ማሕልየ መሓልይ 7 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 አንቺ ልዕልት ሆይ፥ እግሮችሽ በነጠላ ጫማ ውስጥ እንዴት ውብ ናቸው! ዳሌዎችሽስ በአንጥረኛ እጅ እንደ ተሠሩ እንደ ዕንቁዎች ይመስላሉ። 2 እንብርትሽ የወይን ጠጅ እንደማይጐድልበት እንደ ተነጠጠ ጽዋ ነው፥ ሆድሽ እንደ ስንዴ ክምር፥ በአበባም እንደ ታጠረ ነው። 3 ሁለቱ ጡቶችሽ እንደ ሁለቱ መንታ እንደ ሚዳቋ ግለገሎች ናቸው። 4 አንገትሽ እንደ ዝሆን ጥርስ ግንብ ነው፥ ዐይኖችሽ በሐሴቦን ውስጥ በባትረቢ በር አጠገብ የሚግኙ ኩሬዎች ናቸው፥ አፍንጫሽ ወደ ደማስቆ እንደሚመለከት እንደ ሊባኖስ ግንብ ነው። 5 ራስሽ እንደ ቀርሜሎስ ተራራ በላይሽ ነው፥ የራስሽም ጠጉር እንደ ሐምራዊ ሐር ነው፥ ንጉሡ በሹርባው ታስሮአል። 6 ፍቅር ሆይ፥ እንዴት የተዋብሽ ነሽ! እንዴትስ ደስ ታሰኛለሽ! በተድላ 7 ይህ ቁመትሽ የዘንባባ ዛፍ ይመስላል፥ ጡቶችሽም አስካሉን ይመስላሉ። 8 ወደ ዘንባባው ዛፍ እወጣለሁ ጫፎችዋንም እይዛለሁ አልሁ፥ ጡቶችሽ እንደ ወይን ዘለላ የአፍንጫሽም ሽቱ እንደ እንኮይ ናቸው። 9 አፍሽ ለወዳጄ እየጣፈጠ እንደሚገባ፥ የተኙትን ከንፈሮች ይናገሩ ዘንድ እንደሚያደርግ፥ እንደ ማለፊያ የወይን ጠጅ ነው። 10 እኔ የውዴ ነኝ፥ የእርሱም ምኞት ወደ እኔ ነው። 11 ውዴ ሆይ፥ ና፥ ወደ መስክ እንውጣ በመንደሮችም እንደር። 12 ወደ ወይኑ ቦታ ማልደን እንሂድ፥ ወይኑ አብቦ አበባውም ፍሬ አንዠርግጎ ሮማኑም አፍርቶ እንደሆነ እንይ፥ በዚያ ፍቅሬን እሰጥሃለሁ። 13 ትርንጎዎች መዓዛን ሰጡ፥ መልካሞች ፍሬዎች ሁሉ፥ አሮጌው ከአዲሱ ጋር፥ በደጃችን አሉ፥ ውዴ ሆይ፥ ሁሉን ለአንተ ጠበቅሁልህ። |