Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ሕዝቅኤል 38 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


በጎግ የተደረገ ወረራ

1 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

2 የሰው ልጅ ሆይ፥ የማጎግ ምድር፥ በሮሽ፥ በሜሼኽና በቱባል ላይ አለቃ ወደ ሆነው ወደ ጎግ ፊትህን አቅና፥ ትንቢትም ተናገርበት፥

3 እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሮሽ፥ የሜሼኽና የቱባል አለቃ ጎግ ሆይ፥ እነሆ እኔ በአንተ ላይ ነኝ።

4 ወደ ኋላ እመልስሃለሁ፥ መንጠቆ በመንጋጋህ አስገባሃለሁ፥ አንተንና ሠራዊትህን ሁሉ፥ ፈረሶችን፥ ፈረሰኞችን፥ የጦር ልብስ የለበሱትን ሁሉ፥ ሁሉም ሰይፍ የያዙ ጋሻና ራስ ቁርን ካደረጉ ታላቅ ጉባኤ ጋር አወጣሃለሁ፥

5 ሁሉም ጋሻና የራስ ቁር የለበሱ ፋርስ፥ ኢትዮጵያና ፉጥም ከእነርሱ ጋር።

6 ጎሜርንና ሠራዊቱ ሁሉ፥ በሰሜን ዳርቻ ያለው የቶጋርማ ቤትና ሠራዊቱ ሁሉ፥ ብዙ ሕዝቦችም ከአንተ ጋር አወጣለሁ።

7 ተዘጋጅ፥ አንተና ወደ አንተ የተሰበሰቡ ጉባኤ ሁሉ ተዘጋጁ፥ አንተም ጠባቂ ሁናቸው።

8 ከብዙ ዘመንም በኋላ ትፈለጋለህ፤ በኋለኛውም ዘመን፥ የዘለዓለም ባድማ በነበሩ በእስራኤል ተራሮች ላይ ከብዙ ሕዝብ ውስጥ ወደ ተሰበሰበች፥ ከሰይፍ ወደ ተመለሰች ምድር ትገባለህ፤ እርሷም ከሕዝብ ውስጥ ወጥታለች ሁሉም ሳይፈሩ ይቀመጡባታል።

9 አንተም ወደ ላይ ትወጣለህ፥ እንደ ማዕበል ትመጣለህ፤ አንተና ሠራዊትህ ሁሉ፥ ብዙ ሕዝብም ከአንተ ጋር ሆነው ምድርን እንደ ደመና ትሸፍናላችሁ።

10 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚያ ቀን ነገር ወደ ልብህ ይመጣል፥ ክፉ ሐሳብንም ታስባለህ፤

11 እንዲህም ትላለህ፦ ቅጥር ወደሌላቸው መንደሮች እወጣለሁ፤ ያለ ሥጋት በሰላም ወደሚኖሩ፥ ሁሉም ሳይፈሩ ያለ ቅጥር፥ ያለ መወርወሪያና ያለ በር ወደሚቀመጡ እሄዳለሁ፤

12 ምርኮን ልትማርክ፥ ብዝበዛን ልትበዘብዝ፤ ባድማም በነበሩ አሁንም ሰዎች በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ላይ፥ ከአሕዛብም በተሰበሰበ፥ ከብትና ዕቃንም ባገኘ፥ በምድርም መካከል በተቀመጠ ሕዝብ ላይ እጅህን ትዘረጋ ዘንድ።

13 ሳባ፥ ድዳን፥ የተርሴስ ነጋዴዎች፥ መንገዶችዋም ሁሉ እንዲህ ይሉሃል፦ ምርኮን ትማርክ ዘንድ መጥተሃልን? ብዝበዛንስ ትበዘብዝ ዘንድ ብርንና ወርቅንስ ትወስድ ዘንድ ከብትንና ዕቃንስ ትወስድ ዘንድ እጅግስ ብዙ ምርኮ ትማርክ ዘንድ ወገንህን ሰብስበሃልን?

14 ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ ጎግንም እንዲህ በለው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሕዝቤ እስራኤል በሰላም በተቀመጠ ጊዜ በዚያ ቀን አንተ አታውቀውምን?

15 በስተ ሰሜን ርቆ ከሚገኘው ስፍራህ አንተ፥ ከአንተም ጋር ሁሉም በፈረሶች ላይ የተቀመጡ ብዙ ሕዝብ፥ ታላቅ ጉባኤና ብርቱ ሠራዊት ጋር ሆነህ ትመጣለህ።

16 ምድርን እንደሚሸፍን ደመና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። ጎግ ሆይ፥ በአንተ በኩል ቅድስናዬን በፊታቸው በምገልጥበት ጊዜ፥ አሕዛብ እንዲያውቁኝ፥ በኋለኛው ዘመን በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ።


ፍርድ በጎግ ላይ

17 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእነርሱ ላይ እንደማመጣህ፥ ለብዙ ዓመት በተነበዩ በአገልጋዮቼ በእስራኤል ነቢያት እጅ በቀደመው ዘመን ስለ እርሱ የተናገርሁ አንተ ነህን?

18 በዚያም ቀን ጎግ በእስራኤል ምድር ላይ በመጣ ጊዜ፥ ቁጣዬ ከፊቴ ይወጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

19 በቅንዓቴና በቁጣዬ እሳት ተናግሬአለሁ፦ በዚያ ቀን በእስራኤል ምድር ጽኑ መናወጥ ይሆናል፤

20 የባሕር ዓሣዎች፥ የሰማይ ወፎች፥ የምድር አራዊት፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በፊቴ ይንቀጠቀጣሉ፥ ተራሮች ይገለባበጣሉ፥ ገደሎች ይወድቃሉ፥ ቅጥርም ሁሉ ወደ ምድር ይወድቃል።

21 በተራሮቼ ሁሉ ላይ ሰይፍን እጠራለሁ፥ የሰውም ሁሉ ሰይፍ በወንድሙ ላይ ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

22 በቸነፈርና በደም እፈርድበታለሁ፤ ዶፍና የበረዶ ድንጋይ፥ እሳትና ዲን በእርሱና በወታደሮቹ ከእርሱም ጋር ባሉት ብዙ ሕዝቦች ላይ አዘንባለሁ።

23 ታላቅ እሆናለሁ፥ እቀደሳለሁም፥ በብዙ አሕዛብ ዐይን የታወቅሁ እሆናለሁ፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።

Siga-nos em:



Anúncios