1 ቆሮንቶስ 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች 1 ወንድሞቼ ሆይ! አሁን ደግሞ ስለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች እንድታውቁ እፈልጋለሁ። 2 አሕዛብ በነበራችሁበት ጊዜ በማታውቁት ነገር ተመርታችሁ መናገር ወደማይችሉ ጣዖቶች ትወሰዱ እንደ ነበር ታውቃላችሁ። 3 ስለዚህ በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርቶ ኢየሱስን የሚረግም ማንም የለም፤ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ካልሆነ በቀር “ኢየሱስ ጌታ ነው!” የሚል ማንም እንደሌለ እነግራችኋለሁ። 4 ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አሉ፤ መንፈስ ቅዱስ ግን አንድ ነው። 5 ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ፤ ጌታ ግን አንድ ነው። 6 ልዩ ልዩ የሥራ ዐይነቶችም አሉ፤ ነገር ግን ሁሉንም በሁሉ የሚያከናውን አንዱ እግዚአብሔር ነው። 7 ለእያንዳንዱ መንፈስ ቅዱስን የመግለጥ ስጦታ የሚሰጠው ለጋራ ጥቅም ነው። 8 መንፈስ ቅዱስ ለአንዱ ሰው በጥበብ የመናገር ችሎታን ይሰጠዋል፤ ለሌላው ሰው ደግሞ ያው መንፈስ በዕውቀት የመናገርን ችሎታ ይሰጠዋል፤ 9 ያው አንዱ መንፈስ ለአንዱ እምነትን ይሰጠዋል፤ ለሌላውም የመፈወስ ስጦታን ይሰጠዋል፤ 10 እንዲሁም ለአንዱ ተአምራትን የማድረግ ኀይል ይሰጠዋል፤ ለሌላው የትንቢትን ቃል የመናገር ችሎታ ይሰጠዋል፤ ለሌላው ደግሞ ስጦታዎች ከመንፈስ ቅዱስ መሆናቸውን ወይም ከርኩሳን መናፍስት መሆናቸውን ለይቶ የማወቅ ችሎታን ይሰጠዋል፤ እንዲሁም ለአንዱ በተለያዩ ቋንቋዎች የመናገር ችሎታን ይሰጠዋል፤ ለሌላው ደግሞ በተለያዩ ቋንቋዎች የተነገረውን የመተርጐም ችሎታን ይሰጠዋል፤ 11 ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ የሚያደርገው ያው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ እንደ ፈቀደ ለእያንዳንዱ ሰው የተለየ ስጦታን ይሰጠዋል። በአንድ ሰው አካል የተለያዩ ክፍሎች መኖራቸው 12 አንድ ሰው ብዙ የአካል ክፍሎች አሉት፤ የአካል ክፍሎች ብዙዎች ሆነው ሳሉ የሚገኙት በዚያው በአንዱ አካል ነው። እንዲሁም ክርስቶስ ብዙ የሰውነት ክፍሎች እንዳሉት እንደ አንድ አካል ነው። 13 አይሁድም ብንሆን የግሪክ ሰዎች ብንሆን፤ ባሪያዎችም ብንሆን፥ ነጻ ሰዎችም ብንሆን፥ አንድ ሰውነት ለመሆን በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀናል፤ ሁላችንም ከዚሁ ከአንዱ መንፈስ ጠጥተናል። 14 አንድ አካል የተሠራው ከብዙ የአካል ክፍሎች እንጂ ከአንድ የአካል ክፍል ብቻ አይደለም! 15 እግር “እኔ እጅ ስላልሆንኩ የአካል ክፍል አይደለሁም!” ቢል ታዲያ እንዲህ በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? 16 ጆሮም “እኔ ዐይን ስላልሆንኩ የአካል ክፍል አይደለሁም” ቢል፥ ታዲያ፥ እንዲህ በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? 17 አንድ አካል በሙሉ ዐይን ብቻ ቢሆን ኖሮ በምን መስማት ይቻል ነበር? አንድ አካል በሙሉ ጆሮ ብቻ ቢሆን ኖሮ በምን ማሽተት ይቻል ነበር? 18 አሁን ግን እግዚአብሔር እንደ ፈለገው እያንዳንዱን የአካል ክፍል በአካል ውስጥ ተገቢ ስፍራውን ይዞ እንዲገኝ አድርጎታል። 19 ሁላቸውም አንድ ክፍል ብቻ ቢሆን ኖሮ ሙሉ አካል የት በተገኘ ነበር! 20 አሁን ግን ብዙ የአካል ክፍሎች ቢኖሩም አካል ግን አንድ ብቻ ነው። 21 ዐይን እጅን “አንተ አታስፈልገኝም!” ሊለው አይችልም፤ ራስም እግርን “አንተ አታስፈልገኝም!” ሊለው አይችልም፤ 22 እንዲያውም በጣም ደካሞች መስለው የሚታዩ የአካል ክፍሎች ይበልጥ አስፈላጊ ናቸው። 23 አነስተኛ ክብር ያላቸው መስለው ለሚታዩን የአካል ክፍሎች ይበልጥ ክብር እንሰጣቸዋለን፤ ለማየት የሚያሳፍሩ መስለው ለሚታዩን የሰውነት ክፍሎች ይበልጥ ክብር ሰጥተን እንጠነቀቅላቸዋለን፤ 24 ፊት ለፊት ለሚታዩት የአካል ክፍሎች ግን ይህ ሁሉ አያስፈልጋቸውም፤ እግዚአብሔር ግን ለማየት የሚያሳፍሩ መስለው የሚታዩንን የአካል ክፍሎች በበለጠ ክብር እንዲያዙ አድርጎ የአካል ክፍሎችን አገጣጥሞአል። 25 ይህንንም ያደረገው በአካል ክፍሎች መካከል መለያየት ሳይኖር እርስ በርሳቸው እንዲተሳሰቡ ነው። 26 አንዱ የአካል ክፍል ሲሠቃይ ሌሎችም የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረው ይሠቃያሉ፤ አንዱ የሰውነት ክፍል ሲከበር ሌሎቹም የሰውነት ክፍሎች አብረው ከእርሱ ጋር ይደሰታሉ። 27 እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የአካሉ ክፍሎች ናችሁ። 28 ስለዚህ እግዚአብሔር እያንዳንዱ ሰው በቤተ ክርስቲያን የተለያየ አገልግሎት እንዲኖረው አድርጓል፤ በዚህም መሠረት በመጀመሪያ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛ ነቢያትን፥ ሦስተኛ መምህራንን ሾሞአል። ቀጥሎም ተአምራት የሚያደርጉትን፥ ቀጥሎም የመፈወስ ስጦታ ያላቸውን፥ ሰዎችን የመርዳት ስጦታ ያላቸውን፥ አስተዳዳሪዎችንና በተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩትን ሰዎች መድቦአል። 29 ሁሉም ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉም ነቢያት ናቸውን? ሁሉም መምህራን ናቸውን? ሁሉም ተአምራት የሚያደርጉ ናቸውን? 30 ሁሉም የመፈወስ ስጦታ አላቸውን? ሁሉም በተለያዩ ቋንቋዎች የመናገር ችሎታ አላቸውን? ሁሉም በተለያዩ ቋንቋዎች የተነገረውን የመተርጐም ችሎታ አላቸውን? 31 ስለዚህ በጣም የሚበልጡትን ስጦታዎች ለማግኘት ፈልጉ። አሁን ደግሞ ከሁሉ የሚበልጠውን መንገድ አሳያችኋለሁ። |