1 ቆሮንቶስ 14 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበተለያዩ ቋንቋዎች የመናገር ስጦታዎች 1 እንግዲህ ፍቅርን ተከታተሉ፤ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን ይልቁንም ትንቢት የመናገር ስጦታን በብርቱ ፈልጉ። 2 በተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገር ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይናገርም፤ ምሥጢር የሆነውን ነገር በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ስለሚናገር የሚናገረውን ቃል የሚያውቀው የለም። 3 ትንቢትን የሚናገር ግን ሌላውን ለማነጽ፥ ለማበረታታትና ለማጽናናት ለሰዎች ይናገራል። 4 በተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገር ሰው ራሱን ብቻ ያንጻል፤ ትንቢትን የሚናገር ግን ማኅበረ ክርስቲያንን ያንጻል። 5 ሁላችሁም በተለያዩ ቋንቋዎች ብትናገሩ እወድ ነበር፤ ይበልጥ የምወደው ግን ትንቢትን ብትናገሩ ነው፤ ማኅበረ ምእመናን እንዲታነጽ በተለያዩ ቋንቋዎች የተነገረውን የሚተረጒም ከሌለ፥ በተለያዩ ቋንቋዎች ከሚናገር ሰው ይልቅ ትንቢትን የሚናገር ሰው ይበልጣል። 6 እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ በተለያዩ ቋንቋዎች እየተናገርኩ ብመጣ ምን እጠቅማችኋለሁ? ይልቅስ የምጠቅማችሁ የእግዚአብሔርን ምሥጢር መግለጥን፥ ዕውቀትን፥ ትንቢት መናገርን፥ ትምህርትን ይዤላችሁ ብመጣ ነው። 7 እንደ ዋሽንትና እንደ ክራር ያሉት ነፍስ የሌላቸው የሙዚቃ መሣሪያዎች እንኳ የተለየ የድምፅ ቅኝት ከሌላቸው የሚሰጡት የሙዚቃ ድምፅ ምን መሆኑ እንዴት ይታወቃል? 8 እምቢልታ በማይታወቅ ድምፅ ቢነፋ፤ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል? 9 እንዲሁም እናንተ በቋንቋ ስትነጋገሩ ግልጥ በሆኑ ቃሎች ካልተናገራችሁ የምትናገሩትን ማን ሊያውቀው ይችላል? ለነፋስ እንደምትናገሩ ትሆናላችሁ። 10 በዓለም ላይ ብዙ ቋንቋዎች አሉ፤ ትርጒም የሌለው ቋንቋም የለም። 11 እንግዲህ እኔ የሚነገረውን ቋንቋ ትርጒም የማላውቅ ብሆን ለተናጋሪው ሰው እንግዳ እሆናለሁ፤ እርሱም ለእኔ እንግዳ ይሆናል። 12 እናንተም የመንፈስ ቅዱስን ስጦታዎች በብርቱ ስለምትሹ በይበልጥ መፈለግ የሚገባችሁ ክርስቲያኖች የሚታነጹባቸው ስጦታዎች እንዲበዙላችሁ ነው። 13 ስለዚህ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገር ሰው የመተርጐም ችሎታ እንዲኖረው ይጸልይ። 14 በተለያዩ ቋንቋዎች ብጸልይ መንፈሴ ይጸልያል እንጂ አእምሮዬ ፍሬአልባ ነው። 15 ታዲያ፥ ምን ማድረግ ይገባኛል? በመንፈሴ እጸልያለሁ፤ በአእምሮዬም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈሴ እዘምራለሁ፤ በአእምሮዬም ደግሞ እዘምራለሁ። 16 እንዲህማ ካልሆነ አንተ በመንፈስ እግዚአብሔርን ስታመሰግን፥ አንተ የምትለውን የማያውቅ እንግዳ ሰው ለምስጋና ጸሎትህ “አሜን” ሊል እንዴት ይችላል? 17 እርግጥ አንተ ያቀረብከው የምስጋና ጸሎት በጥሩ ሁኔታ ነው፤ ነገር ግን ሌላው ሰው አይታነጽበትም። 18 እኔ ከሁላችሁ ይበልጥ በተለያዩ ቋንቋዎች ስለምናገር እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። 19 ነገር ግን በተለያዩ ቋንቋዎች በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ቃሎችን ከምናገር ይልቅ ሌሎችን ለማስተማር ስል በቤተ ክርስቲያን አምስት ቃላትን በሚታወቅ ቋንቋ በአእምሮዬ መናገር እወዳለሁ። 