Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ሕዝቅኤል 46 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


አንዳንድ ሕጎች

1 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በውስጠኛው አደባባይ ፊቱ ወደ ምሥራቅ የሚመለከተው በር በስድስቱ የሥራ ቀኖች ይዘጋ፤ ነገር ግን በሰንበት ቀን ይከፈት እንዲሁም በወር መባቻ ቀን ይከፈት።

2 መስፍኑ ከውጭ በኩል ባለው በር በመተላለፊያ መንገድ ገብቶ በበሩ መቃን አጠገብ ይቁም፥ ካህናቱም የእርሱን የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የሰላሙን መሥዋዕት ያቅርቡ፥ እርሱም በበሩ መድረክ ላይ ይስገድ፤ ከዚያም በኋላ ይውጣ፥ በሩ ግን እስከ ማታ ድረስ አይዘጋ።

3 የምድሪቱ ሕዝብ በዚያ በር መግቢያ በሰንበታትና በመባቻ በጌታ ፊት ይስገዱ።

4 መስፍኑ በሰንበት ቀን ለጌታ የሚያቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ነውር የሌለባቸው ስድስት የበግ ጠቦቶችና ነውር የሌለበት አንድ አውራ በግ ይሁን፤

5 ለአውራ በጉ አንድ የኢፍ መስፈሪያ የእህል ቁርባን ይሁን፥ ለእያንዳንዱም ጠቦት እጁ የሰጠችውን ያህል የእህል ቁርባን ይሁን፥ ለአንዱም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ያቅርብ።

6 በመባቻ ቀን ከመንጋው ነውር የሌለበትን አንድ ወይፈን፥ ነውር የሌለባቸውንም ስድስት ጠቦቶችና አንድ አውራ በግ ያቅርብ፤

7 ለወይፈኑ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ለአውራው በግ አንድ የኢፍ መስፈሪያ የእህል ቁርባን ያቅርብ፥ ለጠቦቶቹም እጁ የቻለችውን ያህል፥ ለአንዱም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ያቅርብ።

8 መስፍኑ በሚገባበት ጊዜ በበሩ መተላለፊያ መንገድ ይግባ በዚያው መንገድ ይውጣ።

9 የምድሪቱ ሕዝብ ግን በየክብረ በዓሉ ቀን ወደ ጌታ ፊት በመጡ ጊዜ በሰሜን በር በኩል ሊሰግድ የገባው በደቡብ በር በኩል ይውጣ፥ በደቡብ በር የገባው በሰሜን በር በኩል ይውጣ፤ በፊት ለፊት ባለው ይውጣ እንጂ በገባበት በር አይመለስ።

10 በመካከላቸው ያለው መስፍን በሚገቡበት ጊዜ ይግባ በሚወጡበትም ጊዜ ይውጣ።

11 በበዓላትና በክብረ በዓል ቀኖች የእህሉ ቁርባን ለወይፈኑ አንድ የኢፍ መስፈሪያ፥ ለአውራ በጉ አንድ የኢፍ መስፈሪያ፥ ለጠቦቶቹም እጁ የሰጠችውን ያህል፥ ለኢፍ መስፈሪያም አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ይሆናል።

12 መስፍኑ በፈቃዱ የሚያቀርበውን መሥዋዕት፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ ወይም የሰላሙን መሥዋዕት፥ በፈቃዱ ለጌታ የሚያቀርበውን መሥዋዕት ባቀረበ ጊዜ፥ ወደ ምሥራቅ የሚመለከተው በር ይከፈትለት፥ በሰንበትም ቀን እንደሚያደርግ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የሰላሙን መሥዋዕት ያቅርብ፤ ከዚያ በኋላ ይውጣ፥ ከወጣም በኋላ በሩ ይዘጋ።

13 በየዕለቱም ለሚቃጠል መሥዋዕት ነውር የሌለበትን የአንድ ዓመት በግ ጠቦት ለጌታ ያቅርብ፤ ማለዳ ማለዳም ያቅርበው።

14 ከእርሱም ጋር አንድ ስድስተኛ የኢፍ መስፈሪያ መልካም ዱቄትን መለወሻም የሚሆን በኢን መስፈሪያ ሢሶ ዘይት ማለዳ ማለዳ የእህልን ቁርባን ያቅርብ፤ ይህ የእህል ቁርባን ዘወትር ለጌታ የሚቀርብ ለዘለዓለሙ ሥርዓት ይሁን።

15 እንዲሁም ዘወትር ለሚቃጠለው መሥዋዕት ጠቦቱን፥ የእህሉን ቁርባንና ዘይቱን ማለዳ ማለዳ አቅርቡ።

16 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ መስፍኑ ከልጆቹ ለአንዱ ከርስቱ ስጦታ ቢሰጥ ለልጆቹ ይሁን፤ በውርስም ይዞታቸው ይሆናል።

17 ነገር ግን ከባርያዎቹ ለአንዱ ከርስቱ ስጦታ ቢሰጥ እስከ ነጻነት ዓመት ድረሰ ለእርሱ ይሁን፥ ከዚያም በኋላ ለመስፍኑ ይመለስለት፤ ርስቱ ለልጆቹ ብቻ ይሁን።

18 መስፍኑ ሕዝቡን ከይዞታቸው ሊጨቁናቸው ርስታቸውን አይውሰድባቸው፤ ሕዝቤ ሁሉ ከይዞታቸው እንዳይነቀሉ ከገዛ ይዞታው ለልጆቹ ርስትን ይስጥ።

19 በበሩ አጠገብ ባለው መግቢያ ወደ ሰሜን ወደሚመለከተው ለካህናት ወደሚሆን ወደተቀደሰው ክፍል አገባኝ፤ እነሆ በዚያ በምዕራብ በኩል በስተ ኋላ አንድ ስፍራ ነበረ።

20 እንዲህም አለኝ፦ “ካህናቱ ሕዝቡን ለመቀደስ ወደ ውጭው አደባባይ እንዳያወጡ የበደሉን መሥዋዕትና የኃጢአቱን መሥዋዕት የሚቀቅሉበት፥ የእህሉንም ቁርባን የሚጋግሩበት ስፍራ ይህ ነው።”

21 ወደ ውጭው አደባባይ አወጣኝ በአደባባይም ወዳለው ወደ አራቱ ማዕዘን አዞረኝ፤ እነሆ በእያንዳንዱ የአደባባይ ማዕዘን አደባባይ ነበረ።

22 በአደባባዩ በአራቱ ማዕዘን ርዝመቱ አርባ ክንድ ወርዱም ሠላሳ ክንድ የሆነ የታጠረ አደባባይ ነበረ፤ በአራቱም ማዕዘን ያሉት እኩል ነበሩ።

23 በአራቱም ዙሪያ ግንብ ነበረ፥ በግንቡም ሥር በዙሪያው የመቀቀያ ቦታ ነበረ።

24 እንዲህም አለኝ፦ “እነዚህ የቤቱ አገልጋዮች የሕዝቡን መሥዋዕት የሚቀቅሉባቸው ስፍራዎች ናቸው።”

Siga-nos em:



Anúncios