Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


1 ቆሮንቶስ 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተም እኔን ምሰሉ።


የአምልኮ ሥነ ሥርዓት

2 ዘወትር ስለምታስታውሱኝና የሰጠኋችሁንም ትውፊት አጥብቃችሁ ስለ ያዛችሁ፥ አመሰግናችኋለሁ።

3 ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴት ራስ ወንድ፥ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር አብ መሆኑን እንድታውቁ እወዳለሁ።

4 ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም የትንቢት ቃል የሚናገር ወንድ ሁሉ ራሱን ያዋርዳል።

5 እንዲሁም ራስዋን ሳትከናነብ የምትጸልይ ወይም የትንቢት ቃል የምትናገር ሴት በሴት ላይ ሥልጣን ያለውን ወንድን ታዋርዳለች፤ ራስዋን የማትከናነብ ሴት እንደ ተላጨች ትቈጠራለች።

6 ሴት ራስዋን የማትከናነብ ከሆነ ጠጒርዋን ትቈረጥ፤ ነገር ግን ጠጒርዋን መቈረጥ ወይም መላጨት የሚያዋርዳት ነገር ከሆነ ራስዋን ትከናነብ።

7 ወንድ የእግዚአብሔር መልክና የእግዚአብሔር ክብር የሚገለጥበት ስለ ሆነ ራሱን መከናነብ አይገባውም፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት።

8 ሴት ከወንድ ተገኘች እንጂ ወንድ ከሴት አልተገኘም።

9 እንዲሁም ሴት ለወንድ ተፈጠረች እንጂ ወንድ ለሴት አልተፈጠረም፤

10 በዚህ ምክንያትና በመላእክትም ምክንያት ሴት የሥልጣን ምልክት የሆነውን መከናነቢያ በራስዋ ላይ ታድርግ።

11 በጌታ ባለን ሕይወት ሴት ያለ ወንድ አትኖርም፤ ወንድም ያለ ሴት አይኖርም።

12 ሴት ከወንድ እንደ ተገኘች እንዲሁም ወንድ የሚወለደው ከሴት ነው፤ ነገር ግን ወንድም ሆነ ሴት ሌላውም ነገር ሁሉ የሚገኘው ከእግዚአብሔር ነው።

13 እስቲ ራሳችሁ ፍረዱ፤ ሴት ራስዋን ሳትከናነብ ወደ እግዚአብሔር መጸለይዋ ተገቢ ነውን?

14 ወንድ ጠጒሩን ቢያስረዝም ነውር እንደሚሆንበት ተፈጥሮ ራሱ ያስተምራችሁ የለምን?

15 ሴት ግን ጠጒር የተሰጣት ራሷን ልትሸፍንበት ስለ ሆነ ጠጒርዋን ብታስረዝም ለእርስዋ ክብርዋ ነው።

16 ስለዚህ ጉዳይ መከራከር የሚፈልግ ሰው ቢኖር እኛም ሆንን ወይም ሌሎች የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያን ከዚህ የተለየ ልማድ የለንም።


የቅዱስ ቊርባን ሥርዓት
( ማቴ. 26፥26-29 ፤ ማር. 14፥22-25 ፤ ሉቃ. 22፥14-20 )

17 በምትሰበሰቡበት ጊዜ የምታደርጉት ክፉ እንጂ መልካም ነገር ስላልሆነ በዚህ አሁን በምሰጣችሁ ትምህርት አላመሰግናችሁም።

18 ከሁሉ በፊት በማኅበር በምትሰበሰቡበት ጊዜ በመካከላችሁ መለያየት መኖሩን ሰምቼአለሁ፤ የሰማሁትም ነገር በከፊል እውነት መሆኑን አምናለሁ።

19 ትክክል የሆኑት እነማን እንደ ሆኑ ተለይተው እንዲታወቁ በመካከላችሁ መለያየት መኖሩ ግድ ነው።

20 በአንድነት በምትሰበሰቡበት ጊዜ የምትበሉት የጌታን ራት አይደለም።

21 ስትበሉ አንዱ ሌላውን ሳይጠብቅ ብቻውን ይበላል፤ በዚህ ሁኔታ አንዱ ሲራብ ሌላው ይሰክራል።

22 ኧረ ለመሆኑ የምትበሉበትና የምትጠጡበት ቤት የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትንቃላችሁን? ወይስ ምንም የሌላቸውን ችግረኞች ታሳፍራላችሁን? እንግዲህ ምን ልበላችሁ? ስለዚህ ነገር ላመስግናችሁን? ከቶ አላመሰግናችሁም!

23 ከጌታ የተቀበልኩትና ለእናንተም ያስተላለፍኩላችሁ ትምህርት ይህ ነው፤ ጌታ አልፎ በተሰጠበት ሌሊት ኅብስት አነሣ፤

24 የምስጋናም ጸሎት አድርጎ ቈረሰውና “[እንካችሁ ብሉ፤] ይህ ለእናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ።

25 እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ “ይህ ጽዋ በደሜ የሚመሠረት አዲስ ኪዳን ነው፤ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ።

26 ይህን ኅብስት በምትበሉበትና ይህንንም ጽዋ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ ጌታ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ።

27 ማንም ሰው ያልተገባው ሆኖ ሳለ የጌታን ኅብስት ቢበላና የጌታንም ጽዋ ቢጠጣ የጌታን ሥጋና ደም በማቃለሉ ይጠየቅበታል።

28 ስለዚህ ማንም ሰው ይህን ኅብስት ከመብላቱና ይህንንም ጽዋ ከመጠጣቱ በፊት ራሱን መመርመር አለበት።

29 ማንም ሰው የጌታ ሥጋ ምን መሆኑን ለይቶ ሳያውቅ የጌታን ኅብስት ቢበላና የጌታን ጽዋ ቢጠጣ በራሱ ላይ ፍርድን ያመጣል።

30 ከእናንተ መካከል ብዙዎች የደከሙትና የታመሙት አንዳንዶችም የሞቱት በዚሁ ምክንያት ነው።

31 በራሳችን ላይ ፈርደን ቢሆን ኖሮ ባልተፈረደብንም ነበር።

32 ነገር ግን በኋላ ከዓለም ጋር እንዳንኰነን አሁን ፈርዶ ጌታ ይገሥጸናል።

33 ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ! ለጌታ ራት በምትሰበሰቡበት ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ።

34 መሰብሰባችሁ ለፍርድ እንዳይሆን ከመካከላችሁ የራበው ሰው ቢኖር በቤቱ ይብላ። ስለ ቀረው ነገር እኔ እዚያ ስመጣ ተጨማሪ መመሪያ እሰጣችኋለሁ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Siga-nos em:



Anúncios