Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ሕዝቅኤል 48 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የምድሪቱ አከፋፈል

1 የነገዶቹ ስም ይህ ነው። ከሰሜን ወሰን በሔትሎን መንገድ አጠገብ ወደ ሐማት መግቢያ በደማስቆም ድንበር ባለው በሐጸርዔናን በሐማትም አጠገብ በሰሜን በኩል ካለው ከሰሜን ድንበር ይጀምራል። ወርዳቸውም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ይሆናል። ለዳን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።

2 ከዳን ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ አሴር አንድ ድርሻ ይኖረዋል።

3 ከአሴር ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ንፍታሌም አንድ ድርሻ ይኖረዋል።

4 ከንፍታሌም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ምናሴ አንድ ድርሻ ይኖረዋል።

5 ከምናሴ ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ኤፍሬም አንድ ድርሻ ይኖረዋል።

6 ከኤፍሬም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ሮቤል አንድ ድርሻ ይኖረዋል።

7 ከሮቤል ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ይሁዳ አንድ ድርሻ ይኖረዋል።

8 ከይሁዳ ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለምታቀርቡት መባ የሚሆን ድርሻ ይሆናል፤ ወርዱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል፥ ርዝመቱም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ይሆናል፥ ከድርሻዎቹ እንደ አንዱ ይሆናል፥ መቅደሱም በመካከሉ ይሆናል።

9 ለጌታ የምታቀርቡት መባ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ወርዱ ደግሞ አስር ሺህ ክንድ ይሆናል።

10 ይህም ለካህናቱ የተቀደሰ መባ ይሆናል፤ በሰሜን በኩል ሀያ አምስት ሺህ፥ በምዕራብ በኩል ወርዱ ዐሥር ሺህ፥ በምሥራቅ በኩል ወርዱ ዐሥር ሺህ፥ በደቡብ በኩል ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል። የጌታ መቅደስም በመካከሉ ይሆናል።

11 ሌዋውያን በሳቱ ጊዜ፥ እንደ ሳቱት እንደ እስራኤል ልጆች ላልሳቱት ሥርዓቴን ለጠበቁት ከሳዶቅ ልጆች ለተቀደሱት ካህናት ይሆናል።

12 ከምድሪቱ መባ የተቀደሰው መባ ለእነርሱ ይሆናል፥ እጅግ የተቀደሰ ይሆናል፤ በሌዋውያን ድንበር አጠገብ ይሆናል።

13 ለሌዋውያኑ በካህናቱ ድንበር አጠገብ ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም ዐሥር ሺህ ይሆናል፥ ርዝመቱ ሁሉ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም ዐሥር ሺህ ክንድ ይሆናል።

14 ለጌታ የተቀደሰ ስለሆነ ከእርሱ ምንም አይሸጡም አይለውጡም፥ የምድሪቱንም በኵራት ወደ ሌላ አይተላለፍም።

15 በሀያ አምስቱ ሺህ ፊት ለፊት አምስት ሺህ ወርድ ያለው የቀረ ስፍራ ለከተማይቱ ለጋራ ጉዳይዋ፥ ለመኖሪያና ለማሰማርያ ይሆናል፤ ከተማይቱም በመካከሉ ትሆናለች።

16 ልክዋም ይህ ነው፤ በሰሜን በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በደቡብ በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምሥራቅ በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምዕራብም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ይሆናል።

17 ከተማይቱ ማሰማርያ ይኖራታል፤ በሰሜን በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በደቡብ በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምሥራቅ በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምዕራብም በኩል ሁለት መቶ አምሳ ክንድ ይሆናል።

18 በተቀደሰው መባ አጠገብ የተረፈው ርዝመቱ ወደ ምሥራቅ ዐሥር ሺህ ወደ ምዕራብም ዐሥር ሺህ ክንድ ይሆናል። ይህም በተቀደሰው መባ አጠገብ ይሆናል። ምርቷም ከተማይቱን ለሚያገለግሉ ለመብል ይሆናል።

19 ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከተማይቱን የሚያገለግሉ ያርሱታል።

20 መባው ሁሉ ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል፤ የተቀደሰውን መባ ከከተማይቱ ድርሻ ጋር አራት ማዕዘን አድርጋችሁ ትሰጣላችሁ።

21 በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ በዚህና በዚያ ወገን የቀረው ለአለቃው ይሆናል፤ በመባው በሃያ አምስቱ ሺህ ፊት ወደ ምሥራቁ ድንበር፥ በምዕራብም በኩል በሀያ አምስቱ ሺህ ፊት ወደ ምዕራቡ ድንበር፥ እንደ ዕጣ ክፍሎች ሁሉ መጠን፥ ለአለቃው ይሆናል፤ የተቀደሰውም መባና ቤተ መቅደሱ በመካከሉ ይሆናል።

22 የሌዋውያንም ርስት የከተማይቱም ይዞታ ለአለቃው በሆነው መካከል ይሆናል፤ በይሁዳ ድንበርና በብንያም ድንበር መካከል የአለቃ ዕጣ ክፍል ይሆናል።

23 ለቀሩትም ነገዶች እንዲህ ይሆናል፤ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለብንያም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።

24 ከብንያምም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለስምዖን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።

25 ከስምዖንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለይሳኮር አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።

26 ከይሳኮርም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለዛብሎን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።

27 ከዛብሎንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለጋድ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።

28 ከጋድ ድንበር ቀጥሎ በደቡብ በኩል ድንበሩ ከታማር ጀምሮ እስከ ሜሪባ ቃዴስ ውኃ እስከ ግብጽ ወንዝ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሆናል።

29 ለእስራኤል ነገዶች ርስት አድርጋችሁ የምታካፍሉአት ምድር ይህች ናት፥ የእያንዳንዱም ዕጣ እንደዚህ ነው፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

30 የከተማይቱ መውጫዎች እነዚህ ናቸው። በሰሜን ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው።

31 የከተማይቱ በሮች በእስራኤል ነገዶች ስም ይጠራሉ፤ በሰሜን በኩል ሦስት በሮች አሉ፥ አንዱ የሮቤል በር፥ አንዱ የይሁዳ በር፥ አንዱ ደግሞ የሌዊ በር ነው።

32 በምሥራቅ በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው፥ ሦስት በሮችም አሉ፤ አንዱ የዮሴፍ በር፥ አንዱ የብንያም በር፥ አንዱ ደግሞ የዳን በር ነው።

33 በደቡብ በኩል ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው፥ ሦስት በሮችም አሉ፤ አንዱ የስምዖን በር፥ አንዱ የይሳኮር በር አንዱ ደግሞ የዛብሎን በር ነው።

34 በምዕራቡም በኩል ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው፥ ሦስት በሮችም አሉ፤ አንዱ የጋድ በር፥ አንዱ የአሴር በር፥ አንዱ ደግሞ የንፍታሌም በር ነው።

35 ዙሪያዋ ዐሥራ ስምንት ሺህ ክንድ ይሆናል፥ ከዚያም ቀን ጀምሮ የከተማይቱ ስም፦ “ጌታ በዚያ አለ” ተብሎ ይጠራል።

Siga-nos em:



Anúncios