ማሕልየ መሓልይ 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር። 2 በአፉ መሳም ይሳመኝ፥ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ መልካም ነውና። 3 ዘይትህ መልካም መዓዛ አለው፥ ስምህ እንደሚፈስስ ዘይት ነው፥ ስለዚህ ደናግል ወደዱህ። 4 ሳበኝ፥ ከአንተም በኋላ እንሮጣለን፥ ንጉሥ ወደ ቤቱ አገባኝ፥ በአንተ ደስ ይለናል፥ ሐሤትም እናደርጋለን፥ ከወይን ጠጅ ይልቅ ፍቅርህን እናስባለን፥ በቅንነት ይወድዱሃል። 5 እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እኔ ጥቁር ነኝ፥ ውብም ነኝ፥ እንደ ቄዳር ድንኳኖች እንደ ሰሎሞንም መጋረጃዎች። 6 ፀሐይ መልኬን አክስሎታልና ጥቁር ስለ ሆንኩ አትዩኝ፥ የእናቴ ልጆች ተጣሉኝ፥ የወይን ቦታዎችንም ጠባቂ አደረጉኝ፥ ነገር ግን የእኔን ወይን ቦታ አልጠበቅሁም። 7 ነፍሴ የወደደችህ አንተ ንገረኝ፥ ወዴት ታሰማራለህ? በቀትርስ ጊዜ ወዴት ትመስጋለህ? ስለ ምንስ ከባልንጀሮችህ መንጎች በኋላ እቅበዘበዛለሁ? 8 አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ያላወቅሽ እንደሆነ የመንጎችን ፍለጋ ተከትለሽ ውጪ፥ የፍየል ግልገሎችሽንም በእረኞች ድንኳኖች አጠገብ አሰማሪ። 9 ወዳጄ ሆይ፥ በፈርዖን ሰረገሎች እንዳለ ፈረስ መሰልሁሽ። 10 የጉንጭሽ ውበት በከበረ ሉል፥ አንገትሽም በዕንቁ ድሪ ያማረ ነው። 11 ባለ ብር ጉብጉብ የሆነ የወርቅ ጠልሰም እናደርግልሻለን። 12 ንጉሡ በማዕዱ ሳለ፥ የእኔ ናርዶስ መዓዛውን ሰጠ። 13 ውዴ ለእኔ በጡቶቼ መካከል እንደሚያርፍ እንደ ተቋጠረ ከርቤ ነው። 14 ውዴ ለእኔ በዓይንጋዲ ወይን ቦታ እንዳለ እንደ አበባ እቅፍ ነው። 15 ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ፥ ውብ ነሽ፥ እነሆ፥ አንቺ ውብ ነሽ፥ ዐይኖችሽም እርግቦች ናቸው። 16 ውዴ ሆይ፥ እነሆ፥ አንተ ውብ ነህ፥ መልከ መልካምም ነህ፥ አልጋችንም ለምለም ነው። 17 የቤታችን ሠረገላ የዝግባ ዛፍ ነው፥ የጣሪያችንም ማዋቀሪያ የጥድ ዛፍ ነው። |