Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


1 ነገሥት 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ሰሎሞን ከእግዚአብሔር እየራቀ መሄዱ

1 ሰሎሞን ብዙ የባዕዳን አገሮችን ሴቶች አፈቀረ፤ በዚህም መሠረት ከግብጽ ንጉሥ ልጅ ሌላ የሒታውያን፥ የሞአባውያን፥ የዐሞናውያን፥ የኤዶማውያንና የሲዶናውያን ሴቶች ልጆችን አፈቀረ።

2 እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን፥ “አሕዛብ ሴቶችን ያገባችሁ እንደ ሆነ በእርግጥ ወደ አማልእክታቸው ስለሚስቡአችሁ እነርሱን አታግቡ” ብሎ አስጠንቅቆአቸው ነበር፤ እነዚህን ሰሎሞን የወደዳቸው ሴቶች እግዚአብሔር እንዳይጋቡ ከከለከላቸው ሕዝቦች መካከል ናቸው፤ ሰሎሞን ግን ከእነርሱ ጋር በፍቅር ተሰባበረ።

3 ሰሎሞን የነገሥታት ልጆች የሆኑ ሰባት መቶ ሚስቶችና ሦስት መቶ ቊባቶች ነበሩት፤ እነርሱም ሰሎሞንን ከእግዚአብሔር እንዲርቅ አደረጉት፤

4 በተለይም በዕድሜ እየሸመገለ በሄደ መጠን ለባዕዳን አማልክት እንዲሰግድ አደረጉት፤ ሰሎሞን እግዚአብሔርን በታማኝነት በማገልገል እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ሆኖ አልተገኘም።

5 የሲዶናውያን ሴት አምላክ ለነበረችው ለዐስታሮትና ሞሎክ ተብሎ ለሚጠራው ለአጸያፊው ለዐሞናውያን አምላክ ሰገደ።

6 በደል በመሥራትም እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ ሰሎሞን እግዚአብሔርን በቅንነት በመከተል ረገድ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ሆኖ አልተገኘም።

7 ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ በሚገኘው ተራራ ላይ አጸያፊዎች ለሆኑት ከሞሽ ተብሎ ለሚጠራው ለሞአባውያን አምላክና ሞሎክ ተብሎ ለሚጠራው ለዐሞናውያን አምላክ የመስገጃ ስፍራዎችን አዘጋጀላቸው።

8 እንዲሁም የባዕዳን አገሮች ሚስቶቹ ለየአማልክታቸው ዕጣን የሚያጥኑባቸውንና መሥዋዕት የሚያቀርቡባቸውን ስፍራዎች ሠራ።

9-10 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሁለት ጊዜ ተገልጦለት ባዕዳን አማልክትን እንዳያመልክ ያዘዘው ቢሆንም እንኳ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር አልታዘዘም፤ ይልቁንም ከእግዚአብሔር እየራቀ ሄደ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር በሰሎሞን ላይ ተቈጣ፤

11 እንዲህም አለው፤ “ከእኔ ጋር የገባኸውን ቃል ኪዳን ሆን ብለህ ስላፈረስክና ሕጌንም ስላልፈጸምክ፥ መንግሥትህን ከአንተ ወስጄ ከአገልጋዮችህ ለአንዱ ልሰጠው ወስኛለሁ።

12 ይሁን እንጂ ለአባትህ ለዳዊት ስል ይህን የማደርገው አንተ ባለህበት ዘመን ሳይሆን በልጅህ መንግሥት ጊዜ ይሆናል፤

13 ከልጅህም ቢሆን መንግሥቱን በሙሉ አልወስድበትም፤ ለአገልጋዬ ለዳዊትና ለራሴ ርስት እንድትሆን ለመረጥኳት ለኢየሩሳሌም ከተማ ስል አንድ ነገድ እተውለታለሁ።”


በሰሎሞን ላይ የተነሡበት ጠላቶች

14 ስለዚህም እግዚአብሔር የኤዶም ንጉሣዊ ቤተሰብ ወገን የሆነውን ሀዳድን በሰሎሞን ላይ ጠላት አድርጎ አስነሣበት፤

15 ዳዊት ከኤዶማውያን ጋር ይዋጋ በነበረ ጊዜ የጦር አዛዡ ኢዮአብ የሞቱትን ለመቅበር ወጥቶ የኤዶማውያንን ወንዶች ልጆች ሁሉ ፈጅቶ ነበር፤

