Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ኢዮብ 37 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 “ስለዚህም ልቤ ተንቀጠቀጠ፥ ከስፍራውም ውጭ ዘለለ።

2 የድምፁን መትመም ስሙ፥ ከአፉም የሚወጣውን ጉርምርምታ አድምጡ።

3 መብረቁንም ወደ ሰማያት ሁሉ ታች፥ ወደ ምድርም ዳርቻ ይሰድዳል።

4 ከበስተኋላው ድምፅ ያገሣል፥ በግርማውም ድምፅ ያንጐደጉዳል፥ ድምፁም በተሰማ ጊዜ መብረቁን አይከለክልም።

5 እግዚአብሔር በአስደናቂ ሁኔታ በድምፁ ያንጐደጉዳል፥ እኛም የማናስተውለውን ታላቅ ነገር ያደርጋል።

6 በረዶውንና ውሽንፍሩን ብርቱንም ዝናብ፦ በምድር ላይ ውደቁ ይላል።

7 ሰው ሁሉ ሥራውን ያውቅ ዘንድ የሰውን ሁሉ እጅ ያትማል።

8 አውሬዎቹም ወደ ጫካው ይገባሉ፥ በዋሾቻቸውም ይቀመጣሉ።

9 ከተሰወረ ማደሪያውም ዐውሎ ነፋስ፥ ከሰሜንም ብርድ ይወጣል።

10 ከእግዚአብሔር እስትንፋስ በረዶ ተሰጥቶአል፥ የውኆችም ስፋት ይጠጥራል።

11 የውኃውንም ሙላት በደመና ላይ ይጭናል፥ የብርሃኑንም ደመና ይበታትናል፥

12-13 ለተግሣጽ ወይም ለምድሩ ወይም ለምሕረትም ቢሆን፥ ሰው በሚኖርበት ዓለም ላይ ያዘዘውን ሁሉ ያደርግ ዘንድ ፈቃዱ ወደ መራቸው ይዞራሉ።

14 ኢዮብ ሆይ፥ ይህን ስማ፥ ቁም፥ የእግዚአብሔርንም ተአምራት አስብ።

15 በውኑ እግዚአብሔር እንዴት እንደሚያዝዛቸው፥ የደመናውንም ብርሃን እንዴት እንደሚያበራ አውቀሃልን?

16 ወይስ የደመናውን መንሳፈፍ፥ ወይስ በእውቀት ፍጹም የሆነውን ተአምራት አውቀሃልን?

17 በደቡብ ነፋስ ምድር ጸጥ ባለች ጊዜ፥ ልብስህ የሞቀች አንተ ሆይ፥

18 እንደ ቀለጠ መስተዋት ብርቱ የሆኑትን ሰማያት ከእርሱ ጋር ልትዘረጋ ትችላለህን?

19 እኛ ከጨለማ የተነሣ በሥርዓት መናገር አንችልምና ለርሱ የምንለውን አስታውቀን።

20 ማንም በእርሱ ላይ ቢናገር ፈጽሞ ይዋጣልና እኔ መናገር እንደምፈልግ መንገር ድፍረት አይሆንምን?

21 አሁንም ነፋስ አልፎ ካጠራቸው በኋላ፥ ሰው በሰማያት የሚበራውን ብርሃን ሊመለከት አይችልም።

22 ከሰሜን ወርቅ የሚመስል ጌጠኛ ብርሃን ይወጣል፥ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስፈራ ግርማ አለ።

23 ሁሉን የሚችል አምላክን እናገኝ ዘንድ አንችልም፥ በኃይል ታላቅ ነው፥ በፍርድና በጽድቅም ሃብታም ነው፤ አይጨቁንምም።

24 ስለዚህ ሰዎች ይፈሩታል፥ በልባቸውም ጠቢባን የሆኑትን ሁሉ አይመለከትም።”

Siga-nos em:



Anúncios