Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ሕዝቅኤል 37 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የደረቁ አጥንቶች የተከማቹበት ሸለቆ

1 የጌታ እጅ በላዬ ነበረ፥ ጌታም በመንፈሱ አወጣኝ፥ በሸለቆ መካከልም አኖረኝ፤ እሱም አጥንቶች ሞልተውበት ነበር።

2 በእነርሱ ላይ በዙሪያቸው አሳለፈኝ፤ እነሆ በሸለቆው ፊት እጅግ ብዙ ነበሩ፤ እነሆም፥ በጣም የደረቁ ነበሩ።

3 እንዲህም አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች በሕይወት ይኖራሉን?” እኔም “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ” አልሁ።

4 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ በእነዚህ አጥንቶች ላይ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፥ እናንተ የደረቃችሁ አጥንቶች ሆይ፥ የጌታን ቃል ሰሙ።

5 ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በእናንተ ላይ እስትንፋስ አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላላችሁ።

6 ጅማትንም አደርግላችኋለሁ፥ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ ቆዳ አለብሳችኋለሁ፥ በውስጣችሁ እስትንፋስ አገባባችኋለሁ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

7 እንደ ታዘዝሁት ትንቢት ተናገርሁ፤ ትንቢትንም ስናገር እነሆ የመንኰሻኰሽ ድምፅ ነበር፥ አጥንት ከአጥንቱ ጋር እየሆነ አጥንቶች አንድ ላይ ሆኑ።

8 እኔም አየሁ፥ እነሆ ጅማትና ሥጋ ነበረባቸው፥ ቆዳም ከላይ እስከ ታች ሸፈናቸው፥ እስትንፋስ ግን በውስጣቸው አልነበረም።

9 እንዲህም አለኝ፦ “ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስ ትንቢት ተናገር የሰው ልጅ ሆይ፥ ነፋሱንም እንዲህ በለው፦ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነፋስ ሆይ፥ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፥ በሕይወት እንዲኖሩ በእነዚህ በተገደሉት ላይ እፍ በልባቸው።’”

10 እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፥ እስትንፋስም በውስጣቸው ገባ፥ ሕያዋንም ሆኑ፥ እጅግ በጣም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ።

11 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች መላው የእስራኤል ቤት ናቸው፤ እነሆ፦ “አጥንቶቻችን ደርቀዋል ተስፋችንም ጠፍቶአል፤ ፈጽመን ተቆርጠናል” ይላሉ።

12 ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሕዝቤ ሆይ፥ እነሆ መቃብራችሁን እከፍታለሁ፥ ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ ወደ እስራኤልም ምድር አመጣችኋለሁ።

13 ሕዝቤ ሆይ፥ መቃብራችሁን ስከፍት ከመቃብራችሁም ሳወጣችሁ፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

14 መንፈሴን በውስጣችሁ አሳድራለሁ፥ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፥ በገዛ ምድራችሁ አስቀምጣችኋለሁ፤ እኔም ጌታ እንደ ተናገርሁ፥ እንዳደረግሁትም ታውቃላችሁ፥ ይላል ጌታ።


ሁለቱ በትሮች

15 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

16 አንተ የሰው ልጅ ሆይ፥ አንድ በትር ለራስህ ውሰድ፥ በላዩ “ለይሁዳና ለተባባሪዎቹ የእስራኤል ልጆች” ብለህ ጻፍበት፤ ሌላም በትር ውሰድ፦ በላዩም “የኤፍሬም በትር ለሆነው ለዮሴፍና ለተባባሪዎቹ፥ ለመላው የእስራኤል ቤት” ብለህ ጻፍበት።

17 በእጅህ ውስጥ አንድ በትር እንዲሆኑ አንዱ ከአንዱ ጋር አጋጥመህ ያዛቸው።

18 የሕዝብህ ልጆች፦ “እነዚህ ለአንተ ምን እንደ ሆኑ አትነግረንምን?” ሲሉህ፥

19 እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በኤፍሬም እጅና በተባባሪዎቹ በእስራኤል ነገዶች ያለውን የዮሴፍን በትር እወስዳለሁ፥ ከይሁዳ በትር ጋር አስቀምጣቸዋለሁ፥ አንድ በትር አደርጋቸዋለሁ፥ በእጄም አንድ ይሆናሉ።

20 በላያቸው የምትጽፍባቸው በትሮች በዓይናቸው ፊት በእጅህ ይሆናሉ።

21 አንተም እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የእስራኤልን ልጆች ከሄዱባቸው ሕዝቦች መካከል እወስዳለሁ፥ ከየስፍራውም እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ።

22 በምድሪቱ በእስራኤል ተራሮች ላይ አንድ ሕዝብ አደርጋቸዋለሁ፥ አንድ ንጉሥ ለሁሉም ንጉሥ ይሆናል፤ ዳግመኛ ሁለት ሕዝብ አይሆኑም፥ ከዚያ ወዲያም ሁለት መንግሥቶች ሆነው አይከፈሉም።

23 በጣዖቶቻቸው፥ በአጸያፊ ነገሮቻቸውና በመተላለፋቸው ሁሉ ዳግመኛ አይረክሱም፤ ኃጢአት ከሠሩባቸው መኖሪያ ቤቶቻቸው ሁሉ አድናቸዋለሁ፥ አነጻቸዋለሁም፤ እነርሱ ለእኔ ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።

24 አገልጋዬ ዳዊት ንጉሥ ይሆናቸዋል፤ ሁሉም አንድ እረኛ ይኖራቸዋል፤ በፍርዴ ይሄዳሉ፥ ትእዛዜን ይጠብቃሉ ይፈጽሟቸዋልም።

25 ለአገልጋዬ ለያዕቆብ በሰጠኋት፥ አባቶቻችሁም በኖሩባት ምድር ይኖራሉ፤ እነርሱ፥ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ለዘለዓለም በእርሷ ይኖራሉ፤ አገልጋዬ ዳዊት ለዘለዓለም ልዑላቸው ይሆናል።

26 የሰላም ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደርጋለሁ፥ የዘለዓለም ቃል ኪዳን ይሆንላቸዋል፤ አጸናቸዋለሁ፥ አበዛቸዋለሁ፥ መቅደሴንም በመካከላቸው ለዘለዓለም አኖራለሁ።

27 ማደሪያዬ በላያቸው ላይ ይሆናል፤ እኔ አምላካቸው እሆናለሁ፥ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።

28 መቅደሴም ለዘለዓለም በመካከላቸው በሆነ ጊዜ፥ እስራኤልን የቀደስኩ እኔ ጌታ እንደሆንሁ አሕዛብ ያውቃሉ።

Siga-nos em:



Anúncios