16 ኢዮአብና የእስራኤል ሠራዊት የኤዶምን ወንዶች ልጆች ገድለው እስኪጨርሱ ድረስ ስድስት ወራት በዚያ ቈይተዋል።

17 ከሞት የተረፉት ሀዳድና ወደ ግብጽ ሸሽተው የሄዱ ጥቂቶች ኤዶማውያን የአባቱ አገልጋዮች ብቻ ነበሩ፤ በዚያን ጊዜ ሀዳድ ገና ሕፃን ነበር፤

18 እነርሱም ከምድያም ተነሥተው ወደ ፋራን ሄዱ፤ በዚያም ጥቂቶች ሰዎች ከእነርሱ ጋር ተቀላቀሉ፤ ከዚህ በኋላ ወደ ግብጽ ተጒዘው ወደ ንጉሡ ቀረቡ፤ ንጉሡም ለሀዳድ መሬትና አንድ መኖሪያ ቤት ሰጥቶ ምግብ ፈቀደለት፤

19 ሀዳድም የንጉሡ ወዳጅ ሆነ፤ ንጉሡም የሚስቱን የጣፍኔስን እኅት ለሀዳድ ዳረለት፤

20 እርስዋም ገኑባት ተብሎ የሚጠራውን ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ እርሱንም ንግሥቲቱ ወስዳ በቤተ መንግሥት አሳደገችው፤ ከንጉሡም ወንዶች ልጆች ጋር አብሮ ኖረ።

21 ሀዳድ በግብጽ ሳለ የንጉሥ ዳዊትንና የሠራዊቱን አዛዥ የኢዮአብን መሞት በሰማ ጊዜ “ወደ አገሬ ተመልሼ እንድሄድ አሰናብተኝ” ሲል ንጉሡን ጠየቀ።

22 ንጉሡም “ስለምን ትሄዳለህ? ወደ አገርህ ለመሄድ ያሰብከው ከቶ ምን ተጓድሎብህ ነው?” አለው። ሀዳድም “ምንም የተጓደለብኝ ነገር የለም፤ ብቻ ወደ ትውልድ አገሬ እንድመለስ ፍቀድልኝ” ሲል ለንጉሡ መለሰ፤

23 እንደገናም እግዚአብሔር ረዞን ተብሎ የሚጠራውን የኤሊዓዳን ልጅ በሰሎሞን ላይ ጠላት አድርጎ አስነሣ፤ ረዞን የጾባ ንጉሥ ከነበረው ከጌታው ከሀዳድዔዜር ኮብልሎ፥

24 የሸፍቶች አለቃ ሆኖ ነበር፤ ይህም የሆነው ዳዊት ሀዳድዔዜርን ድል ነሥቶ የእርሱ ጦር ተባባሪዎች የሆኑትን ሶርያውያንን ከፈጀ በኋላ ነበር፤ ረዞንና ተከታዮቹም ወደ ደማስቆ ሄዱ፤ በዚያም ሲኖሩ እርሱን የሶርያ ንጉሥ እንዲሆን አደረጉት፤

25 ሰሎሞን በኖረበት ዘመን ሁሉ ሃዳድ ካደረሰበት ችግር በተጨማሪ ረዞን የእስራኤል ጠላት ሆነ። ስለዚህ ረዞን በሶርያ ላይ ገዢ ሆኖ በእስራኤል ላይ ጠላትነቱን ቀጠለ።


እግዚአብሔር ለኢዮርብዓም የሰጠው ተስፋ

26 በሰሎሞን ላይ ያመፀው ሌላው ሰው በኤፍሬም ጸሬዳ ተብላ የምትጠራው ክፍል ተወላጅ የሆነ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ነው፤ እርሱም ከሰሎሞን አገልጋዮች አንዱ ነበር፤ እናቱም ጽሩዓ ተብላ የምትጠራ ባልዋ የሞተባት ሴት ነበረች።

27 ኢዮርብዓም ለዐመፅ የተነሣሣበትም ታሪክ እንደሚከተለው ነው፥ በዚያን ጊዜ ሰሎሞን ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ሚሎ ተብሎ የሚጠራውን ጐድጓዳ ስፍራ በመሙላት እየደለደለና የአባቱን የዳዊትን ከተማ ቅጽሮች እየጠገነ በማደስ ላይ ነበር።

28 ኢዮርብዓም ከፍ ያለ የሥራ ችሎታ ያለው ወጣት ነበር፤ ሰሎሞንም ይህ ወጣት ትጉህና ብርቱ ሠራተኛ መሆኑን በተመለከተ ጊዜ በምናሴና በኤፍሬም ነገዶች ግዛት ውስጥ ባሉት ገባሮች ሁሉ ላይ ኀላፊ አድርጎ ሾመው።

