1 ቆሮንቶስ 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእውነተኛ ፍቅር 1 በሰዎችም ሆነ በመላእክት ቋንቋ የመናገር ችሎታ ቢኖረኝ እንኳ ፍቅር ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሿሿ ጸናጽል መሆኔ ነው። 2 ትንቢት የመናገር ስጦታ ቢኖረኝና ምሥጢርንም ሁሉ ብረዳ፥ ዕውቀትም ሁሉ ቢኖረኝ፥ ተራራን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚያፈልስ እምነትም ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። 3 ያለኝን ሁሉ ለድኾች ባካፍል፥ ሥጋዬም እንኳ ሳይቀር በእሳት እንዲቃጠል አሳልፌ ብሰጥ፥ ፍቅር ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። 4 ፍቅር ያስታግሣል፤ ፍቅር ደግ ያደርጋል፤ ፍቅር ቀናተኛ አያደርግም፤ ፍቅር ያለው ሰው አይመካም፤ ፍቅር ያለው ሰው አይታበይም፤ 5 ፍቅር ሥርዓተቢስ አያደርግም፤ ፍቅር ያለው ሰው የራሱን ጥቅም ብቻ አይፈልግም፤ ፍቅር ያለው ሰው አይበሳጭም፤ ፍቅር ያለው ሰው ቢበደልም በደልን እንደ በደል አይቈጥርም፤ 6 ፍቅር ያለው ሰው እውነት በሆነ ነገር ይደሰታል እንጂ ትክክል ባልሆነ ነገር አይደሰትም፤ 7 ፍቅር ያለው ሰው ሁሉን ይችላል፤ በሁሉም ላይ እምነቱን ይጥላል፤ በሁሉም ላይ ተስፋ ያደርጋል፤ በሁሉ ነገር ይጸናል። 8 ፍቅር ያለው ሰው ምንጊዜም አይወድቅም፤ ትንቢትን የመናገር ስጦታ ያልፋል፤ በተለያዩ ቋንቋዎች የመናገር ችሎታ ያልፋል፤ ዕውቀትም ቢሆን ያልፋል። 9 የምናውቀውም ሆነ ትንቢት የምንናገረው በከፊል ነው። 10 ነገር ግን ፍጹም የሆነው ነገር ሲመጣ ከፊል የሆነው ነገር ይሻራል። 11 ሕፃን በነበርኩ ጊዜ እንደ ሕፃን እናገር ነበር፤ እንደ ሕፃን አስብ ነበር፤ እንደ ሕፃን እመራመር ነበር፤ ሙሉ ሰው በሆንኩ ጊዜ ግን የሕፃንነቴን ጠባይ ተውኩ። 12 አሁን በመስተዋት እንደምናየው ዐይነት በድንግዝግዝ እናያለን፤ በዚያን ጊዜ ግን በግልጥ እናያለን፤ አሁን የማውቀው በከፊል ነው፤ በዚያን ጊዜ ግን እግዚአብሔር እኔን የሚያውቀኝን ያኽል ሙሉ ዕውቀት ይኖረኛል። 13 እንግዲህ እምነት፥ ተስፋ፥ ፍቅር፥ እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ነገር ግን ከእነዚህ መካከል የሚበልጠው ፍቅር ነው። |