20 ወንድሞቼ ሆይ! ለክፉ ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ በአስተሳሰባችሁስ እንደ ሕፃናት አትሁኑ፤ ይልቁንም በአስተሳሰባችሁ የበሰላችሁ ሁኑ። 21 ይህም፦ “ ‘በተለያዩ ቋንቋዎች በሚናገሩ ሰዎችና በባዕድ ሰዎች አፍ ለዚህ ሕዝብ እናገራለሁ፤ ይህም ሆኖ አይሰሙኝም’ ይላል ጌታ እግዚአብሔር” ተብሎ በሕግ ተጽፎአል። 22 ስለዚህ በተለያዩ ቋንቋዎች መናገር ምልክት የሚሆነው ለማያምኑ ሰዎች ነው እንጂ ለሚያምኑ ሰዎች አይደለም፤ የትንቢት ቃል መናገር ግን ምልክት የሚሆነው ለሚያምኑት ሰዎች እንጂ ለማያምኑ ሰዎች አይደለም። 23 ክርስቲያኖች በሚሰበሰቡበት ጊዜ እያንዳንዱ ክርስቲያን በተለያዩ ቋንቋዎች ቢናገርና የማያውቁ ወይም የማያምኑ ሰዎች ቢመጡ ተናጋሪዎችን “እነዚህ ሰዎች አብደዋል” አይሉምን? 24 ነገር ግን እያንዳንዱ የትንቢት ቃል ቢናገርና የማያምን ወይም የማያውቅ ሰው ቢመጣ በሚሰማው ቃል ሁሉ ይወቀሳል፤ እንዲሁም በሚሰማው ቃል ሁሉ ይፈረድበታል። 25 በልቡ የተሰወረው ነገር ይገለጣል፤ በግንባሩም ተደፍቶ “በእርግጥ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ነው!” በማለት ለእግዚአብሔር ይሰግዳል። በማኅበር ጸሎት ጊዜ ሊኖር የሚገባው ሥነ ሥርዓት 26 ወንድሞች ሆይ! እንግዲህ ምን ማድረግ ይገባል? ለጸሎት በምትሰበሰቡበት ጊዜ ከእናንተ አንዱ የመዘመር ስጦታ አለው፤ ሌላው የማስተማር ስጦታ አለው፤ አንዱ ስውር የሆነውን ነገር የመግለጥ ስጦታ አለው፤ አንዱ በተለያዩ ቋንቋዎች የመናገር ስጦታ አለው፤ ሌላው የመተርጐም ስጦታ አለው። ታዲያ፥ ይህ ሁሉ ስጦታ ክርስቲያኖችን የሚያንጽ መሆን አለበት። 27 በተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ ቢኖሩ ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት ሆነው በየተራ ይናገሩ፤ እነርሱ የሚናገሩትንም ሌላ ሰው ይተርጒም። 28 የሚተረጒም ሰው ከሌለ ግን በተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩት በስብሰባ ላይ ዝም ይበሉ፤ ለራሳቸውና ለእግዚአብሔር ብቻ ይናገሩ። 29 ትንቢት የሚናገሩ ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ፤ ሌሎቹ ግን የተነገረውን አዳምጠው በጥንቃቄ ያመዛዝኑ። 30 በስብሰባ ላይ ለሚገኝ ሌላ ሰው አንዳች ራእይ ቢገለጥለት፤ የመጀመሪያው ተናጋሪ ዝም ይበል። 31 እያንዳንዱ እንዲማርና እንዲጽናና ሁላችሁም በየተራ የእግዚአብሔርን መልእክት መናገር ትችላላችሁ። 32 የነቢያት የትንቢት መንፈስ ለነቢያት ይታዘዛል። 33 በእግዚአብሔር ሕዝብ አብያተ ክርስቲያን ሁሉ ዘንድ እንደሚደረገው እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም። 34 ሴቶች በጸሎት ስብሰባ ጊዜ ዝም ይበሉ፤ ሕግ እንደሚያዘው እንዲታዘዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውም። 35 አንዳንድ ነገርን ማወቅ ቢፈልጉ ባሎቻቸውን በቤታቸው ይጠይቁ፤ በጸሎት ስብሰባ ጊዜ ሴት እንድትናገር ተገቢ አይደለም። 36 ለመሆኑ የእግዚአብሔር ቃል የመጣው ከእናንተ ነው? ወይስ የእግዚአብሔር ቃል የደረሰው ወደ እናንተ ብቻ ነው? 37 እኔ ነቢይ ነኝ ወይም እኔ መንፈሳዊ ስጦታ አለኝ የሚል ሰው ቢኖር ይህ የጻፍኩላችሁ የጌታ ትእዛዝ መሆኑን ይወቅ። 38 ይህን የማያውቅ ቢኖር እርሱም አይታወቅም። 39 ስለዚህ ወንድሞች ሆይ! ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፤ በተለያዩ ቋንቋዎች መናገርንም አትከልክሉ። 40 ነገር ግን ሁሉ ነገር በአግባብና በሥነ ሥርዓት ይሁን። |