29 አንድ ቀን ኢዮርብዓም ከኢየሩሳሌም ወጥቶ በጒዞ ላይ ሳለ አዲስ መጐናጸፊያ የለበሰ፥ ከሴሎ የመጣው ነቢዩ አኪያ ከከተማ ውጪ መንገድ ላይ ብቻውን አገኘው፤

30 አኪያም የለበሰውን አዲስ መጐናጸፊያ አውልቆ ከዐሥራ ሁለት ቈራረጠው፤

31 ኢዮርብዓምንም እንዲህ አለው፤ “ዐሥሩን ቊራጭ ለራስህ ውሰድ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ ‘መንግሥትን ከሰሎሞን ወስጄ ዐሥሩን ነገድ ለአንተ እሰጥሃለሁ፤

32 ለአገልጋዬ ለዳዊትና ከሌላው የእስራኤል ምድር የራሴ ርስት እንድትሆን ለመረጥኳት ለኢየሩሳሌም ከተማ ስል ለሰሎሞን አንድ ነገድ አስቀርቼለታለሁ።

33 ይህንንም የማደርገው ሰሎሞን እኔን ትቶ ባዕዳን የሆኑትን ዐስታሮት ተብላ የምትጠራውን የሲዶና አምላክ፥ ከሞሽ ተብሎ የሚጠራውን የሞአብ አምላክና ሚልኮም ተብሎ የሚጠራውን የዐሞን አምላክ ስላመለከ ነው፤ ሰሎሞን ለእኔ ታዛዥ አልሆነም፤ እርሱ አባቱ ዳዊት ለእኔ ይታዘዝ እንደ ነበር ሕጎቼንና ትእዛዞቼን ባለመጠበቁ በድሎአል።

34 ይሁን እንጂ ከሰሎሞን መንግሥትን በሙሉ አልወስድበትም፤ በሕይወት እስካለም ድረስ በሥልጣን እንዲቈይ አደርገዋለሁ፤ ይህንንም የማደርገው ለመረጥኩትና ሕጎቼንና ትእዛዞቼን ለፈጸመው ለአገልጋዬ ለዳዊት ስል ነው።

35 ስለዚህ መንግሥትን ከሰሎሞን ልጅ ወስጄ ለአንተ ዐሥሩን ነገድ እሰጥሃለሁ፤

36 ይሁን እንጂ ስሜ እንዲጠራባት በመረጥኳት በኢየሩሳሌም አገልጋዬ ዳዊት በፊቴ አንድ ዘር ይኖረው ዘንድ ለልጁ አንድ ነገድ እሰጠዋለሁ

37 ኢዮርብዓም ሆይ! እኔ አንተን የእስራኤል ንጉሥ አደርግሃለሁ፤ አንተ በወደድከው ግዛት ሁሉ ላይ መሪ ትሆናለህ።

38 አገልጋዬ ዳዊት እንዳደረገው በፍጹም ልብህ ብትታዘዘኝ፥ በሕጎቼና በትእዛዞቼ ጸንተህ ብትኖር፥ በእኔ ፊት ሞገስ ብታገኝ፥ እኔ ዘወትር ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ በእስራኤል ላይ እንድትነግሥም አደርግሃለሁ፤ ለዳዊት ባደረግሁት ዐይነት ዘሮችህ ከአንተ በኋላ እንደሚነግሡ አረጋግጥልሃለሁ።

39 በሰሎሞን ኃጢአት ምክንያት የዳዊትን ትውልዶች እቀጣለሁ፤ ይሁን እንጂ የምቀጣቸው ለዘለዓለም አይደለም።’ ”

40 ከዚህም የተነሣ ሰሎሞን ኢዮርብዓምን ለመግደል ሞከረ፤ ነገር ግን ኢዮርብዓም ወደ ግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በመኰብለል አመለጠ፤ ሰሎሞንም እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ እዚያው ቈየ።


የሰሎሞን መሞት
( 2ዜ.መ. 9፥29-31 )

41 ሰሎሞን ያደረገው ሌላው ነገር፥ ያከናወነው ተግባርና ጥበቡ ሁሉ በሰሎሞን የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦአል።

42 ሰሎሞን መኖሪያውን በኢየሩሳሌም አድርጎ በመላው እስራኤል ላይ የነገሠበት ዘመን አርባ ዓመት ነው፤

43 ከዚህ በኋላ ሰሎሞን ሞተ፤ በአባቱ በዳዊት ከተማም ተቀበረ፤ ልጁም ሮብዓም በአባቱ በሰሎሞን እግር ተተክቶ ነገሠ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios