሠራቸውም ምስሎች በቤትኤል በሚገኘው መሠዊያ ላይ ለጥጃ ምስሉ መሥዋዕት አቀረበ፤ በዚያም በቤትኤል ለማምለኪያ ባሠራቸው ስፍራዎች የሚያገለግሉ ካህናትን መደበ፤

33 በዓል እንዲሆን እርሱ ራሱ በወሰነው ስምንተኛ ወር በገባ በዐሥራ አምስተኛው ቀን ወደ ቤትኤል ሄደ፤ በዚያም ለእስራኤል በወሰነላቸው መሠረት በዓል ለማክበር በመሠዊያው ላይ መሥዋዕት አቀረበ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios