1 ቆሮንቶስ 16 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምለኢየሩሳሌም ምእመናን የተሰበሰበ የገንዘብ ርዳታ 1 ለምእመናን ስለሚደረገው የገንዘብ መዋጮ ለገላትያ አብያተ ክርስቲያን በሰጠሁት መመሪያ መሠረት እናንተም እንዲሁ አድርጉ። 2 እኔ በምመጣበት ጊዜ የገንዘብ መዋጮ እንዳይደረግ በየሳምንቱ እሑድ ከእናንተ እያንዳንዱ በሚያገኘው ገቢ መጠን እያዋጣ ለይቶ ያስቀምጥ። 3 እኔ ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ እናንተ የምትመርጥዋቸውን ሰዎች ያዋጣችሁትን ገንዘብ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄዱ ከመሸኛ ደብዳቤ ጋር እልካቸዋለሁ። 4 የእኔም መሄድ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ፤ አብረውኝ ይሄዳሉ። የጳውሎስ ዕቅዶች 5 በመቄዶንያ በኩል ለመሄድ ስለ ዐቀድኩ በዚያ ሳልፍ እግረ መንገዴን ወደ እናንተ እመጣለሁ። 6 ወደምሄድበት ወደ ማናቸውም ስፍራ ለጒዞዬ የሚሆነኝን ርዳታ እንድታደርጉልኝ ምናልባት እናንተ ዘንድ እቈይ ይሆናል፤ ምናልባትም ክረምቱን ከእናንተ ጋር አሳልፍ ይሆናል፤ 7 አሁን ሳልፍ እግረ መንገዴን ልጐበኛችሁ አልፈልግም፤ የጌታ ፈቃድ ቢሆን ጥቂት ረዘም ያለ ጊዜ ከእናንተ ጋር ለመቈየት ተስፋ አደርጋለሁ። 8 ነገር ግን እስከ ጰንጠቆስጤ በዓል በኤፌሶን እቈያለሁ። 9 ብዙ ሥራ ያለበት ሰፊ በር ተከፍቶልኛል፤ ተቃዋሚዎች ግን ብዙዎች ናቸው። 10 ጢሞቴዎስ ወደ እናንተ በሚመጣበት ጊዜ ያለ ሥጋት ከእናንተ ጋር እንዲቀመጥ እርዱት፤ እርሱም እንደ እኔ የጌታን ሥራ ይሠራል። 11 ስለዚህ ማንም እንዳይንቀው፤ እርሱ ከወንድሞች ጋር ወደ እኔ እንዲመጣ ስለምጠብቀው ወደ እኔ በሰላም ተመልሶ እንዲመጣ ለጒዞው የሚያስፈልገውን እርዱት። 12 ወንድማችን አጵሎስ ከሌሎች ወንድሞች ጋር እናንተን እንዲጐበኛችሁ በጥብቅ ለምኜው ነበር፤ ነገር ግን እርሱ አሁን ወደ እናንተ ለመምጣት አልፈቀደም፤ ሲመቸው ግን ይመጣል። የመጨረሻ ምክርና ሰላምታ 13 ንቁ፤ በእምነት ጸንታችሁ ቁሙ፤ በርቱ፤ ጠንክሩ። 14 የምታደርጉትን ሁሉ በፍቅር አድርጉ። 15 ወንድሞች ሆይ! የእስጢፋኖስ ቤተሰብ በአካይያ አገር የመጀመሪያዎቹ አማኞች እንደ ሆኑና ምእመናንን ለማገልገል ራሳቸውን አሳልፈው እንደ ሰጡ ታውቃላችሁ። 16 እንደእነዚህ ላሉት ሰዎችና ከእነርሱም ጋር በሥራ ለሚደክሙት ሁሉ እንድትታዘዙ አጥብቄ አሳስባችኋለሁ። 17 በእስጢፋኖስና በፈርዶናጥስ በአካይቆስም ወደ እኔ መምጣት ደስ ብሎኛል፤ እናንተ ከእኔ ጋር ባለመገኘታችሁ እነርሱ በእናንተ ምትክ የጐደለኝን አሟልተውልኛል። 18 እነርሱ የእኔን መንፈስና የእናንተንም መንፈስ አሳርፈዋል፤ ስለዚህ እንደእነዚህ ያሉትን ሰዎች ዕወቁአቸው። 19 በእስያ ያሉ አብያተ ክርስቲያን ሰላምታ ያቀርቡላችኋል፤ አቂላና ጵርስቅላ፥ በቤታቸው የሚሰበሰቡ ክርስቲያኖችም ሁሉ ልባዊ ሰላምታ በጌታ ስም ያቀርቡላችኋል። 20 እዚህ ያሉ ክርስቲያኖች ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል፤ በተቀደሰ መሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ። 21 እኔ ጳውሎስ ይህን ሰላምታ በገዛ እጄ ጽፌላችኋለሁ። 22 ጌታን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን! ጌታችን ሆይ፥ ና! 23 የጌታ ኢየሱስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። 24 ፍቅሬ በኢየሱስ ክርስቶስ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። |